አባትና ልጅ…
የአባትና ልጅ ፍቅር ይለያል። እሳቸው ልጃቸውን ከዓይናቸው ሊያጧት አይሹም። ጠዋት ማታ በስስት እያዩ ይናፍቋታል። ትንሽዋ ልጅም እንዲያው ናት። የአባቷ ነገር አይሆንላትም። ወጥተው እስኪገቡ፣ ተኝተው እስኪነሱ ዓይኖቿ ይንከራተታሉ። አባት ከልጆቻቸው ነጥለው በተለየ ፍቅር ለሚያይዋት ልጅ ሃሳባቸው ብዙ ነው። ቁምነገር እንድትደርስ ከሁሉም እንድትበልጥ ይመኛሉ።
ከጊዜያት በኋላ አጋጣሚዎቹ ከፉ። ተወዳጁ አባወራ በድነገት ታመው ከአልጋ ዋሉ። ይህ ጊዜ ለቤተሰቡ አስደንጋጭ ሆነ። አባት የትንሽ ልጃቸው ጉዳይ ያስጨንቅ ያሳስባቸው ያዘ። ህመማቸው ሲበረታ፣ አቅማቸው ሲደክም ግን ቄስ መነኩሴ ጠሩ። ዋና ጉዳያቸው ልጃቸው ነበረች። ስለእሷ ለሰዎቹ መናገር ማሳሰብ አለባቸው። አባት ስለልጃቸው የውስጣቸውን እውነትና ስጋት ተናግረው የልባቸውን ተነፈሱ።
በእሳቸው ዙሪያ ከከበቡት ሽማግሌዎች በተለይ የንስሀ አባት አደራውን ተቀበሉ። እሳቸው ሕይወታቸው ቢያልፍ ፣ ልጅቷን ከሀገር ቤት ለያወጡ፣ ከተሻለ ቦታ ሊያኖሩ፣ አስተምረው ወግ ማዕረግ ሊያደርሱ ቃል ገቡ።
አባት ይህን የማለታቸው ምክንያት ስለእሷ ቁምነገር ብቻ አይደለም። ከእሳቸው ሞት በኋላ ተወዳጇ ልጅ መቃብራቸውን እያየች እንድታዝን፣ እንድታለቅስ አልፈለጉም። ልጅቷ ካገር ከቀዬው ብትርቅ የአባቷን መቃብር አታይም። ዘወትር እያስታወሰች አታለቅስም፣ አታዝንም። በልጅነቷ ለባል ታጭታለችና በትዳር አትታሰርም። ሰዎቹ ቃላቸውን ሰምተው አደራውን ተቀበሉ።
የአባት አደራ…
ከቀናት በአንዱ የተፈራው ሆነ። ታመው የከረሙት አባት ላይመለሱ አሸለቡ ። ይህ ጊዜ አባቷን እጅግ ለምትወደው እምሻው ብርቄ ፈተና ሆነ። ዳግም እንደማይገናኙ ሲገባት ልቧ በኀዘን ተሰበረ። እምሻው ገና ስምንት ዓመቷ ነው። የሚወዷት አባቷን ፍቅር ሳትጠግብ ኀዘንተኛ ሆናለች። ለቅሶው አልፎ አርባው እንደወጣ የንስሀ አባት ቃላቸውን ሊያከብሩ ወደቤት ዘለቁ። የሙት አደራ ነውና ልጅቷ ለተሻለ ሕይወት ከተማ መኖርና መማር አለባት። ዕቅዱ እንደታሰበው ሆነ። ሸዋ ሮቢት ተወልዳ ያደገችው ልጅ ቀዬ መንደሯን ትታ ካገሯ ራቀች። ጠዋት ማታ አሻግራ የምታየውን የአባቷን መቃብር ተሰናበተች።
አዲስአበባ ዘመድ ቤት የተላከችው እምሻው በእንግድነት ጥቂት ቀናትን አሳለፈች። ቆይታዋ በምቾት አልዘለቀም። ልጅነት ከናፍቆት ተዳምሮ ሆደ አስባሳት። ጠዋት ማታ በለቅሶ ውላ አደረች። ሁኔታዋ ያልጣማቸው ዘመዶቿ ከእነሱ እንድትቆይ አልፈቀዱም። ከቀናት በኋላ ለሌላዋ አክስት ተላልፋ ተሰጠች።
እምሻው በወግ በሥርዓት ያደገች የገበሬ ልጅ ነች ። ቁጣና ተግሳጽ ይገባታል። ሃላፊነትን አሳምራ ታውቃለችና ለነገሮች አትደፍርም ። ይህ ባህርይዋ ከአክስቷ ቤት ልጆች ጠባይ ጋር አልተስማማም። አዲስ አበባ ያመጧት መነኩሴ ከነበረችበት አውጥተው ከሌላ ባዕድ ቤት አስገቧት። ሰዎቹ መልካም ቤተሰብ ሆኑላት። የአባቷ ትዝታና የቤተሰብ ናፍቆት ግን ሊያከርማት አልቻለም። ውሎ አዳሯ በለቅሶና ትካዜ ተሞላ።
እምሻው አሁንም ሌላ አማራጭ ከፊቷ አለ ። ራሷን ችላ እንድትኖር ከሰው ቤት በሠራተኝነት መቀጠር አለባት ተባለ። ሃሳቡን አልጠላችውም። በይሁንታ ተስማማች። ከነበረችበት ቤት ልብሷን ይዛ ስትወጣ ወዴት እንደምትሄድ አታውቅም።
የስድስት ብር ደሞዝተኛ…
የዘጠኝ ዓመቷ ህጻን ዞር ዞር ያለችበት የዘመድ ቤት ለኑሮ አልተመቻትም። ወጣ ገባ ባለችበት ሁሉ ልጅነቷ ፈትኗታል። ኀዘንና ናፍቆት ከብቸኝነት ተዳምሮ አሰቃይቷታል። አሁን ደግሞ በስድስት ብር ደሞዝ ከሰው ቤት ልትቀጠር፣ ልትሠራ ነው። እምሻው ገና እግሯ እንደረገጠ ስለገባችበት ቤት አስደንጋጭ ዜና ተነገራት።
በዚህ ቤት ሠራተኛ ይሉት አይበረክትም። አሰሪዎቹ ክፉና ሃይለኛ ናቸው። በየጊዜው ብዙ ሰው ይሰናበታል። በወቅቱ እሷ በቤቱ ስትቀጠር በአንድ ወር ውስጥ ሰላሳ አራተኛዋ ሠራተኛ ሆና ነበር። ይህ እውነት ለትንሽዋ እንጀራ ፈላጊ ከባድና አስድንጋጭ ሆነ።
የሌሎች ትከሻ ያልቻለውን ጫና እሷ እንደማትሸከመው ሲገባት አብዝታ ተጨነቀች። የገባችበት ቤት የሚመራው በትልቋ እማማ ነው። እሳቸው ለቤተሰቡ አያት ናቸው። ለዓመታት ራስና ቁንጮ ሆነው ቤቱን መርተዋል። ጨርሶ ዋዛ ፈዛዛ አይወዱም ቁጡነታቸው በሁሉ ዘንድ አስፈርቶ አስከብሯቸዋል።
ትልቋ እማማን በፍቅር…
እምሻው ተቀጥራ የገባችው በሃይለኛዋ ሴት ስር ለማደር ነው። ስለ እሳቸው ከሰማችበት ጊዜ አንስቶ ፍርሃትና ጭንቀት ይዟታል።በየቀኑ ሠራተኞች ይባረራሉ መባሉ ያሳስባታል። አንድ ነገር ግን አልረሳችም። ጠዋት ማታ አብዝታ ትጸልያለች። እሷ የሁልጊዜ ምኞቷ ከሁሉም ጋር ተስማምቶ መኖር ነው። በሰፊው ቤተሰብ መሀል ቀናት በሰላም እየነጉ መሹ። ሳምንታት አልፈው ወራት ተቆጠሩ። እምሻው በአሠሪዋ ዓይኖች በክፉ አልታየችም፣ ‹‹ውጭ›› ተብላ አልተባረረችም። ከትልቋ እማማ አልተጣላችም።
