በየትኛውም ሀገር እና ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የተቃርኖ መንገዶችም ሆኑ ሀሳቦች የነበሩ፣ ያሉ እና የሚኖሩ ክስተቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ መነጋገርና መወያየት የችግሮቻቸው ሁሉ ቁልፍ ያደረጉ ሀገራትና ሕዝቦች የመኖራቸውን ያህል፤ በየምክንያቱ ጦር መማዘዝ የጀብደኝነትና የጉዳዮች ሁሉ መቋጫ አማራጭ አድርገው የሚከተሉ ቡድኖች በየሀገሩ ታይተዋል፤ እየታዩም ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም እንዲሁ የእነዚህ ሁለት ተቃርኖ ሁነቶች መከሰቻም፤ መገለጫም ሆና ዘመናትን አሳልፋለች፡፡
በዚህ ረገድ በየዘመናቱ የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ማዕከል አድርገው የተከሰቱ የታሪክ ሁነቶችን መመልከት ይቻላል፡፡ በአንድ ወቅት የመደብ ጭቆናን፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የማንነት ጥያቄን፣ አለፍ ሲልም የፍትሃዊነት (በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም፣ በማኅበራዊ ጉዳዩም) አጀንዳን እንዲሁም የእውነተኛ ምላሽ ሰጪነት ነጥቦች የተነሱበት እና የተመለሱበትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ምክንያቱም እነዚህ ክስተቶች የጨቋኝና ተጨቋኝ፣ የሰጪና ተቀባይ፣ የበዳይና ተበዳይ፣ የጠያቂና ተጠያቂ፣… እሳቤ የወለዳቸው፣ የእኛ እና የእነሱ ምልከታ የተጫናቸው፣ በጥቅሉ የባለቤትነት እና የእንግድነት መንፈስን የተላበሱ ስለነበሩ፤ አንዱ ባለ ጥያቄ ሆኖ ሌላው ጥያቄን መላሽ ተደርጎ የተሳለባቸው ነበሩ፡፡
ለዚህም ነው ጠያቂ ነኝ የሚለው አካል በየትኛውም የኃይል አማራጭ ጥያቄዬን አስመልሳለሁ ብሎ የሚነሳው፤ መላሽ የተባለውም ኃይል በጥያቄ ማስመለስ ሂደት የተሳተፉና ኃይልን አማራጭ ያደረጉ ቡድኖችን በኃይል ጨፍልቆ አደብ ለማስያዝ ሲተጋ የኖረው፡፡ በዚህ መልኩ የሚደረግ ጉዞ ደግሞ በአንድ ወቅት አንዱን አሸናፊ፣ በሌላኛው ወቅት ደግሞ ሌላኛውን የበላይ ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡
ይሄን መሰሉ የኃይል ሚዛንን ማዕከል ያደረገ የጠያቂና ተጠያቂ፣ የመልስ ፈላጊና ምላሽ ሰጪ መንገዶች ታዲያ፤ ሕዝብን እንደ ሕዝብ፣ ሀገርንም እንደ ሀገር ዋጋ እያስከፈሉ በማያባራ ጠያቂነትና መልስ ፈላጊነት የታሪክ መንገድ ውስጥ አስገብተውን ዘልቀዋል፡፡ ዛሬም እንደ ሀገር እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶች፣ አለመረጋጋቶችና ጦርነቶች የዚሁ እሳቤ ቅጣያ ስለመሆናቸው እሙን ነው፡፡
ምክንያቱም የንጉሳውያኑን ሥርዓት ያስወገደው የሕዝብ ጥያቄን የማስመለስ አመጽና ግርግር ሥርዓቱን ቀይሮ አልተገታም፤ ይልቁንም ይዘቱን ለውጡ ንጉሳውያኑን የተካውን የደርግ ሥርዓትንም ሲፈትንና ሲሞግት ኖሯል፡፡ የደርግ ሥርዓትን የለወጠው ጥያቄም በዘመነ ኢህአዴግ በቃኝ አላለም፤ ይልቁንም በሕዝባዊ ማዕበል ፍትሃዊነትን ተነጥቄያለሁ ብሎ የ2010ሩን ሀገራዊ ለውጥ (ሪፎርም) ወለደ፡፡
ዛሬም ይሄ ጥያቄ አለኝ፣ መልስም እሻለሁ የሚለው ፍላጎትና እሳቤ ታዲያ እዚህም እዚያም በተለያዩ ቡድኖችና የግለሰብ ስብስቦች አዕምሮ ውስጥ መፈልፈሉ አልቀረም፡፡ ለዚህም ነው ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስትም ከጥቃቅን ረብሻዎች እስከ ሕልውና ጦርነት የደረሰ ቀውስ እንደ ሀገር የተከሰተው፡፡ አሁንም ድረስ በተወሰኑ ቡድኖችና አንጃዎች የሚመሩ አመጾች በአንዳንድ ክልሎች ቀጥለው የሚታዩት፡፡
እዚህ ጋ ሊታሰብና ልብ ሊባል የሚገባው ግን፣ እነዚህ አንጃዎች እዚህም እዚያም ግጭትና ጦርነትን የሚያውጁትና የሚመሩት እንዲመለስ የምንሻው የሕዝብ ጥያቄ አለን በሚል ምክንያት ነው፡፡ ነገር ግን ጥያቄዎቹ የሕዝብ ከሆኑ የሕዝብ ፍላጎት ጦርነት ወይስ ሰላም የሚለውን መገንዘብ እና ሕዝብ የሚፈልገውን መንገድ መከተል ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
ከሰላም የሚያተርፈው ሕዝብ ነው፡፡ ከጦርነት የሚያተርፉት ደግሞ በጦርነት መንገድ ተጉዘው የሚነግዱ በሕዝብ ስም የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት የሚታትሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ናቸው፡፡ እናም ዛሬ ላይ ሀገርና ሕዝብ ስለ ሰላም ተደጋጋሚ ጥሪ እያደረጉ ባለበት ሁኔታ፤ መንግሥትም እንደ መንግሥት ችግሮችና ጥያቄዎች በሰላምና በውይይት ብቻ መፍትሄም ምላሽም እንዲያገኙ በጋራ ቁጭ ብለን እንወያይ እያለ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን በሚያደርግበት ወቅት፤ ይሄንን ጥሪ ተቀብለውና የሰላምን ዋጋም ሆነ የሕዝብን ፍላጎት ተገንዝበው ለሰላም ጥሪው ምላሽ እየሰጡ ያሉ ቡድኖች በተበራከቱበት በዚህ ወቅት፤ ለሰላም መንገድ ጥሪው ጆሮ የሚነፍግ ኃይል ፍላጎቱ ሰላም፣ ዓላማውም የሕዝብ ጥያቄ ነው ለማለት አይቻልም፡፡
ጦርነትንና ኃይልን የችግሮች መፍቻ አድርጎ የወሰደ፤ በዚህም ነፍጥና ግርግርን እንደ አማራጭ ያደረገ ኃይል ሁሉ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው ከሰላምና ሰላም መንገድ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ ወደዚህ መንገድ የገባው የሰላም መንገድ ተዘግቶብኝ ነው የሚል ምክንያት አለኝ ካለም፤ ዛሬ ላይ የሚደመጡ ዘርፈ ብዙ ድምጾች ይሄንን ምክንያት ቦታ የሚያሳጡ መሆናቸውንም በመረዳት፤ ለሰላም ቅድሚያ መስጠትና ያለ ቅድመ ሁኔታ ስለ ሰላም ለሚደመጡ ጽምጾች ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ ለሰላም ምላሽ መስጠት ማለት ደግሞ የሕዝብን ፍላጎት መፈጸምና ለሕዝብ ፍላጎት መገዛት ስለሆነ፤ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ዛሬም ለሰላም ጥሪዎች ጆሮም ጊዜም መስጠት ተገቢ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም