በሀገራችን በፍትህ ሥርዓት ከሚታወቀው የሕግ አይነት አንዱ የወንጀል ሕግ ነዉ:: የተለየዩ ድርጊቶችን በሕግ ወንጀል በማድረግ ልዩ ልዩ የወንጀል ሕጎች ያሉ ሲሆን ለምሳሌ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ፤ የፀረ ሽብር ሕግ፤ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሕግ፤ የሙስና ወንጀሎች ሕግ እና ሌሎች ሕጎች ይገኛሉ:: የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አጠቃላይ ወንጀል ምንነትና የሙስና ልዩ ባህሪን የሚመለከት ነው:: ስለሆነም ወንጀል ማለት ምን ማለት ነዉ? የሙስና ወንጀል ትርጉሙ ምንድን ነው? የሙስና ወንጀል ከሌላው ወንጀል አንጻር ልዩ ባህሪያት ምን እንደሆነ ለመዳሰስ ተሞክሯል::
ሀ/ የወንጀል ትርጉም
አንድ ድርጊት ወንጀል ነው ለማለት በወንጀል ሕጉ በተጠቀሰው መሰረት ሶስት ፍሬ ነገሮች መሟላት አለበት:: አንደኛው ፍሬ ነገር (element) በሕግ የተከለከለ ድርጊት መሆን አለበት:: ድርጊቱ በሕግ እንዲያደርግ ወይም እንዳያደርግ የሚገልጽና ይህንን ግዴታ የተላለፈ ሰው ላይ ቅጣት የሚጥል መሆን አለበት::
በ1996 ዓ.ም የወጣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 2 ስለ ሕጋዊነት መርህ ሲገልጽ የወንጀል ሕግ ስለ ልዩ ልዩ ወንጀሎችና በወንጀል አድራጊዎች ላይ ስለሚፈፀሙት ቅጣቶችና ጥንቃቄ እርምጃዎች በዝርዝር እንደሚደነግግ ይገልጻል::
ፍርድ ቤቱ ሕገወጥነቱ በሕግ ያልተደነገገን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደ ወንጀል ሊቆጥረው እና ቅጣት ሊወስንበት አይችልም:: ፍርድ ቤቱ በሕግ ከተደነገጉት በቀር ሌሎች ቅጣቶችንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሊወስን አይችልም በማለት ያስቀምጣል:: ስለሆነም አንድ ሰው የፈጸመው ድርጊት በሕግ የተከለከለ ካልሆነና የተከለከለ ሆኖም ቅጣትን የማይወስን ከሆነ የወንጀል ድርጊት አይሆንም:: ሁለተኛው ፍሬ ነገር በሕግ የተከለከለ ድርጊትን መፈጸምን የሚመለከት ነው::
በተመሳሳይ ሕግ አንቀጽ 23 ሕገወጥነቱና አስቀጪነቱ በሕግ የተደነገገውን ድርጊት መፈጸም ወንጀል ነው ይላል:: በሕጉ መሰረት ድርጊት ማለት በሕግ የተከለከለውን ማድረግ ወይም በሕግ የታዘዘውን አለማድረግ ነው:: ሶስተኛ ፍሬ ነገር የሀሳብ ክፍል ወይም ሞራላዊ ፍሬ ነገር የሚመለከት ነው::
በወንጀል ሕግ አንቀጽ 23(2) ላይ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ወንጀሉን የሚያቋቁሙት ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ተሟልተው ሲገኙ ብቻ ነው:: ሞራላዊ ፍሬ ነገር ሲባል የወንጀል ድርጊት የተባለውን ድርጊት አድራጊው ሆን ብለው አስበው ወይም በቸልተኝነት ስለመፈጸሙ የሚመለከት ሲሆን ይህም የሚረጋገጠው ከተፈጸመው ግዙፋዊ ድርጊት አፈጻጸምን በማመዛዘን ነው::
በመሆኑም ወንጀል ድርጊት የሚባለው ድርጊትን የሚከለክል ሕግ፣ በሕግ የተከለከለ ድርጊት መፈጸምንና በሕጉ በተጠቀሰው የሀሳብ ክፍል አይነት አስበው ወይም በቸልተኝነት የተፈጸመ ሲሆን ነው::
ለ/ የሙስና ወንጀል
የሙስና ወንጀል ትርጉም በሙስና ወንጀሎች ሕግ ላይ በግልጽ ትርጉም አልተሠጠም:: ማንኛውም የመንግስት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ወይም ሌላ ማንኛውም ሰው በ2007 ዓ.ም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 2 ስር የተመለከተውን የሙስና ባህርይ የሚያሟላ ወንጀል በፈጸመ ጊዜ ለወንጀሉ የተደነገጉ የቅጣት ድንጋጌዎች ይፈጽመብታል ይላል::
ማንኛውም የመንግስት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማይገባ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በተሰጠው ኃላፊነት ወይም ተግባር ማድረግ የሚገባውን እንዳያደርግ ወይም ማድረግ የማይገባውን እንዲያደርግ ከሌላ ሰው ላይ ጥቅም የተቀበለ ወይም የጠየቀ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ለማስገኘት የተሰጠውን ስልጣን ወይም የሕዝብ አደራ ያላአግባብ የተገለገለ እንደሆነ፤
ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ ለመንግስት ወይም ለሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ የማይገባ ጥቅም ለመስጠት ቃል የገባ፤ ያቀረበ፤ የሰጠ ወይም ለማቅረብ የተስማማ እንደሆነ፤ ወይም በአግባቡ ለተፈጸመ ወይም በአግባቡ ለወደፊት ለሚፈጸም የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም የመንግሰት ልማት ድርጅት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሥራ የማይገባ ጥቅም ለማንኛውም ሰው የሰጠ ወይም ከማንኛውም የመንግስት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ የተቀበለ እንደሆነ በሙስና ወንጀል ፈጻሚነት ተጠያቂ ይሆናል በማለት ይገልጻል፤ (በአዋጁ አንቀጽ 4(2))::
ሙስና ወንጀልን በተመለከተ በቀጥታ ትርጉም የሚያስቀምጥ ሳይሆን ምን አይነት ድርጊት ሲፈጸም በሙስና ወንጀል ሊያስቀጣ እንደሚችል የሚገልጹ ናቸዉ:: ሆኖም ሙስና ከሌሎች ወንጀሎች የራሱ የሆነ ልዩ ባህርይ ያለዉ በመሆኑ በአዋጅ የተለያየ ድርጊቶችን የሙስና ወንጀል በማድረግ በሕጉ ተደንግጎ ይገኛል:: የተሻሻለው የፀረሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 2(1)(1) የሙስና ወንጀል ማለት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 የተሰጠው ትርጓሜ እንደሚኖር ይገልጻል፣ የመስና ወንጀሎች ማለት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 የተጠቀሱት የሕግ ድንጋጌዎችን በመጣስ የሚፈጸም ወንጀል ነው፡
ሐ/ የሙስና ወንጀሎች ልዩ ባህሪያት
- ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት በተመለከተ በሙስና ወንጀል ፈጻሚነት የሚጠየቁት የመንግስት መስሪያ ቤት፤ የመንግስት ልማት ድርጅት እና የሕዝባዊ ድርጅት ሥራ ጋር በተያያዘ በሕጉ የተጠቀሱ ድርጊቶችን በመተላለፍ የሚፈጽም የመንግሰት ሰራተኛ ወይም ኃላፊ ወይም ከእነዚህ ተቋማት ጋር በተያያዘ የሕጉ ድንጋጌ የተላለፈ ማንኛውም ግለሰብ የሚመለከት ነው::
ሕዝባዊ ድርጅት ሲባል በማንኛውም አግባብ ከአባላት ወይም ከሕዝብ የተሰበሰበ ወይም ለሕዝባዊ አገልግሎት ታስቦ የተሰበሰበ ገንዘብ ንብረት ወይም ሌላ ሀብትን የሚያስተዳድር አካልንና አግባብነት ያለውን ኩባንያ የግል ዘርፍ የሚያካትት ሲሆን፤ የሃይማኖት ድርጅትን የፖለቲካ ፓርቲን የዓለም አቀፍ ድርጅትን እና እድርንና ተመሳሳይ ባሕላዊ ወይም ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ማኅበርን አያካትትም::
- ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ወይም ጉዳት ለማድረስ በማሰብ የሚፈጸም መሆኑ፤ የሙስና ወንጀሎች ሕግን በመተላለፍ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በአብዛኛው የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት የሚፈጸሙ ናቸው:: የማይገባ ጥቅም ማለት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ወይም አግባብ ባልሆነ መንገድ የተገኘ ጥቅም ማለት ነው (በአዋጁ አንቀጽ 2(14))::
2.1 ጥቅም በተመለከተ በአዋጁ አንቀጽ 2(13) ጥቅም ማለት የሚከተሉትን ይጨምራል፤
1ኛ. በገንዘብ ወይም በማናቸውም ዋጋ ባለው መያዣ ወይም በሌላ ንብረት ወይም በንብረት ላይ ያለን ጥቅም (መብት)፤ 2ኛ. ማንኛውንም ሹመት፣ ቅጥር፣ ወይም ውል 3ኛ. ብድርን ግዴታን ወይም ማናቸውንም ዕዳ በሙሉም ሆነ በከፊል መክፈልን ማስቀረትን ማወራረድን ወይም ከእነዚህ ነገሮች ነጻ ማድረግን፤ 4ኛ. ከተመሰረተ ወይም ካልተመሰረተ የአስተዳደር፣ የፍትሐብሔር ወይም የወንጀል ክስ ወይም ካስከተለዉ ወይም ከሚያስከትለው ማናቸውም ቅጣት ወይም የችሎታ ማጣት በማዳን ወይም ይህን በመሰለ ዘዴ የሚደረግን አገልግሎት ወይም ውለታ
5ኛ. ማናቸውንም መብት ወይም ግዴታ መፈጸምን ወይም ከመፈጸም መታቀብን፤ 6ኛ. ከተጠቀሱት ውጭ በገንዘብ የማይተመን ማናቸውንም ሌላ ጥቅም ወይም አገልግሎት፣ እና ከተጠቀሱት ውጭ በገንዘብ የማይተመን ማናቸው ሌላ ጥቅም ወይም አገልግሎት፤ እና ከተጠቀሱት ጥቅሞች አንዱን ማቅረብን፤ ጥቅሙ የሚገኝበትን መንገድ ማመቻቸትን ወይም ይሄንኑ በሚመለከት የተስፋ ቃል መግባትን ወይም መቀበልን ያካትታል::
2.2 የሶስተኛ ወገን ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ መሆኑ፤
የሙስና ወንጀል የሚፈጸመው ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ብቻ ሳይሆን በሚሰራበት የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም ሕዝባዊ ድርጅትን ጥቅም ወይም መብት ወይም የሌላ ግለሰብ ጥቅም ወይም መብት ላይ ሕጉን በመተላለፍ ጉዳት ከደረሰ ጥቅም ባያገኝም በሙስና ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል::
-
ጥቅም የማግኘት ወይም ጉዳት የማድረስ ሀሳብ በሕግ ግምት የሚወሰድ ስለመሆኑ፤
ተቃራኒ ማስረጃ ካልቀረበ በስተቀር የሙስና ወንጀሉ የተፈጸሙት የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ወይም ሌላውን ሰው ለመጉዳት መሆኑ በተደነገገ ጊዜ በድንጋጌው የተመለከተው ግዙፋዊ ፍሬ ነገር መፈጸሙ ከተረጋገጠ ድርጊቱ የተፈጸመው ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም ሶስተኛ ወገንን መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት እንደሆነ ይገመታል:: በሕጉ መሰረት ክስ የቀረበበት ሰው የሙስና ወንጀል በመተላለፍ የፈጸመው ግዙፋዊ ነገር ወይም ድርጊቱ ከተረጋገጠ፤ ያደረሰው ጉዳት ወይም ያገኘው ጥቅም አስበው እንደሆነ ሕጉ ግምት ይወስዳል:: ሆኖም በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰው በሌላ ማስረጃ የቀረበበት ክስ ማስተባበል ይችላል::
- በሕግ አግባብ ለተሰራው ሥራ ጥቅም መቀበል ወይም መስጠት በሙስና ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ ሌላ ልዩ ባህሪይ ነው:: ማንኛውም የመንግስት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ በሕግ የተጣለበት ግዴታ ከመፈጸሙ በፊት ይሁን ከፈጸመ በኋላ ጥቅም ያገኘ እንደሆነ በሕጉ የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል ያስጠይቃል:: በተመሳሳይ ሁኔታ ግዴታውን ለተወጣው ሰራተኛ ጥቅም የሰጠ ማንኛውም ግለሰብ በሙስና ወንጀል ያስቀጣል::
- በሙስና ወንጀል ልዩ በሚያደርገው ተጎጂ መንግስት ወይም ሕብረተሰቡ መሆኑ ወይም የአክሲዮን ባለቤቶች መሆናቸው ነው:: ምንም እንኳን ጉቦ መስጠት አይነት ጉዳይ የግለሰብ ተጎጂ ሊኖር የሚችል ቢሆንም በሙስና ወንጀል ቀጥታ ተጎጂ የሚሆነው አብዛኛው ማኅበረሰቡ ነው::
ሙስና ውስብስብ ከሚያደርጉት አንዱ ቀጥተኛ ተጎጂ ግለሰብ ባለመኖሩ ምርመራ፤ ክስ እና የፍርድ ሂደት አስቸጋሪ ያደርገዋል:: ሌላው ጥቅም ሰጪ ይሁን ጥቅም ተቀባይ በስምምነት የሚፈጸሙ በመሆኑ የምርመራም ሆነ የክስ ሂደት አስቸጋሪ ያደርጋል:: ስለሆነም ሕብረተሰቡ የሙስና ድርጊት ሁሉንም ሕብረተሰብ የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ መስናን በመዋጋት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት::
በአጠቃላይ ወንጀል ለማለት ድርጊትን የሚከለክል ሕግ፤ የተከለከለ ድርጊት፤ መጾምንና በሕግ የተከለከለ ድርጊት የፈጸመበት የሀሳብ ክፍልን በአንድነት ተሟልቶ ሲገኝ ስለመሆኑ ተገልጧል::
የሙስና ወንጀል በሙስና ወንጀል ሕጉ የሚከለከሉ ተግባራት የገለጸ ሲሆን የሀሳብ ክፍል በተመከለተ በሕግ ግምት የሚወሰድ ነው:: የተከለከለ ተግባራት በሕጉ ከተደነገጉት መካከል ስልጣን አለአግባብ መገልገል፤ የመንግስት ሥራ በማይመች አኳኋን መምራት፤ ጉቦ መስጠት ወይም መቀበል እና ሌሎች ይገኛሉ::
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም