“የሴቷ ጥቃት የእኔም ነው፤ ዝም አልልም!”

ይህ ዓለም የወንዶች ዓለም ነው የሚለው አባባል፤ከአባባልነት የተሻገር ጥሬ ሀቅ አለው።ያልተበረዘ ያልተከለሰ የወል እውነትም አለው።ይህ ዓለም ለወንዶች እንዲመች ሆኖ የተዋቀር ይመስላል።ዛሬም ሴቶች ከወንዶች እኩል ስራ አያገኙም። ቢያገኙ እንኳ እኩል አይከፈላቸውም። በምዕራባውያን ዘንድ ሳይቀር ከወንዶች እኩል የኃላፊነት ቦታ አያገኙም።

በአጠቃላይ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው በተጻፈም ባልተጻፈም ሕግ የተገደበ ነው። በ21ኛው መክዘ ዛሬም የሴቶች መብትና እኩልነት አለመረጋገጡ ሳያንስ ጾታዊ ጥቃቶች ተባብሰው ቀጥለዋል። እንደ አፍጋኒስታን ባሉ ሀገራት ደግሞ የከፋ ነው። ወደ ሀገራችን ስንመጣም ገና ብዙ የቤት ስራ አለብን። ለዛሬው መጣጥፌ መግፍኤ ወደ ሆነው ሰሞነኛ የፀረ ጾታዊ ጥቃት ቀን ላምራ።ተከተሉኝ።አዎ ! እናታችን ሀገራችን እህታችን ሚስታችን ልጃችን ሴት ናትና ተከተሉኝ።

በዓለም ለ33ተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ ከኅዳር 16 እስከ ታህሳስ 01/2017 ዓ.ም በሁሉም ከተሞች በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቶ ባለፈው ማክሰኞ ተጠናቋል። ዓለም አቀፍ የነጭ ሪቫን ቀን ወይም 16 ቱ የፀረ- ጾታዊ ጥቃት ቀን ንቅናቄ በተለያዩ ሴቶችን ከጥቃት ለመታደግ በሚረዱ ተግባራት ላይ በመመሥረት በየዓመቱ ይከበራል። የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ንቅናቄ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በጋራ በመሆን በድሬዳዋ ከተማ ተጀምሯል። በፕሮግራሙ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀሪቡ ቡዕዝ እና የክልል የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በንቅናቄው “የሴቷ ጥቃት የእኔም ነው ዝም አልልም” በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ መርሀ ግብሮች ተከናውኗል። በንቅናቄ ቀናቱም የሴቶች ጥቃት አስከፊነት ዙሪያ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ድርጊቱን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። መንግሥት ጾታዊ ጥቃት ከግለሰብ ጀምሮ በማኅበረሰብ እና በሀገር ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሴቶች እና ሕፃናት ሰብዓዊ መብት መከበር ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብሎ በማጽደቅ በሥራ ላይ መሆኑን ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

የሴቶች ጉዳይ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊነት ብቻ አለመሆኑንም ገልጸዋል። ሴቷ ጥቃት ከደረሰባት በኋላም ተገቢው የሆነ የጤና እና የሥነ ልቦና ጉዳት ማገገሚያ ተቋማት እንድታገኝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየሠራን ነው። በቀጣይም ሁሉም የሴቷ ጥቃት የእኔ ነው በማለት ሴቷ ጥቃት እንዳይደርስባት፤ ከደረሰባትም ጥቃት አድራሾች ተገቢውን እርምጃ እንዲያገኙ ትብብር ያድርግ ነው ያሉት።

የጾታዊ ጥቃት ለተከታታይ 16 ቀናት በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች በመላ ሀገሪቱ መከበሩ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በቀጣይ ግን እያንዳንዱ መስሪያ ቤት የመደበኛ እቅዱ አካል አድርጎ ሊሰራበት ይገባል። አዎ! ለአንድ ተቋምና ለሴቶች ብቻ የሚተው ተግባር አይደለም።ሁሉም በባለቤትነት ሊሳተፉበት የሚገባ ንቅናቄ መሆን አለበት። ከሕዝባችን ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ሴቶች የረሳ ሀገር የትም ሊደርስ አይችልም።

ቢቢሲ በአንድ ሪፖርታዥ ካሚላት መህዲ፣ ሃና ላላንጎ፣ መዓዛ ካሳ፣ ፋጡማ ኡጋስ፣ አያንቱ ሙስጠፋ፣ አዳናዊት ይሄይስ፣ ጫልቱ አብዲ፣ ወዘተረፈ በተለያየ የዕድሜ፣ የማኅበረሰብ እና የኢኮኖሚ ደረጃ የሚገኙ ናቸው። እንስቶቹ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ናቸው። ከመሀል አዲስ አበባ እስከ ምሥራቅ ሐረረጌ፣ ከባሕር ዳር እስከ ጅግጅጋ። ከሰባት ዓመቷ ሄቨን እስከ የሁለት ልጆች እናቷ አያንቱ ሁሉም ግን የአሰቃቂ ፆታዊ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል።

ሃና ላላንጎ እና ፋጡማ ኡጋስ በአሰቃቂ ሁኔታ በደቦ ተደፍረው ተገድለዋል። እነዚህ ሴቶች አይተዋወቁም። አብረው ማዕድ አልተጋሩም። የደረሰባቸው ግፍ ግን ያመሳስላቸዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከሰቱት ግጭቶች፣ የእርስ በርስ ጦርነቶች እና የፀጥታ መደፍረሶች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን አባብሰውታል።

ነገር ግን በኢትዮጵያ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በጦርነት እና በግጭት አውድ ውስጥ ብቻ የሚፈጸሙ አይደሉም። ግጭት በሌለበት ጊዜም በኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የሴቶች ጥቃቶች ይፈጸማሉ።ሌላ ጥቃት… ሌላ ስጋት… አዳናዊት ይሄይስ ስትገደል 17 ዓመቷ ነበር። ከአስር ዓመቷ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በእንጀራ አባቷ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሲፈጸምባት ነበር።

እኤአ በ2015 ዓ.ም መጀመሪያ በእንጀራ አባቷ ሲፈጸምባት የነበረው ተደጋጋሚ የአስገድዶ መድፈር ከእናቷ ጆሮ ኋላ ላይም ወደ ፖሊስ ይደርሳል።ፖሊስ ተከሳሹን ለመያዝ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት ወንጀሉን የፈጸመው ሚካኤል ሽመልስ የተባለው ግለሰብ ከአካባቢው ይሰወራል። ከሰዓታት በኋላ ወደ ቤቱ የተመለሰው ግለሰቡ ከእናቷ ጋር የነበረችውን አዳናዊት ይሄይስን “ለፖሊስ የጠቆምሽው እና ያዋረድሽኝ አንቺ ነሽ” በማለት በስለት ወግቶ ገድሏታል።

ይህ ክስተት ከሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች ጋር በብዙ ተመሳሳይነት አለው። ሴቶች የደረሰባቸውን ጥቃት በመናገራቸው ብቻ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ይወድቃል። የቅርብ ዘመዶቻቸው ሳይቀሩ ለደኅንነታቸው ይሰጋሉ። ከአንድ ዓመት በፊት የመጀመሪያ ልጇ በቤት አከራይዋ ተደፍራ የተገደለችባት አበቅየለሽ አደባ ለዚህ ማሳያ ናት። ከአምስት ዓመታት በፊት ወርሃ ጥር ላይ መዓዛ ካሳ የተባለች የሁለት ልጆች እናት በሥራ ባልደረባዋ በስለት ተወጋች። መዓዛ ለሁለት ወራት ያህል ህክምና ስትከታተል ቆይታ ሕይወቷ አልፏል። መዓዛን ለሞት የዳረጋትን ጥቃት ያደረሰባት ግለሰብ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ለህክምን ከእስር ቤት በወጣበት አምልጧል። ከዚያ በኋላም በስልክ እየደወለ ቤተሰቦቿን ያስፈራራ እንደነበር በጊዜው ተዘግቦ ነበር።

ይህ የፆታዊ ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት አስተማሪ አለመሆን ለፆታዊ ጥቃቶች መባባስ ምክንያት መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ያነሳሉ።ካሚላት መህዲ ከስድስት ዓመት በፊት “የኔ ጥቃት እንደ ዋዛ እንደ ተራ ነገር ሆኖ ለሌሎቹ መጥፎ ምሳሌ ሆኗል። አሁን አሲድ ጥቃት እንደ ፌዝ ሆኖ የዓይን ብርሃንን እስከማጥፋት ደርሷል። በሰዓቱ የማያዳግም ውሳኔ ቢወሰን ኖሮ ዛሬ በአሲድ የተጠቃን ሴቶች አንበረክትም ነበር” ስትል ለቢቢሲ ተናግራ ነበር።

ብዙዎቹ ፆታዊ ጥቃት የሚያመሳስላቸው ነገር ጥቃት ፈጻሚዎቹ የቅርብ ሰው መሆናቸው ነው። የሴታዊት እንቅስቃሴ መሥራች እና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ስኂን ተፈራ፤ “እነዚህ ወንዶች ማኅበረሰባችን ውስጥ ያሉ የእኛው ወንድሞች፣ አባቶች ጓደኞች ናቸው ከሌላ ቦታ መጥተው አልደፈሩም” ይላሉ።

“በሕጉ ላይ ያሉ ክፍተቶች አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ያስቆርጣሉ።” ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች እና የእንስታዊ እንቅስቃሴ አቀንቃኞች የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለው ክፍተት ለፆታዊ ጥቃት መባባስ ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ። ዶ/ር ስኂን ተፈራ፤ “ከፍተኛ ክፍተት ያለው የፍትሕ ሂደቱ ላይ ነው” ይላሉ። “አጥፊዎች የእውነት ቢያዙ፣ የእውነት ቢቀጡበት፣ የፍርድ ሂደቱ ይሄ ሁሉ ክፍተት ኖሮበት ብዙ ሰው ስለሚያመልጥ እና ያለ ቅጣት ስለሚኖር ነው እዚህ ደረጃ የደረስነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

የፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች “ሪፖርት አያደርጉም” የሚል ችግር ይነሳ እንደነበር የሚጠቅሱት የሴታዊት ዳይሬክተር፤ “ከዚያ በኋላ ግን ብዙ ክፍተት እያየን ነው። ብዙ ጊዜ ሴቶች በፆታዊ ጥቃት ዙሪያ ፖሊስ ጋር ሲሄዱ ከዚያ በኋላ የሚያገኙት ምላሽ ነው እውነት ተስፋ የሚያስቆርጠው። ፋይል ለመክፈት ዳተኝነት ይታያል። ሕፃናት ተደፍረው ሲሄዱ አለማመን አለ” ሲሉ ይናገራሉ።

በፖሊስ እና በዐቃቤ ሕግ መካከል “ከፍተኛ ክፍተት” እንዳለ ዶ/ር ስኂን ያነሳሉ። ይህ ክፍተት የፆታዊ ጥቃት ወንጀሎች ምርመራ በሚከናወንበት ጊዜ አለመናበብ እና “ንትርክ” እንዳለ ያክላሉ። ጠበቃ እና የሕግ አማካሪዋ አዲስ መሐመድም በተመሳሳይ “የፍትሕ ሂደቱ ላይ ክፍተት አለ” በሚለው አስተያየት ይስማማሉ። ለስምንት ዓመታት የሴቶች እና የሕፃናት ዐቃቤ ሕግ ሆነው የሠሩት አዲስ፤ በወንጀል ሕጉ ላይ ፆታዊ ጥቃትን በተመለከተ የሰፈሩት ድንጋጌዎች “መሻሻል አለባቸው” ይላሉ።

የሕግ አማካሪዋ አክለውም፤ “የወንጀል አፈጻጸሙ በጣም ዘግናኝ ሲሆን እና የደረሰው ጉዳት የማይተካ ሲሆን ቅጣቱ በጣም አስተማሪ መሆን አለበት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በወንጀል ሕጉ ላይ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ከሚሏቸው ጉዳዮች መካከል ድንጋጌዎች ይበልጥ ግልጽ እንዲሆኑ ማድረግ ቀዳሚው ነው። ከዚህ በተጨማሪ “የቅጣት ሁኔታው ቢሻሻል የማስጠንቀቅ አቅሙ በጣም ከፍተኛ ይሆናል” ሲሉ ወንጀለኞች ላይ የሚተላለፉ ቅጣቶችን የሚወስኑት የሕጉ ድንጋጌዎችም ሊሻሻሉ እንደሚገባ የሕግ ባለሙያዋ ያነሳሉ።

ቅጣት ከተላለፈ በኋላም አፈጻጸሙ ላይ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ ጠበቃ አዲስ ጠቁመዋል። “አፈጻጸሙን በተመለከተ ከሴቶች እና ሕፃናት ጋር በተያያዘ በጣም ዘግናኝ የሆኑ ወንጀሎች ተፈጽመው ቢበዛ ዕድሜ ልክ ነው የሚቀጣው ።ይህ መሆኑ ማኅበረሰቡ እንዳይማር አድርጎታል” ይላሉ።

ዶ/ር ስኂን በበኩላቸው፤ ይህን የሕግ “ክፍተት” ማሻሻል ብቻውን “ችግሩን ይፈታዋል ብዬ አላምንም” ይላሉ። አክለውም፤ “ሕጉ አንሷል የሚሉ አጥፊዎቹ ሕጉ በሚፈቅደው መጠን እየተቀጡ አለመሆናቸውን ሳያገናዝቡ ነው” ሲሉ ይሞግታሉ። የሴታዊት ዳይሬክተሯ አክለውም “ያሉትን ክፍተቶች የአሠራር ሂደቶች ነው ማስተካከል ያለብን፤ ያለውንም ሕግ መቼ ሠራንበት መጀመሪያ” ሲሉም ይጠይቃሉ።

“በሕጉ ላይ ያሉ ክፍተቶች አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ያስቆርጣሉ” የሚሉት፤ ዶ/ር ስኂን “ዐቃቤ ሕግ የሚከስበት የሕግ ድንጋጌ የትኛው ነው? የሚለው ራሱ የዚያን ተከሳሽ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ነው። የሕግ ክፍተቱን ለመመዘን ይከብዳል” ሲሉ ያስረዳሉ። የሕግ ባለሙያዋ አዲስ መሐመድም፤ “ሕጎቹን ብቻ ማሻሻል መፍትሔ አይደለም፤ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች እንዲቀንሱ ዕድል ይፈጥራል” ይላሉ። ነገር ግን ከሕግ ድንጋጌዎች ማሻሻያ ጎን ለጎን ወንጀሉን ከሚጠረጥሩት ጀምሮ ፍርድ እስከሚሰጡት ሰዎች ድረስ “የተለየ ሥልጠና መውሰድ አለባቸው” በማለት ሊወሰዱ ስለሚችሉ እርምጃዎች ያነሳሉ።

አዲስ መሐመድ “ኃላፊነት የማይሰማቸው መርማሪዎች፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ዐቃቤ ሕጎች፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ዳኞች ሲሆኑ፤ የተጓደለ ፍትሕ እንዲሰጥ ዕድል ይፈጥራል” ይላሉ። “ሴቷ የደረሰባት አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንዳለ ሆኖ ተጨማሪ ጉዳት የሚያስከትል ጥያቄ የሚጠይቁ ዳኞችም እኮ አሉ” የሚሉት ጠበቃ አዲስ፤ ፆታዊ ጥቃቶችን የሚመለከት “ልዩ ችሎት መቋቋም አለበት” ሲሉም አክለዋል። እስኪ ታሪካዊ ዳራውን በወፍ በረር እንቃኝ።

በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ይቁም የሚለው ዘመቻ መነሻ የተፈጸመው እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 6 ቀን 1989 በአገረ ካናዳ በሞንትሪያል ኩቤክ ከተማ በኢኮል ፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ በተፈጸመ ግድያ ነው። ማርክ ሊፓይን የተባለ የ25 ዓመት ወጣት በዕለቱ 11 ሰዓት አካባቢ የሞንቲሪያል ዩኒቨርሲቲ አካል ወደሆነው የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ይገባል። ኮሌጁን በሚገባ የሚያውቀው ሊፓይን ወደ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ያመራል፡፡

50 ተማሪዎች ካሉበት በሁለተኛው ፎቅ ከሚገኘው አንዱ ክፍል ይገባና ሁሉም እንዲያዳምጡት ይጠይቃቸዋል። ተማሪዎቹም ንግግሩ የቀልድ መስሏቸው ቸል ሲሉት በቦርሳው የያዛትን ሽጉጥ በማውጣት ወደ ጣራው ይተኩሳል። በዚህ ጊዜ ሁሉም ተደናግጠው ለመሸሽ ሲሞክሩ ከተማሪዎቹ ውስጥ ወንዶቹና ሴቶቹ ተለይተው እንዲቆሙ ትዕዛዝ ይሰጣል። ከ50 ተማሪዎች ውስጥ ሴቶች ባንድ ጥግ ቀሪዎቹ ወንዶች ደግሞ በሌላው ጥግ ይቆማሉ። ሊፓይን ወንዶቹ ከክፍሉ እንዲወጡ ካዘዘ በኋላ ‹‹እዚህ ክፍል ለምን ሽጉጥ ይዤ እንደመጣሁ የሚነግረኝ አለ?›› በሚል ይጠይቃቸዋል። ከሴቶቹ ተማሪዎች አንዷ ‹‹አናውቅም›› ስትል መልስ ትሰጣለች። እሱም ‹‹I am fight­ing feminism›› ሴቶች የወንዶቹን ያህል መብት ይኑራቸው የሚለውን ሃሳብ ለመታገል ነው፤›› ሲል ያምባርቅባቸዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ከተማሪዎቹ አንዷ ‹‹ተመልከተን! እኛ የምሕንድስና ተማሪዎች ነን። መደበኛ ሕይወት ለመኖር የምናስብ እንጂ ሴቶች ከወንዶች የተለየ መብት ያግኙ ብለን ለመጮህ የተዘጋጀን ፌሚኒስት አይደለንም፤›› በማለት በማስተዛዘን ትመልስለታለች። ማርክ ሊፓይንም ‹‹እናንተ ሁላችሁም ሴቶች ናችሁ። ነገ መሐንዲስ ትሆናላችሁ። በወንዶችም ላይ ጣታችሁን ትቀስራላችሁ። እኔ ፌሚኒስትን እጠላለሁ፤›› በማለት ከግራ ወደ ቀኝ በመደዳው ተማሪዎች ላይ ይተኩሳል። ስድስቱን ይገድላል፤ ሦስቱን ያቆስላል። ከዚያም በኮሪደሩ ላይ፣ ወደ ሌላ ክፍል፣ አንደኛ ፎቅ ወደሚገኘው የኮሌጅ ካፍቴሪያ፣ ወደ ሦስተኛ ፎቅ እየተዘዋወረና እየተኮሰ ሰውን መጉዳት ተያያዘው። ከ20 ደቂቃ የተኩስ ቆይታ በኋላ ሊፓይን ጭንቅላቱ ላይ ተኩሶ ራሱን አጠፋ፡፡

በዚህች አጭር ደቂቃ 14 ሴቶችን (12 የምሕንድስና ተማሪዎችን፣ አንድ የነርሲንግ ተማሪና አንድ የዩኒቨርሲቲውን ሴት ሠራተኛ) ገደለ። አራት ወንዶችን ጨምሮ ሌሎች አሥራ አራት ሰዎችን አቆሰለ። በወቅቱ ለሪፖርተሮች ስለጭፍጨፋው መግለጫ ይሰጥ የነበረው የሞንትሪያል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ሕንፃው ውስጥ እንደገባ የራሱ ልጅ ተገድላ ማየቱ ተዘግቧል። የኩቤክ እና ሞንትሪያል መንግሥታት የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ያወጁ ሲሆን፤ በአንድ ክፍል ውስጥ የተገደሉት ዘጠኝ ተማሪዎች በኅብረት እንዲቀበሩ ተደርገዋል። ፈረንጆች እንደሚሉት የተቀረው ታሪክ ነው። ከዚህ አሳዛኝ ክስተት በኋላ ነው የጸረ ጾታዊ ጥቃት ቀን መከበር የጀመረው።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2017 ዓ.ም

Recommended For You