የትራንስፖርት ዘርፉን የታዳሽ ኃይል መጠቀም አስፈላጊነት ያመላከተው ኤግዚቢሽን

በዓለም የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት እየተባባሰ መምጣቱ ይገለጻል፡፡ ለእዚህ ምክንያት ከሆኑት መካከል ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውም ይታወቃል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ እ.ኤ.አ በ2029/30 የተሽከርካሪዎች የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት 40 ሚሊዮን ቶን እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡ ይህም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ሀገራት የተለያዩ ተግባሮችን እያከናወኑ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል በታዳሽ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን መማተር አንዱ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ በተከናወነው ተግባርም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በአውራ ጎዳናዎች በስፋት እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ ከሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ ያላቸውን አንፃራዊ ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ታዳሽ ኃይልን መሠረት ያደረገውን የትራንስፖርት ዘርፍ መገንባት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ግንባታ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ለዘርፉ ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ የታዳሽ ኃይል በአግባቡ የሚጠቀም፣ በማኅበረሰቡ ጤናና በአካባቢ ብክለት ላይ ጉዳት የማያስከትል አረንጓዴ ትራንስፖርት እውን የማድረጉ ስራም በአሥር ዓመቱ ዕቅድ መሰረት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎችንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ፣ ህብረተሰቡንም የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ የታክስ ማሻሻያው ዓላማ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር በፖሊሲ ማዕቀፍ ከአካባቢ ደህንነት ጋር የሚስማማ ለማድረግ፣ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል፣ በአየር ንብረትና በብዝሃ ህይወት ላይ ተጽእኖ የማያሳርፍ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በአግባቡ የሚጠቀም የመጓጓዣ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡ ማስቻልን ያለመ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

እነዚህ ተሽከርካሪዎች ቀደም ሲል ከውጭ በቀጥታ እንዲገቡ ይደረግ የነበረ ሲሆን፣ የተሽከርካሪዎቹን ፋይዳ የተረዳው መንግሥት ከውጭ በስፋት ሊገቡ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር በሀገር ውስጥ ሊገጣጠሙ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታም ፈጥሯል፡፡ ይህን ተከትሎም ባለሀብቶች በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች ላይ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎች፣ ሚኒባሶችና አውቶቡሶች እየተንቀሳቀሱ ያሉበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል፡፡ የእነዚህን ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ለማስፋትም ሰፊ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡

መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማበረታታት የወሰዳቸውን እርምጃዎች ተከትሎ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር እንደጨመረ ይገኛል፡፡ የባለፈው ወር መረጃ እንዳመለከተው፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ድርጅቶች 15 የደረሱ ሲሆን፣ ተሽከርካሪዎቹን የሚያስመጡት ደግሞ ከ200 በላይ ሆነዋል፡፡

በቅርቡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ባዘጋጀው በአረንጓዴ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ላይ ያተኮረ ኢትዮ- ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ እና ሲምፖዚየም ላይ እንደተጠቆመው ፤ ሀገሪቱ በዚህ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እና ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ትልቅ ፋይዳ ባለው ኢንቨስትመንት ላይ በቀጣይም በስፋት መስራት ያስፈልጋል፡፡

በመድረኩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንደገለጹት፤ የአየር ንብረት ለውጥ እየፈጠረ ያለውን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ መቋቋም የሚችል ዘላቂና አስተማማኝ አረንጓዴ ልማት ማካሄድ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ሊደግፍ የሚችል እምቅ ታዳሽ ኃይል ባለቤት ናት፡፡ ይህን አቅም በመጠቀም የአረንጓዴ ትራንስፖርት ፈር ቀዳጅ ለመሆን እየሠራች ነው።

ሀገሪቱ ያላትን አረንጓዴ እምቅ ኃይልን በመጠቀም በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረትና ለረጅም ጊዜ ሀገራዊ ብልጽግናን የሚደግፉ ጠንካራ የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችን እውን በማድረግ ላይ እንደምትገኝ አመልክተዋል፡፡ ኢትዮ- ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ኤግዚቢሽን እና ሲምፖዚየምም ሀገሪቱ ያላትን እምቅ የአረንጓዴ ኃይል እንዴት መጠቀም እንደምትችል ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዓለም በዘርፉ የደረሰበትን ደረጃና ከፊታችን የሚጠብቀንን ትልቅ ሥራ እንደሚያመላክት አስታውቀዋል፡፡

አፈ ጉባኤው እንዳሉት፤ በሀገሪቱ የተሟላ ለውጥ ለማምጣት፣ እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ እና የሕዝብን ኑሮ ደረጃ በደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው ርብርብ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ያላቸው ተጨማሪ ትግል የሚፈልጉ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው ችግሮችና የከተሞች መጨናነቅን የመሳሰሉ ተግዳሮቶችም አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማሸነፍ በሚደረጉ ጥረቶችም አዳዲስ ፈጠራዎችና መልካም እድሎች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ይህም ኢኮኖሚን ለማሳደግና እምቅ ሀብትን ለመጠቀም እድል ይፈጥራል፡፡

ሀገራት በካርቦን ምንጭ ላይ ከተመሠረተው የትራንስፖርት አገልግሎት በመውጣት በኤሌክትሪክና በሌሎችም ታዳሽ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገልግሎት በማስገባት ላይ መሆናቸውን አፈጉባኤ ታገሰ ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያም በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀትንና በነዳጅ ጋዝ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በሀገሪቱ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን የማምረትና የመገጣጠም ሥራን በማበረታታት እንዲሁም ለዚህ አገልግሎት የሚውሉ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችን ለማበረታታት የሚያስችል ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ ታዳሽ ኃይል ዘላቂነት ያለውና የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የማዕዘን ድንጋይ በመሆኑ በዚህ በኩል ለሚደረግ ኢንቨስትመንት ስኬት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ የበለፀገ ማህበረሰብ ለመፍጠር ፖሊሲ አውጪዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት ይገባቸዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ጠቅሰው፣ የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ ከታለሙ እንቅስቃሴዎች አንዱም ይሄው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብት በመጠቀም በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፈርቀዳጅ ለመሆን የትራንስፖርት መልክዓ-ምድሯን እያሻሻለች እንደምትገኝ አመልክተዋል፡፡

የአሥር ዓመቱ የትራንስፖርት እቅድም ለሞተር አልባ የትራንስፖርት ስትራቴጂዎች፣ ለሕዝብ ትራንስፖርት ፖሊሲዎችና ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸው፣ ለዚህም አስፈላጊውን መሠረተ ልማት ማሟላትና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስቴርም ታዳሽ ኃይል ለሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ወይም ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች የማድረግና ምቹ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ የአዲስ አበባ ከተማን የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ማዕከልነት ለማስጠበቅ የተጀመሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን በአረንጓዴ ትራንስፖርት ለመደገፍ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት ዘርፉን ከነዳጅ ጥገኝነት በማላቀቅ ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ ይጠቅማሉ፤ ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያለው ሲሆን፣ ሚኒስቴሩም በዘርፉ ለተሰማራውና ለሚሰማራው የግል ዘርፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ከኢኮኖሚ ጠቀሜታና የአየር ብክለትን ከመከላከል ባለፈ የድምፅ ብክለትን ለማስቀረትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን እንደሚረዱ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡ ከተሽከርካሪ መሰረተ ልማት ባለፈ የሳይክልና የእግረኛ መንገዶችን በማስፋት ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ፣ የበካይ ጋዝን ለመቀነስና ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና የኢነርጂ መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ዳቢ ኢትዮ- ግሪን ሞቢሊቲ 2024 አውደ ርዕይና ኤግዚቢሽን ከነዳጅ ውጪ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የሚያስችል ሰፊ እድል መኖሩን የሚያመላክት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በሂደትም ነዳጅ ላይ መሠረት ያደረገውን የትራንስፖርት ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ታዳሽ በሆነ የኃይል አቅርቦት ልንተካው እንደምንችል ትልቅ ልምድ የሰጠ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩትም፤ ታዳሽ ኃይልን መሠረት ያደረገ የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ ሥራ መግባት ከነዳጅ የሚወጣውን የካርቦን ልቀት በማስቀረት የአየርን ንብረት ለውጥን በመከላከል በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በተጨማሪም ሀገሪቱ ለነዳጅ ግዢ በየዓመቱ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ በማስቀረት በኩል የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሁሉም ዘርፍ ላይ የታዳሽ ኃይል አጠቃቀም እንዲያድግ እንደሚሠራ ጠቁመው፤ በአምራች ኢንዱስትሪው፣ በትራንስፖርት ዘርፉ ብሎም በቤተሰብ ደረጃ ያለው የኃይል ፍጆታ ሙሉ በሙሉ በታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም የኢነርጂ ልማቱ ታዳሽ ኃይልን መሠረት ያደረገና አካታች እንዲሆን የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጾ እየተተገበረ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች ከታክስ ነጻ ሆነው ወደሀገሪቱ እንዲገቡ ማድረግን ጨምሮ ዘርፉ ላይ የተለያዩ ማበረታቻዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የትራንስፖርት ዘርፉን ጨምሮ በሁሉም መስክ የተፋጠነ የታዳሽ ኃይል ልማት እንዲኖር እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በአውደ ርዕዩ ከተሳተፉ ተቋማት አንዱ የሆነው የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሰጠኝ እንግዳው፤ የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ላለፉት ስምንት ዓመታት የደረቅና ፈሳሽ ጭነት መኪኖችን በሀገር ውስጥ ሲያመርት መቆየቱን ጠቅሰው፣ ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ወደመገጣጠም ተሸጋግሯል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

በዚህም በመጀመሪያው ዙር 216 የሚደርሱ ከ15 ሰው በላይ የሚጭኑ የኤሌክትሪክ ሚኒባሶችን ገጣጥሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በሌሎች ተቋማት ወደ ስራ ማስገባቱን አመልክተው፣ ቬሎሲቲ የተባለ እህት ኩባንያ አቋቁሞ በ20 ሚኒባሶች እና ሁለት አውቶቡሶች አማካኝነት በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ኩባንያው ሚኒባሶች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፤ ደብረብርሃን ከተማ ላይ በገነባው ፋብሪካ አማካኝነት ደግሞ አብዛኛውን ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን እየገጣጠመ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እስካሁንም አሥር ያህል አውቶቡሶችን ገጣጥሞ ለተጠቃሚዎች ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሀገር የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጀር ችግር ለመቅረፍም ከ60 እስከ 160 ኪሎ ዋት አቅም ያላቸው ፈጣን የኤሌክትሪክ ቻርጀሮችን አስመጥቶ ለገበያ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ጥረት ውስጥ ተሳታፊ ሆነን ትልቅ ሀገራዊ አስተዋጽኦ ማድረግ በመቻላችን ደስተኞች ነን ያሉት ኃላፊው፤ ኩባንያው አብዛኛውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይገልጻሉ፡ ፡ የኢትዮ ሞቢሊቲ መድረክ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ የዘርፉን መልካም አጋጣሚዎች ለመመልከትና ተግዳሮቶችን ለመፍታት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አቶ ሰጠኝ አስታውቀዋል።

በአውደ ርእዩ የተሳተፈው የካኪ ሞተርስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እንግዳሰው ደምሴ እንደሚሉት፤ ካኪ ሞተርስ በሀገሪቱ የተለያዩ የጭነት መኪኖችን በስፋት ሲያቀርብ ከሃያ ዓመት በላይ ሆኖታል፤ በሀገር ውስጥ ግዙፍ የአይሱዙ መገጣጠሚያ ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል፡፡

በሀገሪቱ ለታዳሽ ኃይል የተሰጠውን ትኩረት ለማሳካት እንዲቻል በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ወደሀገር እያስመጣ ለተጠቃሚዎች እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይነትም ከውጪ የሚገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በሀገር ውስጥ ለመገጣጠም የሚያስችል ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢግዚቢሽኑ በዘርፉ ምን ያህል አቅም እንዳለ ማመልከታቸውን ገልጸው፣ ለገበያ ትስስር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው ኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2024 አውደ ርዕይና ሲምፖዚየም ላይ ከ700 በላይ ባለድርሻዎች መሳተፋቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። ዝግጅቱም የአረንጓዴ ትራንስፖርትና መሰረተ ልማት አምራቾችን፣ ገጣጣሚዎችን፣ አስመጪዎችን፣ የኢንዱስትሪ መሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አገናኝቷል፡፡ይህም የትብብር እድሎችን ለመፍጠር፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ እንዲሁም ለአረንጓዴ እና ደህንነቱ ለተጠበቀ ቀልጣፋ የትራንስፖርት ዘርፍ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን ማሳደግ ዓላማ አድርጎ የተካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You