ገጠር ሳለች ጀማምራው የነበረው ትምህርት አልቀጠለም። ሰዎቹ ሰው እንዲያገኛት አይሹምና ዕድል አልሰጧትም። እንዲያም ሆኖ ስለእሷ ፍቅራቸው ይለያል። የቤቱ እህትማማቾች ዝምድናዋን ቢሹ የጡት ልጃቸው አድርገዋታል። ሁሉን እንደ ዓመሉ ይዛ በጥበብ የምታድረው ታዳጊ ከሁሉም እጅ ስጦታዎች ይጎርፍላታል።
ባለሙያዋ፣ ቀልጠፋዋ፣ታማኝዋ እምሻው የያዘችውን አትጥልም። ያየችውን አትንቅም። ሁሌም የልጅነት ጉልበቷ ለሥራ ይታዘዛል። እምሻው በፍቅር ለሁሉም አድራ ፣ ጊዜያትን ቆጠረች። አንዳንዴ እማማ ቆጣ ብለው በተበሳጩ ጊዜ ሰበብ ፈልገው ይመቷታል። አታኮርፍም፣ አምርራ አታለቅስም። ሳትቀየም በፍቅር ትደልላቸዋለች። ስለእሷ ሁሉን ረስተው ይሸነፋሉ። በትናንሽ ስጦታዎቿ ደስ ይላቸዋል። እየሳቁ ያመሰግኗታል።
እማማን ልጅቷ ሁሌም ‹‹አባዬ፣ አባይዬ ›› ብላ ትጠራቸዋለች። ደስ ይላቸዋል። በየቀኑ ለሌላው ያላሳዩትን ፈገግታ እየቆጠቡ ይመግቧታል። እምሻው እስከዛሬ በቤተሰቡ ያልነበረውን ፍቅርና ሰላም ሸልማ ለቤቱ እፎይታን አላበሰች። ጠፍቶና ተሰዶ የኖረው ፍቅር በመሃላቸው ነግሶ ዓመታትን አወጀ። እንደ ቀልድ አንድ ሁለት ያለው ጊዜ አስራሰባት ዓመታትን ቆጠረ።
አፍላነት…
አሁን እምሻው ልጅነቷን ተሻግራ ከወጣትነቷ ደርሳለች። ካደገችበት ጊቢ አልፎ በልጆቹ ቤት ሳይቀር ዋጋ የከፈለችበትን ኑሮ ልትሰናበት እያሰበች ነው። እስከመቼ የሚለው ጥያቄ በውስጠዋ ውሎ ካደረ ሰንብቷል። ከሰው ቤት ሥጋ የራሷን ባዶ ሽሮ አብዝታ ፈለገችው። የማታ መማር ከጀመረች ወዲህ ከብዙዎች ተዋውቃለች። ለባብሳ ሰትወጣ ያምርባታል። አድናቂ ተከታዮቿ በዝተዋል።
ወጣትነት ብዙ ያስቡበታል፣ ያቅዱበታል። የእሷም ስሜት ከዚህ አልዘለለም። አሁን ከአስራሰባት ዓመት በኋላ አንዲት ቀንን መጨመር አትሻም። ስለኑሮና ሕይወቷ ማሰብ መወሰን ይኖርባታል። እናም በቁርጠኝነት አደረገችው። ዓመታትን በመልከ ብዙ ገጽታዎች ያለፈችበትን ፈታኝ ሕይወት ርግፍ አድርጋ ለአዲስ ምዕራፍ ተዘጋጀች።
እምሻው ልጅነቷን ከከፈለችበት ቤት ጠፍታ በወጣች ጊዜ አስራ ስምንት ሻንጣ ልብስ በእጇ ነበር። ይህ ሁሉ ግን ነገን አሻግራ ለምታልመው ወጣት ምኗም አልሆነም። ለእሷ ነገዋ ፍጹም ይለያል። ራሷን ማሻሻል፣ ሆቴል መክፈት፣ ድርጀት ማቋቋም ዓላማዋ ነው።
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሆቴል
ወጣቷ ዓላማዋን የምታሳካው በብድርና፣ በሌሎች እገዛ አይደለም። በራሷ ላብና ወዝ፣ በጉልበቷ ድካም እንጂ። ወደፊት ለምትከፍተው ሆቴል ‹‹እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ›› ስትል ስም አውጥታለች። እምሻው ከሃሳቧ አልተናጠበችም። ከመንገዷ አልተመለሰችም። ከነበረችበት ወጥታ አምስት ዓመታትን በሌላ ሥራ አሳለፈች። የሆቴል መስተንግዶ ሙያን ቀሰመች። ይህ ሙያ ወደፊት ልትከፍተው ላሰበችው የራሷ ሆቴል ያግዛታል። ከዛ በፊት ግን ሌላ ዕቅድ አላት። አንድ ቀን በብዙ ውጣውረድ የጀመረችው የውጭ ጉዞ ተሳካ። የሚያውቋት ሁሉ ስለመልካምነቷ ፍቅራቸውን ከፈሏት። በብዙ አጀብና ምስጋና ተሸኝታ ወደ አረብ አገር አቀናች።
ሕይወት በሊባኖስ…
እነሆ! የእምሻው ፈታኝ የሕይወት ዓመታት እንደዋዛ ታለፉ። ዛሬን ደግሞ በአረቦቹ መሀል በሊባኖስ ምድር ተገኝታለች። በቆመችበት ሥፍራ ምን እንደሚገጥማት አታውቅም። አሁንም የልጅነት ጸሎቷ ከእሷ ጋር ነው። ፈጣሪዋን ‹‹እርዳኝ›› ስትል ትማጸናለች። ጸሎቷ መሬት አልወደቀም። አሰሪዎቿ እንደ እናት አባት ሆኗት። እንደ ልጅ ያሻትን አገኘች። የወደደችውን ፈጸመች። የቤቱ አባወራ የህክምና ዶክተር ናቸው። ወይዘሮዋ ደግሞ ዝነኛ የብር ጌጣጌጥ ነጋዴ። ሁለቱም እምሻውን ወደው የተቀበሏት ከልባቸው ነበር። ከቤታቸው ሥራ ውጭ ለትርፍ ገቢዋ ያግዟታል። በቅን እየታዘዘች ገንዘቧን ታገኛለች።
እምሻው በአረብ ሀገር ስምንት ዓመታትን ስትቆይ ኑሮ አልጎረበጣትም። አእምሮዋ ግን ዕረፍት አልባ ሆኗል። በባእዳን ምድር የምታየውን ጸጋ ለራሷ ሀገር ትመኘው ይዛለች፤ ዛሬም እስከመቼ? ይሉት ጥያቄ በውስጧ ውሎ አድራል። ልቧ ወደሀገር ቤት ኮበለለ። ባገሯ ምድር የምትከፍተው ሆቴል፣ የምትገነባው ቤት፣ የምትሞላው ጎዶሎ ወለል ብሎ ታያት።
አሰሪዋ ወይዘሮ ከእሷ በላይ ያስባሉ። ሀገሯ ሄዳ ባል እንድታገባ ልጅ እንድትወልድ እየመከሯት ነው። ወደፊት ባለቤቷን ሊቀበሉ፣ የምትወልደውን ልጇን ሊያሳድጉ ቃል ገብተዋል። እምሻው ሀገር ቤት እጮኛ አላት። ቃላቸውን አልናቀችም። የሚሏትን ሁሉ ተቀበለች። ለጉዞ ስትዘጋጅ ለወደፊት ልጇ የሚያስፈልጓትን ልብሶች፣ መጫዎቻዎች፣ ጡጦዎችና ሌሎችንም ያዘች። ለምትከፍተው የ‹‹እንደግዚአብሄር ፈቃድ›› ሆቴልም የሚፈለጉ ዕቃዎችን ሸከፈች።
አዲስአበባን በአዲስ ሕይወት
እምሻው ሀገር ቤት ተመልሳ አዲስ አበባ ደርሳለች። ዕቅድ ሃሳቧ እንደምኞቷ ሆኗል። ከእጮኛዋ ጋር ትዳር መስርታ ጎጆ ቀልሳለች። ኑሮ በአዲስ መልክ በደስታ መቀጠሉን ይዟል። ነፍሰጡር መሆኗ ደግሞ ሕይወቷን ሙሉ አደርጎታል። ለልጇ የያዘችውን ስጦታ የምታበረክትበት ጊዜ እየቀረበ ነው።
ሲኖትራኩ …
ከቀናት በአንዱ ነፍሰጡሯ ወይዘሮ ከቤት ርቃ ከታናሽ ወንድሟ ጋር ጉዞ ጀመረች። ምክንያታቸው ዕቃ መግዛትና ወላጅ እናታቸውን ማየት ነበር። ከተባለው አካባቢ ሲደርሱ አንድ ድንጋይ የጫነ ሲኖትራክ ከታክሲ ጋር ሲሽቀዳደም አስተዋሉ። ሲኖው በሚያስደነግጥ ፍጥነት አጠገባቸው ደርሶ ነበር። እህትና ወንድም ማምለጥ፣ መሸሽ አልቻሉም። ሁለቱንም ገጭቶ ከአስፓልት ላይ ዘረራቸው።
እንዲህ በሆነ ደቂቃዎች በኋላ ታናሽ ወንድሟ ሕይወቱ ማለፉ ታወቀ። የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። ለቀናት ራሷን ሳታውቅ ከሆስፒታል የተኛችው እምሻው ዓይኖቿን መግለጥ እንደጀመረች ፅንሱ መጨናገፉ ተነገራት። ክፉኛ የተጎዳው አካሏ እግሮቿን ይዞ ሞራሏን አድቅቆት ነበር። ውስጧ ጨለመባት። አምርራ አዘነች። የዛች ጎዶሎ ቀን ክፉ አደጋ ከያዘችው ዕቅድ፣ ካለመችው፣ ህልም ከወጠነችው ብሩህ ተስፋ አለያያት።
አሁን ሆቴል፣ ድርጅትና ቤት ይሏቸው ተስፋዎች የሉም። ነገን ልጅና ባሏን ይዛ ወደ ሊባኖሰ አትጓዝም። የነበረው እንዳልነበረ ሆኗል። ከሆስፒታል በኋላ ድፍን አንድ ዓመት ከአልጋ ሳትነሳ ከቤት ዋለች። ስቃይ፤ ህመም ተመላለሱባት። ውሎ አድሮ የባልና ሚስት አቅም ተሟጠጠ፣ ጓዳቸው ጎደለ። ምርጫ አልነበረም። ባለቤቷ ከኪሱ ያለውን ጥቂት ሳንቲም ለእጇ ትቶ ለሥራ ከአዲስ አበባ ራቀ። እምሻው ሆድ ባሳት። አምርራ አዘነች።
አንዳንዴ ቁጭ ስትል ያመጣችውን ዘመናይ ልብስና ጫማ ታስበዋለች። ሀገሯ ስትገባ ልትዋብ፣ ልትዘንጥበት ነበር። አሁን እንዲህ ይሉት ታሪክ የለም። እግሯ ክፉኛ ተጎድቷል። ቁመናዋ ተበላሽቷል። የትናንቷ ፈጣን ሯጭ ዛሬ ከሰው እጅ ወድቃለች። አራት ዓመታትን በክራንች ታግዛ ተጓዘች። ሕይወት እንደትናት ባይሆንም እንደነገሩ ቀጠለ።
እምሻው ጥቂት ሻል ሲላት ከራሷ ጋር ተወያይታ ተስማማች። ወድቆ መቅረት ዓላማዋ አለመሆኑ ሲገባት በህመሟ ጊዜ የጠጣችውን የአጥሚት እህል ጥቂት ሚጥሚጣና ቅመሞች አክላ በሻንጣ ይዛ መዞር ጀመረች። በአንድ እጇ ክራንች በጀርባዋ ደግሞ የምትሸጠውን ያዩ ብርታቷን አደነቁ።
‹‹ይጠቅማችኋል ግዙኝ›› ያለቻቸው ሁሉ ደንበኞቿ ለመሆን አልዘገዩም። በሯ ላይ የምትሠራውን ባልትና ለጥፋ ራሷን ማስተዋወቅ ያዘች። ሙያዋን የቀመሱ ሁሉ በደጇ ተመላለሱ። ታሪኳን የሰሙ፣ ጥረቷን ያደነቁ አንድ ሥፍራን ጠቆሟት። ቀበሌ ነበር። ቦታው ደርሳ እውነታውን አስረዳች።
ከብዙ ትግል በኋላ ዓይኖች ሁሉ ወደእርሰዋ ተመለከቱ ። ጆሮዎችም አደመጧት። ውሎ አድሮ ብድር ወስዳ ቤቷ ላይ እንድትሠራ ተፈቀደላት። ‹‹እምሻው ባልትና›› በሚል ስያሜ ሙያዋን ማስመሰከር ጀመረች። እያደር ዝናዋ ተሰማ፣ ዕውቅናዋ ናኘ። ደንበኞቿ በረከቱ። ዕንቁላል ቀቅላ መሰኮቷ ላይ አኖረች። የሚጠይቁ በዙ። ጠጅ መጣል ጀመረች። በእጅጉ ተወደደላት። ከዓመታት በኋላ ባዛር የመውጣት ዕድል ስታገኝ ለቅመሙ አሮጊት ጎረቤቶቿን ሰበሰበች። እግሯን በትራስ አስደግፋ በመጅና ወፍጮ ያሻትን አዘጋጀች። አንድ በርሚል አዋዜና ቅመሞቹን ይዛ በወጣች ጊዜ ገበያዋ ደራ። ጊዜው ሳያበቃ በሁለት ቀን የእጇን ሸጣ ጨረሰች።
እምሻው ብርታቷ ቀጠለ። በሥራው ታዋቂ ሆነች። እያሰፋች፣ ደንበኞች ማበርከቷ ከእውቅና ጥግ አደረሳት። ዛሬ ከ68 አይነት በላይ ቅመሞች ታዘጋጃለች አብዛኞቹ የራስዋ ፈጠራና ግኝቶች ናቸው። ይህ እውነታ ከ30 በላይ ሰርተፊኬት እንድታገኝ አድርጓታል። የዓመቷ ምርጥ ሞዴል ተብላም ተሸልማለች። እናት አባቴ የምትላቸው የውጭ ሀገር አሠሪዎቿ በችግሯ ጊዜ አልራቋትም። ሀኪሙ አባቷ ዛሬ በሕይወት ባይኖሩም በሙያቸው ሊያግዟት ሞክረዋል።
እንደገና…
እምሻው ከስደት ከተመለሰች አስራስድስት ዓመታት ቆጥራለች። በዓመታቱ መሀል ብዙ አግኝታ ብዙ አጥታለች ወድቃ ተነስታለች። አልቅሳ ስቃለች። ይህ ብቻ አይደለም። ከሞት መትረፍ በኋላ ወልዳ የታቀፈቻት ልጅ ዛሬ አስራሶስት ዓመቷ ነው። ‹‹የአብስራ›› ስትል ሰይማታለች። የምታሳድጋት የሟች እህቷ ል ጅም እህ ቷ ሆናታለች።
ታማኙ የክፉ ቀን ባሏ ዛሬ ከጎኗ አልራቀም። በራሳቸው መኪና የግል ሥራውን ጀምሯል። እሷ በሕይወት ውጣውረድ ብዙ ተፈትናለች። ያለፈው ትናንት ለዛሬ ሕይወቷ መልካም ሆኖ ስለነገው አሻግሮ እያሳየት ነው። እምሻው ወርቄ ብርቱዋን ወይዘሮ ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም