በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወታደራዊ ሕግ ያወጁት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ዮል ለተግባራቸው ይቅርታ ጠየቁ። ፕሬዚዳንቱ ሌላ እንደዚህ ዓይነት ድንጋጌ እንደማይኖር ቃል ገብተዋል። የህዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም መግለጫቸውን የሀገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት በፍጥነት የቀለበሰው ሲሆን፣ እርሳቸውም ከሥልጣን ሊነሱ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የፕሬዚዳንቱ ንግግር ምላሽ ተከትሎ የገዥው ፓርቲ ፣ ፒፕል ፓወር ፓርቲ መሪ (ፒፒፒ) ለጋዜጠኞች እንደተናገረው ዩን መደበኛ ሥራቸውን ማከናወን ከብዷቸዋል። ሃን ዶንግ-ሁን “ከሥልጣናቸው ቀድመው መልቀቃቸው የማይቀር ነው” ብለዋል። “በጣም አዝናለሁ እናም የተደናገጡትን ሰዎች ከልብ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ” ሲሉ ዩን በቴሌቪዥን በተላለፈ አጭር ንግግራቸው ይቅርታ ጠይቀዋል።
“ሀገሪቱ በወታደራዊ ዕዝ ሥር እንድትሆን ማወጄን በተመለከተ፣ ራሴን ከማንኛውም የሕግ ወይም እና ፖለቲካዊ ኃላፊነቶች አልሸሽም”ነው ያሉት፡፡ ፕሬዝዳንቱ ሀገሪቱ በወታደራዊ ዕዝ ሥር እንድትሆን ከደነገጉ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለሕዝባቸው ንግግር ሲያደርጉ ከሥልጣን እንደሚወርዱ ያሳውቃሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይህንን አላደረጉም፤ ይልቁንም ሁኔታውን የማረጋጋት ሥራ ለገዥው ፓርቲያቸው አሳልፈው መስጠታቸውን ገልጸዋል።
ከሥልጣን እንዲነሱ ክስ ስለመቅረቡም ያሉት ነገር የለም። ቅዳሜ ዕለት ተቃዋሚዎች ዮንን ከሥልጣን ለማውረድ በቀረበው ጥያቄ ላይ ድምጽ እንዲሰጥ ግፊት እያደረጉ ነው። 300 መቀመጫዎች ባሉት ፓርላማ ውስጥ፣ ጥያቄው ሁለት ሶስተኛ ድምጽ ማግኘት ያለበት ሲሆን፣ ቢያንስ ስምንት የዩን ፓርቲ አባላት ድጋፋቸውን መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሊ ጄ ሚዩንግ አርብ ዕለት የፕሬዚዳንት ዩን አስተያየት በጣም እንዳሳዘናቸው እና የሕዝቡን የቁጣ እና የክህደት ስሜት እንደሚጨምሩ ተናግረዋል። ሊ አክለውም ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን ለማውረድ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። “በአሁኑ ወቅት ደቡብ ኮሪያን የገጠማት ትልቁ ስጋት የፕሬዚዳንቱ በሥልጣን ላይ መኖር ነው።” ሲሉ ገልጸዋል።
በዩኦን ድርጊት የተበሳጩት ፖለቲከኞች ብቻ አይደሉም። የ50 ዓመቷ ያንግ ሶንሲል በደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሴኡል በሚገኘው የናምዳሚን ገበያ የምግብ ቤት ባለቤት ነች። ሀገሪቱን በወታደራዊ ዕዝ ስር የሚያስቀምጠው ሕግ ሲታወጅ ፍርሃትና አለማመን እንደተሰማት ተናግራለች። “በእሱ [ዮን] እንደ ፕሬዚዳንት ሙሉ እምነት አጥቼበታለሁ፣ እሱ ከእንግዲህ የእኔ ፕሬዚዳንት ነው ብዬ አላስብም” ብላለች።
“እስከ መጨረሻው ድረስ መታገል አለብን፤ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ እንዲይዝ መፍቀድ አንችልም። “በዚያው ገበያ ላይ የተገኘው ሸማቹ ሃን ጁንግሞ ደግሞ፣ ፕሬዚዳንት ዮን ይቅርታ መጠየቁ በቂ አይደለም ።ፕሬዚዳንቱ ከሕዝቡ ጋር ያላቸውን አመኔታ በማፍረሳቸው “ወይ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቅ አልያም በሕግ እንዲወርዱ ሊደረግ ይገባል” ብሏል።
“በፕሬዚዳንትነቱ ለመቀጠል ፍላጎት ካሳየ በጣም ተስፋ ቢስ ሁኔታ ይሆናል፤ ምክንያቱም ይህ ፕሬዚዳንት የፈጸመው በደል የወታደራዊ ሕጉ ብቻ አይደለም። “ደቡብ ኮሪያ ማክሰኞ ምሽት ላይ ዩን አስደንጋጩን ወታደራዊ ሕግ ማወጃቸውን ተከትሎ በፖለቲካዊ ቀውስ እና ትርምስ ውስጥ ገብታለች። ፕሬዚዳንቱ ከሰሜን ኮሪያ ኮሚኒስት ኃይሎች ሀገራቸውን ለመጠበቅ ወታደራዊ ሕጉ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን ወታደራዊ ሕጉ በታወጀ ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፓርላማ አባላቱ ፕሬዚዳንቱን ተቃውመው በምክር ቤት ከተሰበሰቡ በኋላ አስቸኳይ ድምጽ በመስጠት ውሳኔውን አግደዋል። ፕሬዚዳንቱ ይህንን ሕግ እንዲያውጁ ምክንያት የሆናቸው እሳቸው እንዳሉት የውጭ ኃይሎች ስጋት ሳይሆን ውስጣዊ የፖለቲካ ችግሮች እንደሆኑ ግልጽ የሆነው ብዙም ሳይቆይ ነበር።
አንዳንድ የሕግ አውጭዎች ፓርላማ ውስጥ ለመሰብሰብ እና የዮንን ድንጋጌ ለመሻር ለማድረግ የጸጥታ ኃይሎችን ለማለፍ አጥር ሲዘሉ፣ የተቀመጡ መከላከያዎችን ሲሾልኩ ታይተዋል። የፓርላማ አባላት የዮን ድንጋጌ ከሻሩ በኋላ፣ ሌላ አዋጅ ያወጣሉ ተብሎ ተሰግቶ ነበር። አንዳንድ የሕግ አውጭዎች ሌላ ሕግ ቢወጣ በፍጥነት ለመሻር በብሔራዊ ምክር ቤት አቅራቢያ ቆይተው ነበር ተብሏል።
ወታደራዊ ሕግ (ማርሻል ሎው) የሲቪል ባለሥልጣናት ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደማይችሉ በሚቆጠርበት ጊዜ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲመሩ የሚደረግበት ጊዜያዊ አገዛዝ ነው። አንዲት ሀገር በወታደራዊ ሕግ ስር በምትሆንበት ወቅት የሲቪል መብቶች መታደግ እንዲሁም ወታደራዊ ሕጉ ሊራዘም የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በደቡብ ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ወታደራዊ ሕግ የታወጀው በአውሮፓውያኑ 1979 ሲሆን፣ ወቅቱም ሀገሪቱን ለበርካታ ዘመናት የገዙት አምባገነኑ ፖርከ ቹንግ ሂ በመፈንቅለ መንግሥት መገደላቸውን ተከትሎ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም