የደን መራቆት ችግር የአየር ሁኔታን በማዛባት ለተፈጥሮ አደጋዎች ከማጋለጥ ባሻገር ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት እንዳለው ይገለጻል። በተለይም የሀገሪቱን የልማት እንቅስቃሴ ለማሳካትም የደን ዘርፉ እድገት ወሳኝ መሆኑ ይገለጻል። የተራቆተ መሬትን መልሶ እንዲያገግም ለማድረግም መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን የጋራ ርብርብ ይጠይቃል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጎዱ አካባቢዎችን በደን ለመሸፈንና እንዲያገግሙ ለማድረግ የአረንጓዴ ዐሻራን መርሐ ግብርን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮግራሞች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው። የደን ሽፋንን ለማሳደግና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችም እየተሠሩ ይገኛል። ታዲያ ለመሆኑ የተራቆተ መሬትን መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ።
በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ያደሳ እንደገለጹት፣ የተራቆተ መሬትን መልሶ እንዲያገግም በማድረግ የሁምቦና የሶዶ አርሶ አደሮች ብቻ ከካርቦን ሽያጭ አንድ ነጥብ 18 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።
የተራቆተ መሬትን መልሶ እንዲያገግም የሚያስችለው ፕሮጀክት በስምንት ክልሎች በሚገኙ 37 ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፣ እስካሁን ከ268 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን መልሶ ማልማት መቻሉንም ነው የገለጹት።
ፕሮጀክቱ አካባቢውን ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ መልሶ እንዲያገግሙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የአፈር መሸርሸርን መቀነስ፣ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ለእንስሳት መኖን ጨምሮ፣ ብዝኃ ሕይወትን ለመጨመርና የአርሶ አደሩንም ገቢ ለማሳደግ እንደሚያስችል ይገልጻሉ።
በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ 388 ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በፕሮጀክቱ ትግበራ ዙሪያ ሥልጠና ለአርሶ አደሮች መሰጠቱንም ያስረዳሉ።
ፕሮጀክቱ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በመካከለኛው ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በአፋር ክልሎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝም በመግለጽ፣ ፕሮጀክቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ለሚገኘው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ትልቅ አስተዋፅዖ ያለው መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር የተራቆተ መልክዓ ምድርን መልሶ እንዲያገግም ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በአካባቢው የሰዎች ባለቤትነት ስሜት ባለመኖሩ ምክንያት የደን ዛፎችን ለማገዶነትና ለመኖ በመጠቀም መሬቱ ባዶ ቀርቶ እንደነበር የሚገልጹት ደግሞ የሆቢቻ በዳ ወይጦ ተራራ ደን ልማትና ጥበቃ መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበር ሰብሳቢ አቶ መኮንን ጉጆ ናቸው።
በአካባቢው የታየውን የደን መራቆት ተከትሎ ድርቅ፣ የምርት መቀነስ፣ የውሃ እጥረትና የእንስሳት ሞት ተከስቶ እንደነበር በመግለጽ፣ የተራቆተው መሬት መልሶ ለማልማት በተደረገው ጥረት በአካባቢው የደን ሽፋን ማደግ መቻሉን ይናገራሉ።
በማኅበር በመደራጀት ደኑን የመጠበቅ ሥራ መሥራታቸውንና ከደን ልማቱ የካርበን ሽያጭ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በየዓመቱ ከሚገኘው ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ በመጠቀም የልማት ሥራዎችን እንደሚሠሩ፣ ወፍጮ ቤት ማቋቋማቸውንና ለትምህርት ቤቶች እገዛ ማድረጋቸውን ያስረዳሉ።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም