የጥንካሬ ተምሳሌቶቹ የመሃንዲሱ እጆች

‹‹አቋራጭ መንገድ ሰውን ያጠፋል እንጂ ካሰበበት አያደርስም›› የሚል መርህ አላቸው። ሁሉም ሰው ከራዕዩ ለመድረስ በሕይወት ዘመኑ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ፊት ለፊት መጋፈጥ አለበት ብለውም ያምናሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው አንድ ሰው ፈተናዎችን የመጋፈጥ አቅሙን ማጎልበት በቻለ ቁጥር ካሰበበት የማይደርስበት መንገድ አይኖርም የሚል ነው። ከችግር መውጣት የሚቻልበትን መንገድ መቀየስ እንጂ መሸሽ አማራጭ ሆኖ አያውቅም ባይም ናቸው፤ የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችን ኢንጂነር ሳሙኤል ሳህለማርያም።

ኢንጂነር ሳሙኤል የሳምኮን ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን እና ፓራጎን ሪልስቴት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ከተቀጣሪነት እስከ የግል ድርጅት ማቋቋም ለከተሞች ድምቀት የሆኑ ውብ ህንፃዎችን በመገንባት ከሚታወቁ መሐንዶሶች አንዱ ናቸው። በዚህ ሥራቸው ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል።

ከ25 ዓመታት በላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ላይ በሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ለዘርፉ እድገት አወንታዊ ሚና እንደተጫወቱም ሥራዎቻቸው ይመሰክራሉ። እንግዳችን በሀገር ግንባታ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ እንዲሁም ከበርካታ የመንግሥት ኃላፊዎች እና ድርጅቶች የእውቅና ሰርተፍኬት አግኝተዋል።

የተወለዱቱም ሆነ ያደጉት በአዲስ አበባ በተለምዶ ሰፈረ ሰላም በሚባለው አካባቢ ነው። የሂሳብ ባለሙያ ከሆኑት አባታቸው እግር ሥር እየተከተሉ በማደጋቸው ‹‹ልክ እንደ አባቴ አካውንታት እሆናለሁ፤ አልያም ደግሞ ዶክተር መሆኔ አይቀርም›› የሚል የልጅነት ህልም እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።

ይህ ህልማቸው ግን አብሯቸው አልዘለቀም፤ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ በአካባቢያቸው ዘወትር የሚያገኟቸውን የህንፃ ኮሌጅ ተማሪዎች ሲመለከቱ በአጠቃላይ ሁኔታቸው ተማረኩ። በምህንድስና ዘርፍም ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል በመረዳታቸውና በመሬት ላይ በሚያዩት ውጤት በመሳባቸው ሙያውን ለመቀላቀል አሰቡ፤ አስበው ብቻ ግን አልቀሩም፤ ይልቁንም ውጥናቸውን እውን ለማድረግም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያገኙትን ውጤት ይዘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲውን የህንፃ ኮሌጅ ተቀላቀሉ።

ከህንፃ ኮሌጁ አድቫንስድ ዲፕሎማቸውን በህንፃ ምህንድስና ይዘው እንደወጡም በአንድ የግል ተቋራጭ ድርጅት በሳይት መሃንዲስነት ተቀጥረው ለአንድ ዓመት ያህል አገለገሉ። ጎን ለጎንም በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከዚያው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በዘርፉ ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ የራሳቸውን ድርጅት ከፍተው ቢሰሩ የበለጠ የተሻለ እንደሆነ አምነው ሥራቸውን ለቀቁ።

ኢንጂነር ሳሙኤል የራሳቸውን ድርጅት ለመክፈት ስላነሳሳቸው ምክንያት ሲያስረዱም፤ ‹‹የራሴን ኩባንያ ለማቋቋም ዋና የነበሩት ምክንያቶች በርካታ ናቸው፤ በተለይ ግን በወቅቱ በዘርፉ የሥራ እድል ያለመኖሩ አንዱ ነው››፤ የሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ገና እያደገ የሚገኝ መሆኑ ሌላው ምክንያታቸው ስለመሆኑም ይገልጻሉ፤ እነዚህ ሁለት ችግሮች በማየት ይህንን ክፍተት ለመሙላት በማለም ወደ ሥራው መግባታቸውን ይናገራሉ።

ኢንጂነር ሳሙኤል ይህንን ያስቡ እንጂ፣ መጀመሪያ ላይ ወላጆቻቸውን ጨምሮ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ሃሳባቸውን ቶሎ ለመቀበል በመቸገራቸው ‹‹ተው ይቅርብህ›› የሚል ምክር አዘል ማስጠንቀቂያ እንደሰጧቸው ያስታውሳሉ። የቤተሰባቸው ትልቁ ስጋት ደግሞ ወጣቱ ኢንጂነር ሳሙኤል ከአዲስ አበባ ወጥተው የማያውቁ በመሆናቸው የሥራው ባህሪ ደግሞ ርቀው ለመሄድ የሚያስገድድ መሆኑ እንደነበርም ያነሳሉ። ‹‹በተለይም ቤተሰቦቼ የርቆ መሄዱ ጉዳይ እምብዛም ስላላስደሰታቸው እና በግል መሥራት የተለመደ ባለመሆኑ ሃሳቤን ቶሎ ለመቀበል ተቸግረው ነበር። በወቅቱ ልጅ ስለነበርኩ የራሴን ኩባንያ ከፍቼ ገንዘብ ማንቀሳቀስ የምችል አርገው አላመኑም ነበር›› ሲሉም ይገልጻሉ።

ቤተሰቦቻቸው የኢንጂነር ሳሙኤልን በሥራ የመለወጥ ቆራጥ አቋም እና ትጋት በመመልከታቸው የበለጠ እንዲጠነክሩ ይደግፏቸው ጀመር። በተለይ የአጎታቸው ድጋፍ አሁን ላሉበት ደረጃ ለመድረሳቸው ወሳኝ ሚና እንደተጫወተላቸው ይገልፃሉ። ወንድማቸውም የኢንጂነር ሳሙኤልን ፅኑ ፍላጎት ከተረዱ በኋላ የሚሠሩበት ቦታ ድረስ በመሄድ ያበረታቷቸው እንደነበርም ይናገራሉ።

ከሁሉም በላይ ግን በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማግኘት ትልቅ ችግር የነበረ በመሆኑ ዘርፉን በቀላሉ መቀላቀል መቻላቸውን ያስረዳሉ። በወቅቱ ደግሞ ፍቃድ ለማውጣት የቤተሰብ መኪና ብቻ በቂ በመሆኑ ነገሮችን ሁሉ ቀላል አደረገልኝ ሲሉ የጀመሩበትን ሁኔታ ያስታውሳሉ። ያጠራቀሟትን 50 ሺ ብር እንደ መነሻ እርሾ በመጠቀም እና አስር ሠራተኞችን ቀጥረው ማሠራት ጀመሩ።

አብዛኛውን ሥራ ግን ራሳቸው ቀን ተሌት ሳይሉ ይሠሩ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ‹‹ጊዜው ጥሩ ስለነበር ልፋቴ በከንቱ አልቀረም፤ ውጤቱን ለማየትም ብዙ አልቆየሁም፤ በወቅቱ እንደ እኛ ጀማሪ ለሆኑ ሰዎች ግብዓት አቅራቢ ድርጅቶች በዱቤ የተለያዩ እቃዎችን ይሰጡን ስለነበር ራሴን ችዬ ለመቆም ብዙ አልተንገዳገድኩም›› ሲሉ የነበሩትን መልካም አጋጣሚዎችም ያስረዳሉ።

ሁሉም ሰው ጠንክሮ ከሠራ የልፋቱን ፍሬ ማየቱ አይቀሬ እንደሆነ በፅኑ የሚያምኑት ኢንጂነር ሳሙኤል፤ ሥራን ሳይመርጡ በመሥራታቸው፤ ደንበኞቻቸውን ትንሽ ትልቅ ሳይሉ በታማኝነት በማገልገላቸው ሥራቸው እየሰፋ፤ የድርጅታቸው አቅም እየጎለበተ መምጣቱን ይናገራሉ። በዚህም የግንባታ ሥራ ከሚያከናውነው ሳምኮን ኢንጂነሪግ ባሻገር ፓራጎን ተሰኘ ተጨማሪ ድርጅት መክፈት ችለዋል። ይህም ድርጅታቸው የሪል ስቴት ግንባታ፤ ኪራይና ሽያጭ የሚያከናውን መሆኑን ይጠቁማሉ።

በአስር ሠራተኞች የተጀመረው ሳምኮን ኢንጂነሪንግ በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ የሚሆኑ ዜጎች በቋሚነት፤ ከ500 ለማያንሱ ሰዎች ደግሞ በጊዜያዊነት የሥራ እድል ተጠቃሚ ያደረገላቸው መሆኑም ነው ያመለከቱት።

ኢንጂነር ሳሙኤል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ የእጅ ጥበባቸው የታከለባቸውን በርካታ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች ህንፃዎችን ገንብተዋል። ከእነዚህም መካከል በቴፒ ዩኒቨርሲቲ የገነቧቸው በርካታ የመማሪያና መኖሪያ ብሎኮች ይገኙበታል፤ ቦረና ዩኒቨርሲቲ የገነቧቸው የመማሪያ ብሎኮችም ተጠቃሽ ናቸው፤ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤት ህንፃዎችን ገንብተዋል። ፍላሚንጎ አካባቢ የሚገኘውን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ህንፃ ዋነኞቹ መሆናቸውን ያመላክታሉ።

ድርጅታቸው ለኮንስትራክሽን ዘርፉም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ይናገራሉ። በተለይ ከኮንስትራክሽን ጋር በተያያዙ ሕጎች ፣ ደንቦች እና መመሪያዎች ዙሪያ ጥናቶችን በማካሄድ ብሎም በሰው ኃይል ስልጠና የበኩላቸውን ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

እንደ ኢንጂነር ሳሙኤል ገለፃ፤ ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት አርአያነት ያለው ተግባር ሲፈፅም ቆይቷል። ከእነዚህም መካከል ሚክሲኮ አካባቢ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ውስጥ የሠራው የመመገቢያ ብሎክ (ክፍል) ይጠቀሳል። ከዚህ ባሻገርም በየዓመቱ አቅመ-ደካማ ለሆኑ አረጋውያን ቤት በማደስ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፤ አሁንም እየገነባ ይገኛል።

‹‹መንግሥት በሚጠይቀን የድጋፍ መርሃ-ግብሮች ሁሉ እጃችንን በመዘርጋት የበኩላችንን አስተዋፅኦ እያበረከትን እንገኛለን›› ይላሉ። በተለይም የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ጊዜ በሚያሰናዳው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ሙያቸውን ከልብ ወደው በመሥራት የሚታወቁት እኚህ እንግዳችን ከግንባታ ሥራው ጎን ለጎን በዘርፉ ያላቸውን እውቀት ማሳደግ እንደሚገባ ያምናሉ። ይህንን አቋማቸውን እውን ለማድረግ ሲሉም እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በኢንተርናሽናል ቢዝነስ አድሚስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ወስደዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሌላኛውን የማስተርስ ዲግሪያቸውን በኮርፖሬት ፋይናንስ ለመያዝ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

‹‹እኔ እዚህ ልደርስ የቻልኩት በወጣትነቴ ትልቅ ህልም ስለነበረኝ ነው። ላለፉት 26 ዓመታት እኔም ሆንኩ መላው የድርጅታችን ሠራተኞች ግብ አስቀምጠን በመሥራታችን ነው ውጤት ማየት የቻልነው›› የሚሉት ኢንጂነር ሳሙኤል፤ አሁን ያለው ወጣት ግን ህልሙን ለማሳካት በትክክለኛው መንገድ ከመጓዝ ይልቅ አቋራጭ እየመረጠ መሆኑን ተናግረዋል፤ በዚህ የተነሳም ከህልሙ ሳይደርስ የሚጨናገፍበት ሁኔታ እንዳለ ይገልፃሉ።

‹‹አቋራጭ መንገድ ከራስ አልፎ ለሀገርም ጭምር ትልቅ ጥፋት ነው የሚያመጣው፤ ‘በአንድ ጀምበር ሮም አልተገነባችም’ እንደሚባለው ሁሉ ትክክለኛ እና የጠራ ህልም በመያዝ እዚያ የሚያደርሱን መንገዶች ሁሉ በፅናት ማለፍ ይጠበቅብናል›› ሲሉ ያስገነዝባሉ።

ኢንጂነር ሳሙኤል በአዲስ አበባ በመንግሥት እየተካሄደ ስላለው የኮሪደር ልማትም ገንቢ አስተያየት ሰጥተዋል። የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ስር ነቀል በሆነ መልኩ እንደሚለውጣት ጠቅሰው፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉም ከወደቀበት ተነስቶ ዳግም እንዲያሰራራ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፤ አቅም ያላቸው ተቋማት እንዲፈጠሩ ምክንያት እየሆነ ነው ብለዋል።

በዚህ የከተማ ማልማት ሥራ እሳቸውም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ መሳተፍ እንደሚፈልጉ ጠቅሰው፣ በተለይም የተፈጠረውን ምቹ እድል በመጠቀም ወደ ቤት ልማት ግንባታ ዘርፉ በስፋት የመግባት ራዕይ ሰንቀው እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

‹‹በከተማ ደረጃም ሆነ እንደ ሀገርም በከፍተኛ ደረጃ የመኖሪያ ቤት እጥረት አለ ፤ ይህንን እጥረት መፍታት በሚያስችል እና የቤት ልማትን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አዲስ አሠራር እየቀረፅን ነው›› የሚሉት ኢንጂነር ሳሙኤል፤ ድርጅታቸው ባካበተው ተሞክሮ በመጠቀም የቤት ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ጥናት እያካሄደ መሆኑን ያስረዳሉ።

ከእስካሁኑ ካለው የተለየና አብዛኛውን ህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የሚያደርግ ‘የቤት እቁብ’ ሥርዓት ይዘው በቅርቡ እንደሚመጡም ያመለክታሉ። ከአስር እስከ 15 ዓመት በክፍያ ሥርዓት ሰው በየወሩ እየቆጠበ ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ድረስ የቤት ባለቤት መሆን የሚችልበት ሶፍትዌር ተቀርጿል ይላሉ። ይህም አዲስ ሥርዓት የሀገሪቱን ቤት ሽያጭ ገበያ ያረጋጋዋል የሚል እምነት አላቸው።

በአሁኑ ወቅት የቤት ልማት መርሃ ግብሩ የአዋጭነት ጥናት የተሠራ ሲሆን፣ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ይሁንና ይህ ህልማቸው እንዲሳካ እንደ ሀገር እየተሰጠው ትኩረት ሊጠናከር እንደሚገባ ያምናሉ። ‹‹በተለይም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በደንብ ለማሳደግ በዘርፉ የሚስተዋለውን የግብዓት፤ የበጀት እጥረት መፍታት ያስፈልጋል›› ይላሉ። በተጨማሪም ዘርፉን ለማዘመን ውድድር ተኮር የሆነ የፕሮጀክት አመራር ሊኖር እንደሚገባም አስገንዘበዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የሪል ስቲት ኩባንያቸው እስካሁን ለ25 ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን፣ አዲስ የቤት ልማት ፕሮጀክታቸው እውን ሲሆን ደግሞ እስከ 400 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጠር ይታመናል።

በሌላ በኩል በሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ገና በማደግ ላይ ያለ ቢሆንም በዘርፉ ለመሰማራት ለሚሹ ወጣቶች ብዙ እድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል። በተለይም አዳዲስ የኪነ ህንፃ የፈጠራ ውጤቶች ለሚያመጡ የዘርፉ ተዋናዮች አቅማቸውን የሚያሳዩበት ነባራዊ ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳሉ። በመሆኑም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሠማሩ ወጣቶች የጥበብ እጃቸውን ውጤት በመጠቀም ለሀገር ግንባታ አወንታዊ አስተዋፅኦ ለማበርከት እንዲዘጋጁ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You