አዲስ አበባ፡- አገራዊ አንድነት በሚፈለገው መልኩ ከብሔራዊ ማንነት ጋር ተሳስሮ አለመተግበሩና አለመጎልበቱ የፌዴራል ሥርዓቱ አገራዊ አንድነትን ጠብቆ እንዳይጓዝና ልዩነቶች እንዲሰፉ ዕድል መስጠቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም አስታወቁ።
13ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ትናንትና በአዲስ አበባ ስታዲየም በተከበረበት ወቅት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵ ያውያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በአስተሳሰብ የተለዩ ቢሆንም በአንዲት የጋራ ጎጆ ክፉና ደጉን በጋራ አሳልፈዋል። ሆኖም ብሔራዊ ማንነት ከአገራዊ አንድነት ጋር ተሳስሮ በሚፈለገው መልኩ አለመተግበሩ የፌዴራል ሥርዓቱ አገራዊ አንድነቱን ጠብቆ በመሄድ ረገድ ውስንነት እንዲኖርበት አድርጓል።
እንደ ወይዘሮ ኬሪያ ገለጻ፤ አገራዊ አንድነትን ማጎልበት ላይ ባለመሰራቱም የሚያቀራርቡና አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮች እንዳይሰፉ ከማድረጉም በላይ ልዩነቶች ብቻ እንዲሰፉ ዕድል ሰጥቷል። እርስ በርስ በጥርጣሬ ዓይን እንዲተያዩ፣ ብሔራዊ ማንነቶች ወደ ውድድር ገብተው የብሔር ጥላቻ ስር እንዲሰድ አድርጓል። ብሔራዊ ማንነት ያለ ኢትዮጵያዊ አንድነት፤ ኢትዮጵያዊ አንድነት ደግሞ ያለ ብሔራዊ ማንነት ማጉላት አይቻልም። ስለሆነም የሚያዋጣው ሁለቱንም ማንነቶች ሳይጣረሱ፣ ሳይዛነፉና ሳይንኳሰሱ ሚዛኑን ጠብቆ ማስኬድ ነው።
ማንኛውም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ሙሉ መብት ሲረጋገጥ የየራሱን አጥር ገንብቶ፤ ብዙ አዳዲስና ጥቃቅን አገር ለመፍጠር አለመሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ኬሪያ፤ መብቱ እኩልነት ለማጎናጸፍ የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ማንኛውም ሕዝብ የሁሉም ወዳጅ እንጂ ጠላት እንዳልሆነ ማመን፣ አንዱ ያለ አንዱ መኖር እንደማይችል መቀበል ያስፈልጋል። በማህበረሰቡ ውስጥ ተጋጭተው የሚያጋጩት ሰዎችን አስተሳሰብና ተግባር መግታት፣ከዚያ ካለፈ ደግሞ ስጋዬ ናቸው በሚል ካባ አልብሶ እንደ ዋሻ መደበቅ ሳይሆን በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ ይገባል። ማንንም ሰው በሚያራምደው ሃሳብ እንጂ በማንነት መመዘን አይገባም። ይልቁንም ያሉትን መልካም ዕድሎች በማጉላት የአገሪቱን ሁኔታ መቀየር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ያስፈልጋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ታላቅ አገር የመገንባት ህልምን እውን ለማድረግ ከሰላምና አብሮ መኖር ውጪ አማራጭም ሆነ አቋራጭ የለም። አገሪቱ ከድህነት ለማላቀቅና አድጋ መስመር እንድትይዝ ለማድረግ ልዩነቶችን ከሚያሰፉ አስተሳሰቦች መላቀቅ ይገባል። በዓለም ደረጃ መሰረታዊ የልማት ግቦች ከተባሉትና አገሪቱም ከፈረመችው ውስጥ አንዱ ማንም መንግሥት ሆነ የህብረተሰብ አካል ብቻውን አገርን ማበልጸግ አይችልም ነውና አገሪቱም ይህንን አምና መስራት ይኖርባታል።
የመቻቻል ሁኔታ ልዩ ትኩረት ሊያገኝ እንደሚገባ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቷ፤ አለመቻቻል በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ነው። ስለ መቻቻል መናገር ብቻውን ተግባር ሊሆን አይችልምና በመናገር ውስጥ ትርጉም ያለው ሥራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል። ሁሉም በአገር ጉዳይ ላይ ይመለከተኛል፣ ድርሻ አለኝ ሊል ያስፈልጋል ብለዋል።
በዓል ማክበር ጥሩ መሆኑንም ገልጸው፣ በበዓሉ ግንኙነት ይጠነክራል፣ ብዙህነት ይሰበካል፣ ምን ያህል ሀብት እንዳለም ይታያልና በየዓመቱ እየተገናኙ ማክበር ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ የሚሰራና የሚተገበር መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ቀኑ የኢትዮጵያ ከፍታ የሚታይበት ነው። በተለይ በለውጥ ጎዳና ላይ ሆኖ የመደመርን ብስራት የምናሳይበት ጊዜ በመሆኑ ለየት ያደርገዋልና ይህንን መጠቀም ይገባል። የፈረሱትን የኢትዮጵያ አንድነት ቅጥሮች የሚጠገንበት፣ ባህላችን የሚገነባበት ማድረግም ያስፈልጋል።
‹‹ኢትዮጵያውያን ባህላችንን ለመጠበቅ የአባትና እናቶችን ፈለግ መከተል ላይ ማተኮር አለብን›› ያሉት ኢንጅነር ታከለ፤ አገራዊ አንድነትንና አብሮነትን መንከባከብ የተረካቢው ኃላፊነት ስለሆነ ግጭትን ወደኋላ ጥሎ አንድነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። አንድነትንና አብሮነትን ከሚያጠለሹ ችግሮች ወጥቶ አገራዊ ዕድገት ላይ ማተኮርም እንደሚገባ ገልጸዋል።
አሁን እየመጣ ያለው ለውጥ ከግብ እንዲደርስ እስካሁን ከተከፈለው የበለጠ መስዋዕትነት፣ ካለፈው የበለጠ ዳገት አለው ያሉት ኢንጅነር ታከለ፤ ቅንነትንና ታማኝነትን ገንዘብ አድርጎ ማለፍ ከምንጊዜም በላይ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። በአገሪቱ የእኔ ብቻ ባይነት፣ ግለኝነት፣ የግል ጥቅምን ወደ ወል በማምጣት ህዝቦች እንዲወናበዱ እያደረገ በመሆኑ መላው የአገሪቱ ህዝብ የተሰጠን የተፈጥሮ ፀጋ እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ ነገን አሻጋሪነት በመመልከት ለትግበራው መነሳት እንዳለበት አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው