የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ በተያዘው በጀት ዓመት የስድስት የጭነት መርከቦች የግዢ ሂደት በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ አመልክቷል። የእነዚህ መርከቦች ግዥ እያደገ የመጣውን የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ ለማሳለጥ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስታውቋል።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ ? በአሁኑ ወቅትስ ያለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ለሚሉት እና ሌሎችም ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡን የተቋሙን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፤- የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አመሰራረት የተቋቋመበት ዓላማ ምንድን ነው ?
ዶ/ር በሪሶ፤- ተቋሙ የተቋቋመበትን ዓላማ ከማንሳቴ በፊት ስለ አመሰራረቱ ትንሽ ልግለጽ። የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ፤ በሎጀስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ በተናጠል ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን ሶስት ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አክስዮን ማሕበር፣ የባሕርና ትራንዚት አገልግሎት ድርጅትና የደረቅ ወደብ አግልግሎት ድርጅቶችን በማዋሀድ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 255/2004 የተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው። መስከረም 2007 ዓ.ም ደግሞ የቀድሞው ኮሜት ትራንስፖርት አክሲዮን ማሕበር ድርጅቱን ተቀላቅሏል::
የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት መጋቢት አንድ ቀን 1956 ዓ.ም በብር 50,000 (ሃምሳ ሺ) መነሻ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን ይህ ዕለት ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ነበር ማለት ይቻላል::
የንግድ መርከብ ሲቋቋም የአሜሪካው ታውረስ ኢንቨስትመንት 51 ከመቶ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የገንዘብ ሚኒስቴር ደግሞ 49 በመቶ ድርሻ ነበራቸው:: መጋቢት 18 ቀን 1956 ዓ.ም የድርጅቱ ካፒታል ወደ 375,000 (ሶስት መቶ ሰባ አምስት ሺ) ብር እንዲያድግ ተደረገ:: በዚህ ጊዜም ነበር የመጀመሪያዎቹ ሶስት መርከቦች ማለትም ንግስተ ሳባ፣ የይሁዳ አንበሳ እና ላሊበላ የተባሉት መርከቦች የተገነቡት::
በዚህም መሰረት ድርጅቱ በእነኚህ ሶስት መርከቦች በ1958 ዓ.ም ሥራውን በይፋ ጀመረ:: ድርጅቱ በ1959 ዓ.ም፣ በ1960 እና በ1961 ዓ.ም በተከታታይ አዱሊስ፣ ጣና ሐይቅ እና አሸንጌ የተባሉትን ተጨማሪ መርከቦች በመግዛት በአስተማማኝ መሰረት ጉዞውን አጠናክሮ ለመቀጠል ችሏል::
የባሕር ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት ከውህደት በፊት ያለውን ታሪክ ስናይ፤ የገቢና ወጪ ንግድ ዝውውርን ለማቀላጠፍ ሚያዚያ 1960 ዓ.ም በ500,000 ብር መነሻ ካፒታል ነበር የተቋቋመው:: ድርጅቱ የሀገራችን ገቢና ወጪ እቃዎች ሲስተናገዱ በነበሩባቸው ወደቦች ሁሉ በመገኘት ሀገራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል:: ድርጅቱ ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በፊት በዋናነት ከወደብ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶቹን በአሰብ ወደብ በኩል ሲያከናውን ነበር።
የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ተከትሎ የሀገራችን ገቢና ወጪ እቃዎች በሙሉ በጅቡቲ ወደብ በኩል ማስተናገድ ሲጀመር፤ ራሱን በወደብ መሳሪያዎች፣ በሰው ኃይልና በአሰራር በማደራጀት ከባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን ይሰጥ ነበር:: ድርጅቱ በዋናነት ዕቃዎችን ከመርከብ የማውረድና የመጫን አገልግሎት፣ ዕቃዎችን በባሕር ወደብ አመች በሆነ ቦታ ወይም መጋዘን በጊዜያዊነት አደራጅቶ የማቆየት ሥራዎች፣ የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎትና የትራንዚት ሥራዎችን ለበርካታ ዓመታት ያከናውን ነበር::
የደረቅ ወደብ አገልግሎትን ስንመለከት፤ በወቅቱ በአገሪቱ የሚካሄደው የወጪና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ አብዛኛው የሚስተናገደው በጅቡቲ በኩል ብቻ ነበር። በመሆኑም ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለውን የወደብ መጨናነቅና ወደሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች በወደብ ለይ የሚኖራቸውን የረጅም ጊዜ ቆይታ መቀነስ አስፈላጊ ነበር።
ይህንን ችግር ለማቃለል ብሎም ለዚህ አገልግሎት እየዋለ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ እንዲቻል በአገሪቱ ክልል ወሰን ውስጥ የደረቅ ወደብ አገልግሎት ማቋቋም ያስፈልግ ነበር። ይህም በመንግስት በመታመኑ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 136/1999 መሰረት የደረቅ ወደብ አገልግሎት ድርጅት እንዲቋቋም ተደረገ:: ድርጅቱ ከጥር ወር 2000 ዓ.ም ጀምሮ ቢሮ የማደራጀትና መዋቅር የማዘጋጀት፣ የሰው ኃይል የማሟላት፣ እንዲሁም የተለያዩ መመሪያዎችን በመቅረፅ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቶ በ2001 ዓ.ም ሥራውን ጀመረ::
የኮሜት ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር፤ በደንብ ቁጥር 193/86 የተቋቋመና በዋናነት በትራንስፖርት ዘርፍ እና ሌሎች ተጓዳኝ የልማት ሥራዎች ብዙ ተወዳዳሪዎች ባሉበት የኢኮኖሚ ዘርፍ የሚገኝ ተቋም ነው:: ተቋሙ በተሰማራበት የንግድ ዘርፍ መስክ ውድድሩን በመቋቋም አትራፊ በመሆን ሕልውናውን አስጠብቆ የቆየ አንጋፋ ድርጅትም ነበር::
አዲስ ዘመን ፦ ተቋማቱ ን ወደ አንድ በማምጣት ማንቀሳቀስ ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነበር ?
ዶ/ር በሪሶ ፦ በወቅቱ በሀገሪቱ ከነበረው ኢኮኖሚያዊ እድገት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሥርዓት መገንባት አስፈላጊነቱ የሚያጠያይቅ አልነበረም። በመሆኑም እነዚህ በተናጠል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተቋማት መቀናጀት ተገቢ ስለነበር በተደረገው ከፍተኛ የመንግስት ድጋፍና ውሳኔ በባሕርና ሎጀስቲክስ ዘርፍ በተናጠል ሲንቀሳቀሱ የቆዩትን ድርጅቶች በ2004 ዓ.ም ለማዋሃድ ተችሏል። የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (ኢባትሎ) የሚል ስያሜ በመያዝ በሶስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ስራውን ጀመረ:: በዚህ ሁኔታ እየሰራ ከቆየ በኋላ በሚያዚያ 2008 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የመቋቋሚያ ካፒታሉ ከነበረበት ሶስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ወደ ሀያ ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ተደርጓል::
አዲስ ዘመን ፦ ተቋሙ እንዲያከናውን የተሰጡት ተግባራትና ኃላፊነቶች ምን ምን ነበሩ ?
ዶ/ር በሪሶ ፦ ተቋሙ የተሰጠው ኃላፊነት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ቁልፍ ሚና ያላቸው ናቸው ለማለት ይቻላል። ዝርዝር ለማድረግ ያክል፤ በጠረፍ አካባቢ፣ በዓለም አቀፍ ባሕሮች እና በሀገር ውስጥ የውሃ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት፤ የዕቃ አስተላላፊነት ውክልና፤ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት፤ የመርከብ ውክልና እና የአየር ውክልና አገልግሎት መስጠት፤ ለወጪና ገቢ ዕቃዎች የስቴቭዶሪንግ፤ ሾር ሃንድሊንግ፤ የወደብ፤ የመጋዘን እና ሌሎች የሎጀስቲክስ አገልግሎቶች መሰጠት፤ የኮንቴይነር ማስተናገጃና ማከማቻ አገልግሎት መስጠት፤ የወደብ ይዞታዎችን ማልማት፤ ማስተዳደርና አገልግሎት መስጠት፤ የማሪታይም ዘርፍ የሙያ ክህሎት ማሳደጊያ የሰው ኃይል ልማትና ስልጠና ማዕከል ማቋቋምና ማስተዳደር፤ የሃገሪቱን የገቢና የወጪ ንግድ ፍላጎት በማጥናት የማሪታይምና ትራንዚት ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን ብቃት ለማጎልበት የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ፤ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ የሆኑ ሥራዎችን ማካሄድ ናቸው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተቋሙ እንዲያከናውነው ከተሰጠው ተልዕኮ መካከል የሀገር ውስጥ የውሃ ትራንስፖርትን ማስፋፋት አንዱ ነው። በዚህም ረገድ የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅትን ከሕዳር ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከክልሉ መንግስት የልማት ድርጅት በመረከብ ውህደቱን ወደ አምስት አድርሶታል:: ይህ የሀገር ውስጥ የውሃ ትራንስፖርት ጅማሮም ጣና ሐይቅ ላይ ብቻ ሳይሆን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ ባሮ፣ አባያ እና ሌሎች ለውሃ ትራንስፖርት አመቺነት ባላቸው ስፍራዎች ሁሉ በማስፋፋት ረገድ ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት ነው። በዚህ ረገድም በቀጣይ የሚከናወኑ በርካታ ሥራዎች ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን፦ባለፉት ዓመታት እንደ ተቋም ከተያዘው አቅድ አኳያና እንደ ሀገር ከታሰበው አንጻር ምን ያህል ውጤታማ መሆን ተችሏል ?
ዶ/ር በሪሶ ፦ ምን ያህል ወጤታማ ሆኗል ? የሚለውን ለመገምገም በቅድሚያ የተቋቋመበትን ዓላማ ማየቱ ተገቢ ነው። የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ዕድገት ለመደገፍ የሎጀስቲክስ አቅርቦቱን ዘመናዊ፤ ቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆን ለማድረግ ጠንካራና ብቃት ያለው የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተቋቋመ የልማት ድርጅት ነው:: ከዚህ አኳያ ድርጅቱ በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ መስክ የሚሰጣቸውን ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች በዕቅድ በመምራት የተሳካ አፈጻጸም እያስመዘገበ ነው ለማለት የሚያስደፍሩ ሥራዎችን ለማከናወን ተችሏል::
ባለፉት አራት ዓመታት ድርጅቱ ባከናወናቸው ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች በአንፃራዊነት ሲታይ አመርቂ ናቸው። ለዚህም እንደ ማሳያ ያለፉትን አራት ተከታታይ ዓመታት የገቢ መጠን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል። ዓመታዊ የገቢ መጠን በ2013 ዓ.ም. 29 ነጥብ 80 ቢሊዮን ብር፤ በ2014 ዓ.ም. 51 ነጥብ 38 ቢሊዮን ብር፤ በ2015 ዓ.ም. 42 ነጥብ 73 ቢሊዮን ብር፤ በ2016 ዓ.ም 57 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር በላይ ዓመታዊ ገቢ አግኝቷል። በተመሳሳይ ለውጤታማነቱ አንዱ ማሳያ የሚሆነውን የጭነት መጠንም ያለፉትን አራት ዓመታት
ስንመለከት፤- በባሕር የተጓጓዘ ገቢ ጭነት በ2013 ዓ.ም. 4,814,206 ቶን፤ በ2014 ዓ.ም. 3,616,343 ቶን፤ 2015 ዓ.ም 2,965,542፤ እንዲሁም በ 2016 ዓ.ም ከአራት ሚሊየን 590 ሺህ ቶን በላይ የጭነት አገልግሎት ማከናወን ተችሏል።
በዚህ ረገድ በተለይም በ2016 በጀት ዓመት በርካታ ዓለማቀፍና አገር አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል። እነዚህን ችግሮች በመቋቋም ከላይ የተዘረዘሩትን ስኬቶች ማስመዝገብ ችሏል። ብሎም ሌሎች ተግባራትንም በማከናወን በበጀት ዓመቱ በእቅድ የተቀመጡትን በአግባቡ ለማጠናቀቅ መብቃቱ እንደ ትልቅ ስኬት የሚወሰድ ነው።
አዲስ ዘመን፤- የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ለአጠቃለይ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት የሚኖረው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል ?
ዶ/ር በሪሶ፤- ተቋሙ አጠቃላይ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለመፈተሽ በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰቱ ያሉ ነገሮችን ማየትም ተገቢ ነው። ዓለማችን ከሁለት ዓመታት በላይ ከቆየው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ኢኮኖሚያዊ ጫና ሳትላቀቅ እና ከአንድ ዓመት በፊት የተቀሰቀሰው የእስራኤል ሐማስ ጦርነት በመካከለኛው ምስራቅ አጠቃላይ የንግድም ሆነ የመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል።
በየመን የሁቲ ታጣቂዎች በጦርነቱ ለሐማስ ድጋፍ ለማድረግ በሚል የንግድ መርከቦች በኤደን ባህረ-ሰላጤ እንዳይንቀሳቀሱ ጥቃት በማድረስ ላይ ይገኛሉ:: በዚህ ምክንያት የምርቶች እንቅስቃሴ በጉልህ የተስተጓጎለበት ወቅት ከመሆኑም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለብዙ አገራት ፈተና የሆነ ከፍተኛ የዋጋ ንረትም ተፈጥሯል:: ይህም ከባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ጋር ያለው ተዛምዶ ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን ኢባትሎም ሆነ በዘርፉ የተሰማሩ ግዙፍ ዓለማቀፍ ተቋማት የተፈተኑበት ክስተት ሆኖ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል::
በሌላ በኩል የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ ባለበት በዚህ ወቅት ለአጭር ጊዜ ቀንሶ የነበረው የኮንቴነር ማጓጓዣ ዋጋ በእጅጉ እየጨመረ ይገኛል:: እነዚህና መሰል ዓለማቀፋዊ ተጽኖዎች ለመቋቋም የሎጀስቲክስ አቅምን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሰፊ ጥረቶች በተቋም ደረጃ ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን ከነዚህም መካከል የድርጅቱን በባሕር የማጓጓዝ አቅም ለማሳደግና በቀጠናው ያለውን ድርሻ ለማሻሻል ግዙፍ መርከቦች ለመግዛት ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል:: ከዚህ በተጨማሪም የ205 ከባድ ተሽከርካሪዎች ግዢ ለማከናወን በእቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል::
የደረቅ ወደቦችን አቅም ከማሳደግ አኳያ ነባር ወደቦችን የማስፋፋት ሥራዎች ተከናውነዋል፤ የድርጅቱን አደረጃጀት በማሻሻል የመዋቅር ጥናት አጸድቆ እንዲተገበር አድርጓል:: እነዚህንና ሌሎች መሰል የተጀመሩ ጥረቶች ከግብ ለማድረስ ኢባትሎ በ2017 በጀት ዓመት የተለያዩ ኢላማዎችንና እነዚህን ዒላማዎች ለማሳካት የሚረዱ ዝርዝር ተግባራትን ለመፈፀም የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅቷል::
ይህ እቅድ ሲዘጋጅ ከአገራዊ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ጋር በማዛመድ ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባር ላይ የሚውል የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ (2016 ዓ.ም እስከ 2020 ዓ.ም) መነሻ የተደረገ ሲሆን በዚሁ አግባብ የ2017 በጀት ዓመት የኦፕሬሽንና የፋይናንስ ዕቅድ ተዘጋጅቶ በስራ አመራር ቦርድ እንዲጸድቅ ተደርጓል::
የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ስራውን በጀመረበት ዓመት ዓመታት ብሎም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበረው አቅም ሲታይ መርከቦች የነበራቸውን ከሶስት ሺህ እስከ 18ሺ የመጫን አቅም እያሳደገ በመምጣት ከ28 ሺህ እስከ 63 ሺ ቶን የመጫን አቅም ያላቸው መርከቦች ባለቤት ለመሆን በቅቷል:: አሁን ላይ ድርጅቱ ስምንት የደረቅ ወደብና ተርሚናሎች አሉት፣ በተጨማሪ በቂ የወደብ መሳሪያዎች እና ብዙ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ያሉት ሲሆን፤ ተደራሽነቱ እና ጭነት የማንሳት አቅሙም ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መጥቷል::
በተጨማሪም ተቋሙ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋትም የላቁ ውጤቶችን እያስመዘገበም ይገኛል:: ዛሬ ላይ እየሰጣቸው ያሉ የአገልግሎት አይነቶችንም ስንመለከት በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የሀገሪቷን ገቢና ወጪ ጭነቶች በብቸኝነት በማጓጓዝ ለአስመጪና ላኪዎች የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት የሚሰጥ መንግስታዊ ተቋም ነው:: ይህም ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ በግልጽ የሚያመላክት ነው።
አዲስ ዘመን ፤- የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የተቀመጠለትን ዓላማ ከማሳካት አኳያ በሰው ሀብት እና በሌሎች ግብአቶች ያለበት ሁኔታ እንዴት ይገለጻል ?
ዶ/ር በሪሶ ፤- የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ከ 3000 በላይ ቋሚ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን እነዚህ ከባሕር እስከ የብስ በላቀ ትጋትና በእረፍት የለኝም መንፈስ ስራቸውን የሚያከናውኑ ናቸው:: ተቋሙ እነዚህን ሰራተኞች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃትና በታማኝነት እንዲወጡ ለማስቻልም በየወቅቱ አስፈላጊውን ስልጠና፤ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ይገኛል። በግብዓት ረገድም ቢሆን ኢባትሎ ከሀገራዊ ድርጅቶች ጋር በአንጻራዊነት ሲታይ በተሻለ ደረጃ ሆነው ከሚታዩት መካከል ነው ለማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን ፤- የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ በዘርፉ ዓለም ከደረሰበት አኳያ ያለው አቅም እንዴት ይታያል ? ሌሎች ሀገራት ወደ ደረሱበት ደረጃ ለማሸጋጋር ምን እየተሰራ ነው ?
ዶ/ር በሪሶ፤- በመሰረቱ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ተወዳዳሪነቱና ተፎካካሪነቱ ሀገር ውስጥ ካሉ ድርጅቶች ጋር አይደለም:: ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ካተረፉት እንደ Maersk, Mediterranean Shipping Company (MSC), COSCO Shipping Corporation, CMA CGM Group እና Hapag-Lloyd ከመሳሰሉት ጋር ነው:: በእርግጥ እነዚህ በሰው በሃብት ኃይል አደረጃጀት፣ በሃብት ምጣኔ እና በአገልግሎት ስፋትም ከፍታ ላይ ያሉ ናቸው::
ይሁን እንጂ ብዙዎች በአህጉሪቱ ያሉ ስመጥር የመርከብ ድርጅቶች ከዘርፉ ተደነቃቅፈው እና በግዙፎቹ ተውጠው እንደመውጣታቸው የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሃብት የሆኑት መርከቦቻችን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፈው ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት የራሳቸውን ባንዲራ እያውለበለቡ በኩራትና በክብር 345 የወደብ መዳረሻዎች ላይ ማገልገል መቻላቸው እንደ ትልቅ ድል የሚቆጠር ነው:: ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ድርጅቱ አቅሙ እንዲያድግና በስመጥርነቱ እንዲቀጥል የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተዘጋጅቶ በቅርቡ በአገልግሎት ስፋትና በአሰራር ጥራት ላይ ተመስርቶ ወደ ልሕቀት ያመራ ዘንድ የሚያስችለው ሥራ እየተሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ፤- የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፍ ለሙስና ተጋላጭ እንደሆነ ይነሳል ይህንን ለመቅረፍ እንደ ተቋም ምን ምን ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ?
ዶ/ር በሪሶ ፤- የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ለሙስና ተጋላጭ ስለመሆኑ እንደሚነሳ አሁን ከእናንተ እየሰማን ነው:: በድርጅቱ ውስጥ ሥራዎች የሚከናወኑት ሕጋዊ መርህና አሰራር ተከትሎ ነው:: ይህም ሆኖ ለሙስና ሊያጋልጡ ይችላሉ ብለን የሰጋንባቸውን ከባቢዎች በዘመናዊ አሰራር ታግዘን (አሰራራችንን ዲጂታላይዝ) እየሰራን እንገኛለን:: ምንም እንኳ የዲጂታላይዜሽን ሥራችን በተወሰነ መልኩ ያልተጠናቀቀ እና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ቢሆንም በአስጊ ደረጃ ለሙስና ተጋላጭ የሚያደርጉ አሰራሮች የሉም:: ይሁንና ሙስና በባህሪው ከሁኔታዎችና ከአሰራሮች ጋር የሚለዋወጥ በመሆኑ አሰራሮችን በማዘመንና ግልፀኝነት በማስፈን ሥራዎች እንዲከናወኑ ማድረግ ላይ በተቋሙ የሥነምግባር ክፍል አማካይነት የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፤- በቅርቡ የጭነት መርከቦች ግዢ እንደሚፈጸም ተገልጿል እነሱን ቢያብራሩልን? በተጨማሪ የእነዚህ መርከቦች ወደ አገልግሎት መግባት የሚኖረው ፋይዳና የሚያመጣው ለውጥ ቢገለጽ ?
ዶ/ር በሪሶ ፤- የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ቀደም ሲል የመጫን አቅማቸው 27 ሺህ ቶን የሆነ ዘጠኝ መርከቦችና አንድ ዓባይ ሁለት የተሰኘች 63 ሺህ ቶን የምትጭን ግዙፍ አልትራማክስ መርከብ ባለቤት ነው:: አሁን ደግሞ በተያዘው የበጀት ዓመት ሁለት 62 ሺህ ቶን የመጫን አቅም ያለው አልትራማክስ መልቲፐርፐዝ መርከብ፣ ሁለት ከ 3000-4000 ቲኢዩ ኮንቴይነር የመጫን አቅም ያላቸው መርከቦች፣ እና ሁለት አልትራማክስ 63 ሺህ ቶን የሚጭኑ የደረቅ ጭነት መርከቦች በአጠቃላይ ስድስት መርከቦች ግዥ በሂደት ላይ ይገኛል:: እነዚህ ስድስት መርከቦች ወደስራ ሲገቡ አጠቃላይ የመርከቦቻችንን ቁጥር ወደ 16 ያደርሰዋል:: ይህ ማለት 94 በመቶ የሚደርሰውን የሀገሪቱ የወጪ ገቢ ጭነት ከማሳለጥ አኳያ ዓይነተኛ ሚና የመጫወት ዕድሉን ከፍ ያደርገዋል::
አዲስ ዘመን ፤- የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ በቀጣይ እንደ አጠቃላይ ምን እቅድ ይዟል? መዳረሻውስ ምንድን ነው ?
ዶ/ር በሪሶ ፤- ተወዳዳሪ የሺፒንግና የሎጀስቲክስ አገልግሎት በማቅረብ በ2022 ዓ.ም ተመራጭና ስመጥር አፍሪካዊ ተቋም የመሆን ራዕይን ይዞ እየሰራ ያለው ድርጅታችን በቀጣይ የዲጂታል አሰራርን ሙሉ በሙሉ መተግበር የመርከቦቹን እና የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎቹን ቁጥር መጨመር፣ የሀገር ውስጥ ወደብና ተርሚናሎችን ማዘመን እና ማስፋፋት፣ የተሽከርካሪዎቹን እና የወደብ መሳሪያዎችን ቁጥር መጨመር እና ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱን ማስፋት ለአብነት የሚጠቀሱ ቀጣይ ዕቅዶቹ ናቸው::
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም