ዕለተ ቅዳሜ አዲስ አበባ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳው ላይ ነን። የነብር ቆዳ የለበሱ ሰዎች በርቀት ይታያሉ። የአጋዘን ቀንድ የያዘውም ድምጹን እያሰማ ባህላዊ ጭፈራውን ያስነካዋል። ወዲህ ዞር ሲሉ ደግሞ ነጭ ኮፍያቸውን ያጠለቁ ወይዛዝርት ከበሮ ይመታሉ። ከወዲያኛው የስታዲየሙ ክፍል ባለቢጫ ቀለም ካናቴራ የለበሱ የአዲስ አበባ የሰላም ተጓዦች የሆኑት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ይገኛሉ።
ወጣቶቹ በጭብጨባ የታጀበ የስፖርት ኅብረ ዝማሬዎቻቸውን ያሰማሉ። አለፍ ሲሉ ሱርማው፣ ጋሞው፣ ኦሮሞው፣ ጉራጌው፣ ትግሬው፣ አማራው፣ ጋምቤላው፣ ቤኒሻንጉሉ …በአጠቃላይ ኢትዮጵ ያውያን በአንድ ማዕድ፤ በአንድ ቦታ አዲስ አበባ ስታዲየም ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም 13ኛውን የብሔር፣ብሔረሰቦች በዓል እያከበሩ ነው።
የዳውሮ እና የኮንታ ሶስት እና አራት ሜትር የሚደርሱ የትንፋሽ ድምጽ መሳሪያዎችም ከሁሉም በላይ ከፍ ብለው ይታያሉ። ጦር እና ጋሻ ሰድረው የሚሸልሉና የሚፎክሩ የወላይታ ሰዎች፣ ክብ የሰሌን ኮፍያ እና አረንጓዴ ቁምጣቸውን የታጠቁ የአላባ ወጣቶች፤ ፊቱን በአፈር እና በተለያየ ቀለማት ያስጌጠው የሱርማ ወጣት ሁሉም አዲስ አበባ ላይ ናቸው። ምን ኢትዮጵያውያን ብቻ ጥቂትም ቢሆኑ የውጭ አገር ዜጎችም የበዓሉ ታዳሚ የመሆን ዕድል ነበራቸው። የውጭ ዜጎቹ የኢትዮጵያውያንን ባህል እና የስታዲየሙን ክንውን በአግራሞት ሲከታተሉ አልፎ አልፎም በጭብጨባ ማበረታቻቸውን ሲሰነዝሩ ውለዋል።
ሊሳ ዴለቬንዴር አከር ጀርመናዊት ናቸው። በበዓሉ ታዳሚ ሆነው ከደቡቡ ማኦው ጭፈራ እስከ ሰሜኑ ኢሮብ ድረስ ያለውን ባህላዊ አልባሳት አይተዋል። «ኢትዮጵያውያን ለዓለም የሚተርፍ ባህል እንዳላቸው ማሳየት ችላችኋል፤ ይህ የሚያኮራ ነው። ለዓይን የሚስብ እና ለጆሮ የሚመጥን የውብ ባህሎች ስብስብ መመልከት ተችሏል። ከዲዛይን ውበታቸው አንጻር የኪነጥበብ ፋይዳቸው የጎላ የተለያዩ አልባሳት ባለቤት የሆኑ ብሔረሰቦችን ያሉበትን በዓል መታደም እንደ አንደ የውጭ አገር ዜጋ ያስደስታል» ይላሉ።
በተመሳሳይ ባህላዊ ክንውኖች ላይ በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ መታደማቸውን የሚገልጹት ጀርመናዊቷ፤ አሁን በድጋሚ ሲሳተፉ ግን ባህላዊ ክንውኖቹ ልክ እንደ አዲስ እንደሳቧቸው ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ሁለቱ ጀርመኖች አንድ የሆኑበት ክስተት የሚያስታውስ ቀን በጀርመን ይከበራል። የኢትዮጵያውያኑን በዓል ደግሞ የጀርመኑን አንድነት ቀንን የሚያስታውስ ዓይነት ክንውን አለው። ነገር ግን የኢትዮጵያውያንም በበርካታ ብሔሮች ባህላዊ አለባበስ እና ጭፈራ የታጀበ መሆኑ ለየት ያደርገዋል።
በመሆኑም የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በዓለም ደረጃ ሊተዋወቅና የቱሪስት መስህብ መሆን ይችላል። ከአራቱም ማዕዘናት የመጡ ብሔሮችን በአንድ ቦታ ሆኖ ማየት የሚፈልጉ ጎብኚዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ አጋጣሚውን መጠቀም ይገባል።
ህንዳዊው ሚስተር አልታዝ ሙሐመድ ደግሞ የታየውን አንድነት የሚያክል ትዕይንት በበዓሉ መመልከታቸውን ይገልጻሉ። በተለያዩ አገራት ቢዘዋወሩም እንዲህ ያለ የበርካታ ብሔረሰቦች ትርዒት እንዳላጋጠማቸው ነው የሚያስታውሱት።
በመሆኑም በርካታ ተሳታፊዎች እንዳሏቸው የብራዚል ካርኒቫል እና የስፔን ኮርማ ግልቢያዎች ሁሉ የኢትዮጵያም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የቱሪስት ቀልብ የመሳብ ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
አንድ ጎብኚ በቅድሚያ ኦሞ ሄዱ ከዚያ አፋር ቀጥሎም ትግራይ ልሂድ ቢል የሚያወጣውን ወጪ ስለሚያስብ ላይሞክረው ይችላል። ነገር ግን ሁሉንም በአንድ ቦታ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል በዓሉ ስላመቻቸ አጋጣሚውን ለቱሪስት መስህብነት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
ሚስተር አልታዝ እንደሚሉት፤ የበዓሉ ማዘጋጀት የቱሪዝም ዕምቅ ሃብትን ከማሳየት ባለፈ የኢትዮጵያውያንን ኅብረት ያሳያል። ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያም ባለፈ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን ሰላም ለማጠናከር የሚረዳ መንገድን ያሳየ አካሄድ ነው። በርካታ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተቀራረበ ባህል እንዳላቸው መረዳት ይቻላል። በመሆኑም በኢትዮጵያውያን መካከል እንደተደረገው የተለያዩ ብሔረሰቦች ባህል ትውውቅ ሁሉ በምስራቅ አፍሪካውያንን ህዝቦች መካከልም ተመሳሳይ መድረክ በማዘጋጀት የቀጣናውን ሰላም እና አንድነት ማጠናከር የሚቻልበትን ዕድል ከበዓሉ መውሰድ ይገባል።
ነህዛ አላውይ ምሃምዲ ደግሞ በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ልክ በኢትዮጵያ እንዳለው ሁሉ በርካታ ባህሎች በሞሮኮም ይገኛሉ። በኢትዮጵያውያን የሚዘጋጀው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልም ለቀጣይ ትውልድ ሊተላለፍ የሚገባው ኅብረትን የሚያሳይ በጎ ዝግጅት ነው። ኢትዮጵያውያን በአመጋገባቸው፣ አለባበሳቸው እና ሙዚቃዎቻቸው የራሳቸው የሆነ ቃና አላቸው። ይህን ልዩ ቃና ደግሞ ጠብቆ ለመቆየት አስፈላጊው ጉዳይ በህብረት መስራት ነው።
እንደ አምባሳደሯ ከሆነ፤ በዓሉ አዲስ አበባ ላይ መከበሩ ደግሞ ስለብሔሮች የቱሪስት መስህብነት በርካታ አፍሪካውያን እና የዓለም ዜጎች እንዲያውቁ ዕድል ይፈጥራል። አፍሪካውያን በወንድማማችነት አህጉራቸውን ማሳደግ ይገባቸዋል ሲባል እንደዚህ ዓይነቶቹ ባህሎች ተጠብቀው ወደ ቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፉ የሚችሉበት መንገድ ላይ በጋራ በመስራት ጭምር መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
ጌትነት ተስፋ ማርያም