ካንሰር በአለማችን እጅግ አስቸጋሪና ህይወት ቀጣፊ እየሆኑ ከመጡ በሽታዎች ውስጥ አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወጡ አለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የካንሰር ህመም በአሁኑ ወቅት ኤች አይቪ ኤድስ፣ሳምባ ነቀርሳና የወባ በሽታዎች በጋራ እያደረሱ ካሉት ሞት በላይ የሰዎችን ህይወት በከፍተኛ ደረጃ እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ በሽታው በቂ ቁጥጥር ካልተደረገበትም በ20 አመት ጊዜ ውስጥ በየአመቱ 24 ሚሊዮን ለሚጠጉ የአለማችን ሰዎች ሞት ምክንያት ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡
በኢትዮጵያም በየአመቱ ከ67 ሺ በላይ ሰዎች በካንሰር ህመም እንደሚያዙና ባለው የህክምና አገልግሎት ውስንነት ምክንያት 44 ሺ ያህሉ ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ እንደሚሞቱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በቅርቡ የወጡ ጥናቶች እንደሚየሳዩት ደግሞ በኢትዮጵያ 52 በመቶ የሚሆነው ሞት የሚከሰተው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 5 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆነውን የሞት መጠን የካንሰር ህመም ይሸፈናል፡፡
የካንሰር ህመምን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየጊዜው የሚደረገው ጥረት እጅግ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ እየሆነ ቢመጣም አሁንም በህመሙ ላይ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ከሰሞኑም ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ያደረገው የሶርባን ዩኒቨርሰቲ ተመራማሪዎች ቡድን በጣፋጭ መጠጦችና ካንሰር ህመም መካከል ባለው ግንኙነት ዙሪያ ምርምር በማካሄድ ከውጤት ላይ መድረሳቸውን ሳይንስ ዴይሊ ይፋ አድርጓል፡፡
በብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል የታተመው ይህ የምርምር ውጤት የስኳር መጠናቸው ከ5 በመቶ በላይ የሆኑ ስኳር ያልተጨመረባቸውን ጨምሮ የፍራፍሬ ጭማቂዎች፣ የለስላሳ መጠጦች፣ ጣፋጭ ወተቶች፣ ሃይል ሰጪ መጠጦች፣ እንዲሁም የስኳር ይዘት ያላቸው ቡናና ሻይ በከፍተኛ ደረጃ መጠቀም በካንሰር ህመም ከመያዝ እድል ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
ምንም እንኳን ጣፋጭ መጠጦችን አብዝቶ መጠቀም ምን ያህል ለካንሰር ህመም ሊያጋልጥ እንደሚችል አሁንም ተጨማሪ ማረጋገጫዎችን የሚጠይቅ ቢሆንም ፣የተገኘው የምርምር ውጤት ግን በተለይ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣልና የገበያ ገደብ በማበጀት የጣፋጭ መጠጥ ፍጆታዎችን መቀነስ ምን አልባት በካንሰር ህመም የመያዝ እድልን ዝቅ በማድረግ ረገድ አስታዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ጣፋጭ መጠጦችን የመጠቀም ሁኔታ በመጨረሻዎቹ ጥቂት አስርት አመታት እየጨመረ መሆኑን ሳይንስ ዳይሊ ያስታወሰ ሲሆን፣ ይህም ለሰውነት ያለቅጥ መወፈርና በኋላ ደግሞ በተለያዩ የካንሰር ህመሞች የመያዝ እድልን እንደሚያሰፋ አስታውቋል፡፡ ይሁንና ጣፋጭ መጠጦች ለካንሰር የመጋለጥ እድልን ምን ያህል ከፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚያሳዩ የምርምር ስራዎች አሁንም ውስን መሆናቸውን ገልጧል፡፡
የምርምር ቡድኑ ጣፋጭ መጠጦችን አብዝቶ መጠቀም ምን ያህል ለሁሉም የካንሰር አይነቶች በተለይ ደግሞ ለጡት፣ ለፕሮስቴትና ኮሎሬክታል ካንሰር ሊያጋልጡ እንደሚችሉና ከነዚህ የካንሰር አይነቶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለመገምገም ሞክሯል፡፡
የቡድኑ የምርምር ግኝት መሰረት ያደረገው 101 ሺ 257 በሚሆኑ አዋቂ ፈረንሳውያን ላይ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ በአማካይ በ42 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙና 21 በመቶዎች ወንዶች 79 በመቶዎቹ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች ከሃያ አራት ሰአታት ውስጥ ቢያንስ ሁለቱን ሰዓት ከ(2009-2018) ለዘጠኝ አመታት ሲወስዷቸው የነበሩ 3 ሺህ 3 መቶ የተለያዩ የምግብ እና የመጠጥ ዓይነቶችን ለመከታተል የተዘጋጁ መጠይቆችን በኦን ላይን ሞልቶ ለማጠናቀቅ አሳልፈዋል፡፡
በመቀጠልም የጣፋጭ መጠጦችና በሰው ሰራሽ መንገድ የሚዘጋጁ ጣፋጭ የምግብ መጠጦች የቀን ፍጆታ ተሰልተው በተሳታፊዎች ሪፖርት የተደረገው የመጀመሪያው የካንሰር ህመም በህክምና መዝገብ ከተረጋገጠ በኋላ የጤና መድህን ብሄራዊ ኢንሹራንስ ዳታ ማእከል ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በርካታና የታወቁ ለካንሰር ህመም አጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎች በተለይም እድሜ፣ ፆታ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የቤተሰብ የካንሰር ህመም ታሪክ፣ የማጨስ ደረጃና የአካል እንቅስቃሴ ደረጃዎች ከግምት ውስጥ ገብተዋል፡፡
በዚሁ መሰረት አማካይ የጣፋጭ መጠጦች የቀን ፍጆታ ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ ከፍ እንደሚል በምርምሩ ተረጋግጧል፡፡ ወንዶች 90 ነጥብ 3 ሚሊ ሊትር ጣፋጭ መጠጦችን በቀን ሲወስዱ ሴቶች ደግሞ 74 ነጥብ 6 ሚሊ ሊትር እንደሚጠቀሙ ታውቋል፡፡ በክትትሉም 2ሺ 193 የመጀመሪያ የካንሰር ኬዞች በምርመራ የተረጋገጡ ሲሆን፣ 693 የጡት ካንሰር፣ 291 የፕሮስቴት ካንሰር እንዲሁም 166 ኮሎሬክታል ካንሰር መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በካንሰር ምርመራ ላይ የነበረው አማካይ አድሜም 59 መሆኑ ታውቋል፡፡
የምርምሩ ውጤት እንደሚያሳየውም በቀን 100 ሚሊ ሊትር ጣፋጭ መጠጦችን መውሰድና ይህን ፍጆታ ከፍ ማድረግ በ18 በመቶ በካንሰር ህመም የመያዝ እድልን ይጨምራል፡፡ 22 በመቶ ደግሞ በጡት ካንሰር የመያዝ እድልን መጠጥ አይነቶቹ ወደ ፍራፍሬ ጭማቂዎችና ወደሌሎች ጣፋጭ መጠጦች ተበታትነው ሲታዩ ደግሞ የሁለቱም ለስላሳ መጠጥ ፍጆታ ከሁሉም የካንሰር ተጋላጭነት ጋር ይገናኛል፡፡ ጣፋጭ መጠጦች ከፕሮስቴትና ኮሎሬክታል የካንሰር አይነቶች ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው በምርምር ውጤቱ የተገለፀ ሲሆን የነዚህ የካንሰር አይነቶች መገኛ ቁጥር አነስተኛ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
በንፅፅርም በሰው ሰራሽ መንገድ እንዲጣፍጡ የተደረጉ የምግብ መጠጦች ለካንሰር ከማጋለጥ አኳያ ግንኙነት እንደሌላቸው የምርምር ውጤቱ ያለመከተ ቢሆንም፣ በዚህ ናሙና ውስጥ ዝቅተኛ ፍጆታ እንዳለ ከምርምሩ ተሳታፊዎች የተገኘ ምላሽ በመኖሩ ውጤቱን በመተርጎም ረገድ ጥንቃቄ መወሰድ እንደሚገባው የምርምሩ መሪ አስታውቀዋል፡፡
በጣፋጭ መጠጦች ውስጥ ያለው ስኳር በተለይ በጉበትና ጣፊያ ውስጥ በሚገኘው /visceral fat/ ፣ በደም ውስጥ በሚገኘው የስኳር መጠን /Inflammatory markers/ ላይ በጎ ያልሆነ ተፅእኖ እንዳለውና ይህም በካንሰር የመያዝ እድልን ከፍ ሊያድርግ እንደሚችል ለምርምሩ ውጤቶች አስረጂ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በጣፋጭ መጠጦች ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የኬሚካል ውህዶችም ለካንሰር በማጋለጥ ረገድ የራሳቸውን ሚና እንደሚጫወቱ በምርምሩ ተጠቅሷል፡፡
ምርምሩ የቅኝት ጥናት በመሆኑና አዳዲስ የካንሰር ህመሞች ዋነኛ ምክንያታቸውን በትክክል ለመለየትና ለማሳየት ዋስትና ሊሆን ባይችልም በጥናቱ የተወሰደው ናሙና ትልቅ በመሆኑ ተመራማሪዎቹ ለካንሰር ስፋት ያላቸው ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሳያዎችን ለማስቀመጥ ሞክረዋል፡፡ ከብዙ ሙከራዎች በኋላ የምርምሩ ውጤቶች በአብዛኛው ያልተለወጡ መሆናቸውም ግኝቱ ጥብቅ ምልከታና ፍተሻ የተካሄደበት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ውጤቶቹ ተደጋጋሚና ስፋት ያላቸው ተጨማሪ ጥናቶችን እንደሚፈልግም ተመላክቷል፡፡
በምርምሩ የተገኘው ጥሬ ሃቅ የተቀነባበሩ የፍራፍሬ ጭማቂዎችን ጨምሮ የጣፋጭ መጠጦችን ፍጆታ ለመቀነስ በአሁኑ ወቅት ካለው የስነ ምግብ ምክረሃሳብ ጋር የሚዛመድና በጣፋጭ መጠጦች ላይ ያተኮረ የቀረጥ ጭማሪና የገበያ ገደብ እንዲኖር ብሎም የፖሊሲ ርምጃ በመውሰድ የካንሰር የመከሰት እድልን ለመቀነስ ያስችላል ሲል የምርምር ቡድኑ ገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2011
አስናቀ ፀጋዬ