የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ቡድን ተሸለመ

ፓሪስ በ2024 ባስተናገደችው 17ኛው ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሽልማት ተበርክቶለታል:: ቡድኑ በፓራሊምፒክ ውድድሩ ሁለት አሯሯጮችን ጨምሮ በስድስት አትሌቶች ተሳትፎ ሁለት የወርቅና አንድ የብር በጥቅሉ ሶስት ሜዳሊያ እንዲሁም ዲፕሎማ በማስመዝገብ አዲስ ታሪክ መስራቱ ይታወሳል::

ይህን አኩሪ ውጤት ያስመዘገበው የፓራሊምፒክ ቡድን አትሌቶችና ተሳትፎ የነበራቸው የቡድኑ አባላት ከወራት በኋላ የማበረታቻ ገንዘብና እውቅና ከትናንት በስቲያ ተረክበዋል::

በዚህም መሰረት ሙሉ ለሙሉ የዓይነ ስውራን የ1ሺ500 ሜትር ውድድር የዓለምና የፓራሊምፒክ አሸናፊዋ አትሌት ያየሽ ጌቴ የዓለምን ክብረወሰን በመስበሯ ጭምር 7 ሚሊዮን ብር እንዲሁም 50 ግራም ወርቅ ተሸልማለች። ሌላኛዋ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ 7 ሚሊዮን ብር ስትሸለም፣ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው አትሌት ይታያል ስለሺ ደግሞ 4 ሚሊዮን ብር ተበርክቶለታል:: ዲፕሎማ ያስመዘገበው አትሌት ገመቹ አመኑ ደግሞ 200 ሺ ብር ተሸልማል::

የወርቅና የብር ሜዳሊያዎች እንዲሁም ዲፕሎማ እንዲመዘገብ ምክንያት የሆኑት አሰልጣኝ ንጋቱ ኃይለማርያም የ2 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆነዋል። በልኡኩ የተለያየ ኃላፊነት የነበራቸው ባለሙያዎችም የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል::

የሽልማት መርሀ ግብሩን ተከትሎ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ፣ ‹‹በሀገራችን ከ17 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አካል ጉዳተኞችን መደገፍ ሀገር የማልማት አንዱ አካል ነው። ዛሬ በትንሽ ድጋፍ ይህንን ውጤት ያመጣችሁ በብዙ ብንደግፍ ደግሞ ሀገራችንን በዓለም አደባባይ ከፍ ታደርጋላችሁ። በመሆኑም በቀጣይ በሰፊው በመደገፍ አብረን እንሰራለን፤ እናንተም በሰፊው ድል አድርጋችሁ ሀገራችሁን እንደምታኮሩ ተስፋዬ ነው›› ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ በበኩላቸው፤ ስፖርት የሰውን አዕምሮ የሚገነባ፣ በመተባበር የሚሰራ፣ ለድል የሚያበቃ ሰውነትና አዕምሮ የሚያዳብር ትልቅ ዘርፍ መሆኑን ገልጸው፤ ‹‹አካል ጉዳተኛ የሚለው ቃል ስለሚባል ብቻ እንለዋለን እንጂ ልበ ሙሉዎች ናቸው። በስፖርት ዘርፍ የሀገራችሁን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ስላደረጋችሁ ክብር ይገባችኋል። ይህንን ሽልማት ያዘጋጀውና ከአካል ጉዳተኞች ጋር በስፋት የሚሰራውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም አመሰግናለሁ›› በማለት ተናግረዋል::

አትሌቶች በቂ ስልጠና ወስደው እንዲወዳደሩ ለማድረግ ባለው አቅም ከፍተኛ ጥረት መደረጉን የጠቆሙት የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ጊዮን አሰፋ፤ አትሌቶቹ በፓሪሱ የፓራሊምፒክ ውድድር ውጤታማ የሆኑት በተገቢው ልክ ድጋፍ አግኝተው ሳይሆን በተለያዩ ውድድሮች ተሳትፎ ባዳበሩት ምርጥ አቅማቸው መሆኑን መስክረዋል:: ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ላደረገው መጠነ ሰፊ ድጋፍም ምስጋና እንደሚገባው ገልጸዋል::

በፓራ አትሌቲክስ ስፖርት በ1ሺ500 ሜትር ሙሉ በሙሉ የዓይነ ስውራን ውድድር አትሌት ያየሽ ጌቴ 4፡27.68 በሆነ ሰዓት የዓለም ክብረወሰን በመስበር አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል:: በኢትዮጵያ የፓራሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በቶኪዮ 2020 ፓራሊምፒክ ላይ ያስመዘገበችው አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ደግሞ ፓሪስ ላይም ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በ1ሺ500 ሜትር ጭላንጭል መድገም ችላለች:: በተመሳሳይ ርቀት በወንዶች ጭላንጭልም አትሌት ይታያል ስለሺ የብር ሜዳሊያ አስመዝግቧል:: በዚህም ውጤት መሰረት ኢትዮጵያ በፓሪስ ፓራሊምፒክ ከዓለም 44ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፤ በአፍሪካ ደግሞ ከአልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ እና ግብጽ በመቀጠል ስድስተኛ ሆና ማጠናቀቋ አይዘነጋም::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You