ኢትዮጵያ ከወራት በፊት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጓ እሙን ነው:: ማሻሻያ ለማድረጓ ዋና ምክንያት ከለውጡ አስቀድሞ የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማራመድ የማያስችል በመሆኑ ነው:: በተለይም ኢትዮጵያን ፈትኗት የቆየው የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የግሉ ዘርፍ በሚፈልገው ልክ ብድር ማግኘት አለመቻል ማሻሻያው አስፈላጊ እንዲሆን ማድረጉን በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ መናገራቸው ይታወሳል:: ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም መንደፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ውድቀትን ለመታደግ የሚያስችል እንደሆነም ማስረዳታቸው ይታወቃል::
ከሳምንታት በፊት በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት‹‹ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትናንት የነበረው፣ ዛሬ ያለውና ወደፊት ስላለው ሁኔታ›› ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የተካሄደ መሆኑ ይታወቃል:: በወቅቱ ከአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ደርግ እና የኢህአዴግ መንግሥት ድረስ ስላለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዳሰሳ ተደርጎበታል:: በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ስላለው የኢኮኖሚ አተገባበር በስፋት ውይይት ተካሂዶበታል::
በውይይቱ ወቅትም በተለይም ከግሉ ዘርፍ የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ ትኩረት ያደረጉትም ሥልጡን የሰው ኃይል አስፈላጊነት ላይ፣ በሚጣለው ታክስና ቫት ጉዳይ ላይ፣ የውጭ ባለሀብት እንደሚበረታታው ሁሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን ማበረታት ላይ ምን የታሰበ ነገር አለ የሚሉት ጥቂቶቹ ሲሆኑ የሚመለከታቸውም አካላት በተነሱት ነጥቦች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል::
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ ያደረገችው ሪፎርም እያሳየ ያለው ውጤት በጣም መልካም የሚባል ነው፤ ምክንያቱም ሪፎርሙ በሚቀረጽበትና ተግባራዊ በሚደረግበት ጊዜ ዋና ጉዳይ ምንድን ነው ከተባለ እንደ ግሉ ዘርፍ ያሉ አምራችን ለማበረታታት እንዲሁም የወጪ ንግድን ለማሳደግ ታስቦ ነው:: ከዚህ በፊት የነበረው አሠራር በሕጋዊ መልኩ ኤክስፖርት የሚያደርጉ አካላትን በእጅጉ የሚጎዳ ነው::
ጥንቅቅ ያለ ሥራ እንዲሆን ለማድረግ የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ እናውቃለን ያሉት የባንኩ ገዥው፣ በእኛ እምነት የተነሱ ዓይነት ችግሮች በሂደት እየተፈቱ የሚሄዱ ሲሆን፣ ችግሮችን እየለየንና እየፈታን ለመሔድ እንሠራለን ብለዋል::
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ውስጥ ስለገባን የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት ሊሰፋ ይገባል፤ ይህን ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች መሠራት አለባቸው:: ከዚህ ውስጥ አንዱ ከአሁን በፊት ከነበረው በተሻለ ሪሜታንስን ማበረታታት ሲሆን፣ በዚህ ዙሪያ ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቃል::
እንደግሉ ዘርፍ ኤክስፖርት የሚያደርግ ድርጅት ደግሞ ያገኘውን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ካለምንም ችግር ሳይቀንስና ሳይጨምር ለባንኮቹ መስጠት እንዳለበት የተናገሩት ገዥው፣ ባንኮችም፣ ኤክስፖርተሮችም፣ የግል ዘርፉም በዚህ ዙሪያ በትብብር መሥራት አለበት ብለዋል:: የመሰባሰባችን ዋና ዓላማም በትብብር በመሥራት የኢኮኖሚ ችግሮቻችንን በጋራ ለመፍታት እንደሆነ ተናግረዋል::
ለባንኮች ማስታወቅ የምፈልገው ነገር የውጭ ምንዛሬው ሥርዓት አያያዝ እየተረጋጋ ስለሆነ ባንኮች በተለየ ትኩረት የውጭ ምንዛሬ የማሰባሰብ ሥራ ላይ ሊሰሩ ይገባል:: በተለይ ከውጭ የሚላክ ገንዘብን በተመለከተ በስፋት መሥራት አለባችሁ ብዬ አስባለሁ ሲሉ አቶ ማሞ አሳስበዋል:: ሰዎች የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚችሉ ከሆነ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ይረዳል:: ስለዚህ በዚህ አቅጣጫ መሥራት ተገቢ ነው ሲሉ አስረድተዋል::
የብሔራዊ ባንክ ገዥው እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ባለፉት ስድስት ዓመታት ብዙ የተሞከሩ ሥራዎች አሉ:: እንዲህ ሲባል ቀደም ባሉ ዓመታት የተሞከሩ ሥራዎች ሁሉ ምንም ዋጋ የላቸውም ማለት አይደለም:: ከዚህ በፊት የነበሩት መንግሥታት በገባቸው ልክ በቅን ልቦና ሀገራቸውን ወደፊት ለማሳደግ ሰርተዋል:: ከሰሩትም ሥራ የሚወሰድ ነገር አለ::
ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ወጥ በሆነ መልኩ ሁሉንም ነገር መንግሥት ብቻ ይሥራው የሚል ነበር፤ ይህ አካሔድ ትክክል አይደለም፤ በደርግ አይተነዋል:: መንግሥት ብቻውን ልማት ሊያመጣ አይችልም:: በሌላ በኩል የግሉ ዘርፍ ብቻ ሥራውን ይሥራ ሊባልም አይችልም:: ምክንያቱም በእኛ ሀገር ያለው የግሉ ዘርፍ እያደገ ቢሄድም ብቻውን ግን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሊሸከም አይችልም:: ስለዚህ ዋናው ቁልፉ ነገር ምንድን ነው ከተባለ ሀገራችንን ወደፊት ለማራመድ ከፈለግን ገበያን በሚደግፍ መንግሥት፣ የግል ዘርፉን በሚደግፍ መንግሥትና በግል ዘርፉ ትብብር ሀገራችንን ማሳደግ ነው:: ዋና ነጥቡ የትብብርና የጋራ መንፈስ መኖር መቻል አለበት ይላሉ::
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በግሉ ዘርፍ የተነሱ ሃሳቦች ተገቢ ናቸው ይላሉ:: ልክ እንደ ብሔራዊ ባንክ ገዥው ሁሉ እርሳቸውም፤ የሀገር ልማት የጋራ ሥራ መሆኑ እሙን ነው ይላሉ:: አክለውም እኛ እድለኞች ነን ብዬ አስባለሁ:: የኢትዮጵያን ለዘመናት ቆየ የኢኮኖሚ መሻት ለማሳካት የሚችልበት የተሟላ እይታ እየመጣ ነው:: የተሟላ እይታ ሲባል የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ የሕዝቡ መነሳሳት፣ የግሉ ዘርፍ ለአጋርነት መቆም እንዲሁም ከየት ተነስተን ምን እንደምንፈልግ ግልጽ የሆነ ነገር ይዘናል ማለት ነው:: ይላሉ::
በየትኛውም ሀገር ተሞክሮ ወስዳችሁ ብታዩት ሀገር የምትበለጽገው አንድ ትውልድ ጨክኖ በሚሠራ ሥራ ነው:: አንድ ትውልድ ጥርሱን ነክሶ አሻጋሪ የሆነ ሥራ መሥራት አለበት:: የኢትዮጵያ ሕልም ምንድን ነው በጋራ መሄድ የምንችለው የት ነው:: እስካሁንስ ሳይሳካ የቀረው ለምንድን ነው የሚለውን መለየት ያስፈልጋል:: በቀጣይም ይህ ትውልድ የብልፅግና ጉዞውን ያሳካል የሚለው ላይ ርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል::
የአምራች ዘርፉን ማገዝ ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ የአምራች ዘርፉን ጠጋ ብሎ በመምራትና በማገዝ ረገድ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት የተሔደበትን ርቀት ማየቱ መልካም እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህም ለቀጣይ ሥራ አጋዥ ነው ብለዋል:: መንግሥት ብዝሀ ዘርፍ ላይ ትልቅ ሥራ እየሠራ እንደሆነም አስታውሰዋል:: ግብርና ላይ የመጣው የሚገርም ሥራ ነው፤ መንግሥት ማዕድን፣ ቱሪዝምና ሌሎችን ጨምሮ ብዝሀ ዘርፍ ላይ በተከታታይ ለመሥራት ሞክሯል::
በዕለቱ የኢትዮጵያን የትናንቱን፣ የዛሬውንና የነገውን ኢኮኖሚ ምን እንደሚመስል ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በታዳሚያኑ የተነሱ ጥያቄዎች እንደየዘርፉን የሚወሰዱና እንዴት የፖሊሲ ግብዓት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚታዩ ይሆናሉ ብለዋል::
ፍጹም (ዶ/ር) ልክ እንደ እዮብ (ዶ/ር) ሁሉ ሀገርን ለማሻገር አንድ ትውልድ የግድ ዋጋ መክፈል አለበት ይላሉ:: እነዚያ የሚያሻግሩ ትውልዶች ቁርጥ አቋም የሚወስዱና ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ እንደሆነም አስረድተዋል::
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያደጉ ሀገሮችን ታሪክ ስናጤን ጥቂት የማይባሉቱ ያደጉት አንድ ትውልድ በከፈለው ዋጋ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፣ እንዲያም ሆኖ የሁሉም ልምድ አንድ ዓይነት ነው ማለት እንደማይቻል አመልክተዋል:: የሚያሳየን ነገር ቢኖር አንደ ትውልድ ዋጋ መክፈል እንዳለብን ነው:: ይህ ዋጋ የከፈለ ትውልድ፣ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖለት ሳይሆን ለልጆቹ የተሻለ ሀገር ለመሥራት ዋጋ መክፈል ስላለበት የሚያደርገው ሲሉ ገልጸዋል::
ስለሆነም የሀገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ፣ ሀገሩ ኢትዮጵያ ስለሆነች ከውጭ ከሚመጣው ይልቅ በእኔነት መንፈስ አንድ ሆኖ ተናብቦ የረጅም ጊዜ ሕልማችንን እንዲጋራ ነው ፍላጎታችን ይላሉ:: ዋና ዓላማው እኛ ይህን ዋጋ ለመክፈል የተመረጥን ትውልዶች መሆናችንን መረዳት ነው:: ስለዚህም ዋጋ ከፍለን ከፊት ለፊታችን የምናየውን ግብ እና አጓጊ ሕልም እንድናሳካ አብረን እንሁን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል::
እንደ አቶ ማሞ ገለጻ፤ መንግሥት ብቻውን የኢትዮጵያን ችግር ሊፈታ አይችልም:: ስለዚህ የግሉ ዘርፍ የራሱን ሚና መወጣት መቻል አለበት:: የሁለቱ ትብብር ሀገሪቱን ወደፊት የሚያስኬዳት ይሆናል:: ለዚህ ደግሞ ጥንካሬን ይፈልጋል:: በተቻለ መጠን መንግሥት የግሉን ዘርፍ መደገፍ ይጠበቅበታል:: የግል ዘርፉ ሀብት እንዲፈጥር ሊገፋፋ ይገባል:: የግሉ ዘርፉ የተሻለ ሀብት አፍርቶ፣ የሥራ እድል ፈጥሮ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ አስገኝቶ ሀገሪቷን ወደፊት ሊያሳድግ ይገባል::
ሌላው ፍጹም (ዶ/ር) እንደጠቀሱት፤ በተቻለ መጠን መንግሥት የረጅም ጊዜ እይታ ያለው መሆን አለበት:: ይህን ለማድረግ ሁለት ቁልፍ ነገሮች አሉ:: አንደኛ የግሉ ዘርፍ እንዳነሱት ሁሉ የረጅም ጊዜ የሰብዓዊ ልማት ላይ መሥራት ያስፈልጋል:: ለምን ቢባል የለሙ ሀገሮችን ካልለሙ ሀገሮች የሚለየው ትልቁ ነገር ምንድን ነው ከተባለ ቴክኖሎጂ ነው:: ቴክኖሎጂ ደግሞ በሰው አዕምሮ ያለ ነገር ነው:: የረጅም ጊዜ እይታ ማለት በሰው ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ወደፊት የሚያስኬደን የጋራ የሕዝብ ኢንቨስትመንት መሠረተ ልማት ላይ የሚተኩር መሆን አለበት::
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግሥት ታዳሽ ኃይል ላይ ኢንቨስት እያደረገ ነው:: ይህ በዋናነት ዓላማው ምንድን ነው ከተባለ የኢትዮጵያ እድገትና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲጓዝ ስለታሰበ ነው::
የሀገራችንን ልማት ለማረጋገጥ ከፈለግን የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ አስፈላጊ ነው:: ይህ መሠረታዊ ነው:: የውጭ ምንዛሬ አስተዳደሩ፣ የገንዘብ ፖሊሲ አስተዳደሩ፣ የፊስካል አስተዳደሩ፣ የፋይናንስ ሴክተር አስተዳደሩ በተቻለ መጠን የተረጋጋ መሆን አለበት:: ይህ ስኬታማ የሚሆነው በትብብር መሥራት ሲቻል ነውና አብረን እንሥራ ሲሉ ጥሪ ያቀርባሉ:: ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሥራ እንደሌለም ጠቅሰው፤ ሥራውን በጋራ እንሥራ ሲሉ ያበረታታሉ::
ፍጹም (ዶ/ር)፣ የባንክ ገዥውን ሐሳብ ሲያጠናክሩ እንዳሉት፤ መንግሥት የሚያወራው ስለአምስት ዓመት ርዕይ ሳይሆን የረጅም ጊዜ እና ለትውልድ ስለሚሻገር እይታ ነው:: ይህን ሕልም የግሉ ዘርፍም ሆነ ሁሉም እንዲጋራ ይፈለጋል:: የአጭር ጊዜ ፈተናዎችን እንደምንፈታው ሁሉ የረጅም ጊዜ ሕልማችን እውን እንዲሆን ከወዲሁ አካሔዳችንን ማስተካከል ይኖርብናል::
ግብርና ላይ ትኩረት የምናደርገው ለሌሎቹ ዘርፎች ወሳኝ በመሆኑ ነው:: በሌላ በኩል የሰው ሀብት ልማት ላይ መሥራት አለብን፤ ርካሽ የሰው ኃይል ሳይሆን ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ላይ እንሠራለን ሲሉ ፍጹም (ዶ/ር) ተናግረዋል::
ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ (ዶ/ር)፣ ታክስን በተመለከተ ሲናገሩ፤ ሁሉም የራሱ ሴክተር ታክስ እንዳይጣልበት ፈላጊ መሆኑ ሲሆን፣ ታክስ ካልሰበሰብን ደግሞ የምናሰበውን ሀገራዊ ለውጥ ልናመጣ አንችልም ሲሉ ያስረዳሉ:: ስለዚህም ሚዛን መጠበቅ የግድ ነው ይላሉ::
በተዘዋዋሪ መንግሥት በተለያዩ አቅጣጫዎች ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ ነው:: ከተማሪ ምገባ ጀምሮ በሴፍትኔት ብዙዎቹን እየመገብን ነው:: ዘይት ደጉመን እያስገባን ነው:: በጣም ደሃ ተኮር የሆነ መንግሥት ነው:: በጥቅሉ አሁንም ቢሆን ድጋፍ የሚፈልጉትን ዘርፎች ለይተን የምንደግፍ ይሆናል ብለዋል::
አሁን ሪፎርም ጨርሰናል:: ስለሆነም አሁን የአዝመራ ጊዜ ነው:: የዚህን ሪፎርም ውጤት በዘርፎች የምናይበት፣ ሀገር ሽግግር ላይ መሆኗን የምናይበት እንዲሁም በአጠቃላይ ለኢትዮጵያውንና ለኢትዮጵያ ያስቀመጥንላት ግብ የሚሳካ መሆኑን የምናይበት ጊዜ ነው:: ትልቁን ሥራ አመራር የሚቀጥል ሲሆን፣ ታክስ መክፈል፣ የግሉን ዘርፍ ማበረታታት፣ ባንከሩ በአግባቡ የጋራ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ እንዲገባ ማድረግ፣ ይህን እየፈጠርን መሔድ ይጠበቅብናል:: የኢትዮጵያ ብልፅግና እነዚህን መሰል ድልድዮች ይፈልጋል::
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የዕለቱ ውይይት ዋና ዓላማ፤ ዘመናዊ ኢኮኖሚ መገንባት ነው:: በዚህም በሁሉም ዘርፎች ተከታታይ የሆነ ውጤት መምጣቱን ለማረጋገጥ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ እድገትን ማረጋገጥ ነው:: በተለይ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከታታይነት እንዲኖረው ማድረግ ይጠይቃል::
ስለሆነም ዋናው ነገር ተከታታይነት ያለው፣ ዘላቂነት ያለው በቴክኖሎጂ እድገት የታገዘ፣ ዘርፈ ብዙ እድገት ማረጋገጥ ነው:: ግብርና ላይ ብቻ ሳይሆን እኛ ትኩረት ማድረግ ያለብን ሁሉም ዘርፍ ላይ ነው ብለዋል::
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የኢኮኖሚ ሚና ያላቸው ኃይሎችን በጠቅላላ በተሟላ መልኩ ምርታማ እንዲሆኑ ማስቻል ነው:: የግሉን ዘርፍ በሚገባ ማብቃት፣ የሕዝቡን የተደራጀ ተሳትፎ ማጠናከር፣ የመንግሥት ተቋማት ብቃት ያለው አገልግሎትና ሀብትን ወደ ንብረት የመቀየር ጉዳይ በሚገባ እንዲያሳኩ ማድረግ ነው:: ሕዝቡን በአግባቡ በማስተዳደር ሰላምን አረጋግጦና አጠናክሮ መሄድ ነው::
ስለዚህ ጠንካራና ዘላቂ ተቋማት ያለው ሀገረ መንግሥት መገንባት የሚቻለው መሠረት ልማት ላይ በብቃትና በተከታታይነት ኢንቨስት ማድረግ ሲቻል ጭምር ነው:: ዘርፈ ብዙ በሆነ መልኩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍና የማብቃት፣ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢኮኖሚያችን ገብተው እንዲያሳድጉ ማድረግም የሚጠበቅ ነው ብለዋል::
ይህን ለማድረግ የቁጠባ መጠንን ማሳደግ ያስፈልጋል:: ከውጭ የሚላከውን ገንዘብና የኤክስፖርትን መጠን በኢኮኖሚው ውስጥ ማሳደግም ወሳኝ ነው:: ሁሉም ዘርፎች ለገቢም ለኤክስፖርትም በከፍተኛ ደረጃ እንዲያመርቱ ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጓል:: ቱሪዝም፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ አገልግሎት እንዲሁም ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት የተደረገው ለዚያ ነው:: ስለዚህ ዘርፈ ብዙ እድገትን ማረጋገጥ፣ ባለብዙ ተዋናዮችን ሚና በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ፣ ይህም ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ፣ የረጅም ጊዜ እይታ ያለው አጠቃላይ አካሔድ ነው ያለን ሲሉ አብራርተዋል::
ለዚህም ነው የ30 የ50 ዓመት እያልን በረጅም ጊዜ ትልም እየተንቀሳቀስን ያለነው ያሉት አቶ አሕመድ፣ ይህ ደግሞ እንደተባለው የትውልድን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው ብለዋል:: የኢኮኖሚ እድገት ስንል ተከታታይነትና የተረጋጋ ኢኮኖሚ መፍጠርን፣ አንድነትንና በጋራ መሥራትን፣ ሰላማችንን በሚገባ ማረጋገጥን ይጠይቃል:: በተለይ ደግሞ ሁሉም ዘርፎች በኢኮኖሚ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በሚገባ ማሳደግን የሚጠይቅ መሆኑን አመልክተዋል::
የግሉ ዘርፍ ዋነኛው የልማት ሞተር ነው:: መንግሥት ያለው ሚና የማስተባበርና ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ብሎም የመምራት ነው:: ስለዚህ ሁሉም ዘርፎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የተቀመጠው የረጅም ጊዜ እቅድ ነው:: ይህ ደግሞ የጋራ ሥራን ይጠይቃል:: ሀገራችን የበለጸገች እንድትሆን በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ዘርፍም ጠንካራ ሆና እንድትሔድ የሚሰራው ሥራ ተጠናክሮ የሚሄድ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም