አዲስ አበባ፡– በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው ሕገወጥ የግንባታ ተረፈ ምርቶችን የማንሳት ንቅናቄ ባለፉት ዓመታት በከተማዋ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ይበልጥ አጉልቶ የሚያወጣ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ሕገወጥ የግንባታ ተረፈ ምርቶች እና ግብዓቶችን በማንሳት እና ሥርዓት በማስያዝ የከተማዋን ውበት መጠበቅ የሚያስችል ንቅናቄ በትናንትናው እለት ተጀምሯል።
ማስጀመሪያ መድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሲታ እንደገለፁት፤ ባለፉት ዓመታት የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ የቀየሩ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ እነዚህን ሥራዎች ይበልጥ አጎልቶ ለማውጣትም ሕገወጥ የግንባታ ተረፈ ምርቶች እና ግብዓቶችን የማንሳትና ሥርዓት የሚያሲያዝ ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡
ንቅናቄው ተከማችቶ የከተማው ጽዳት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሣደረ ያለውን ሕገወጥ የግንባታ ተረፈ ምርት በማንሳት እምርታዊ ለውጥ ማምጣጥ ዓላማ እንዳለው ጠቁመው፤ በዚህም በከተማው የሚታየውን ሕገወጥ የግንባታ ተረፈምርት እና ግብአት ሙሉ ለሙሉ በማንሳት ከተማዋን ጽዱ፣ ከደረቅ ቆሻሻ ሀብቷ ተጠቃሚ እንዲሁም ለኑሮ ተመራጭ ከተማ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
ንቅናቄው በዘላቂነት በመተግበርም የከተማዋን ደረጃ የሚመጥን ጽዳት እንዲኖር የሚያስችል ብሎም ከተማዋን የጽዳት ተምሳሌት የሚያደርግ መሆኑንም አንስተዋል።
ከተማዋ የምታመነጨው ደረቅ ቆሻሻ በአይነቱም ይሁን በመጠኑ እየጨመረ ቢሆንም ይህን ቆሻሻ በወቅቱ በመሰብሰብ፤ በማጓጓዝ፤ መልሶ በመጠቀምና በማስወገድ ረገድ መልካም የሚባል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ንቅናቄው ያለአግባብ በየመንገዱ የተከማቹ የግንባታ ተረፈ ምርቶች የማንሳትና የማጽዳት ሥራ በከተማው በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች በተለይም በተመረጡ በ66 ወረዳዎች እና 303 ቦታዎች ይካሄዳል ነው ያሉት፡፡
የግንባታ ተረፈ ምርቶችን ባለቤቶች እንዲያስነሱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ከመሥራት ጀምሮ ድርጅቱ ወይም ተቋሙ በተገደበ ጊዜ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲደርሰው የሚደረግ መሆኑን አመልክተው ፤ አንድ ተቋም ሆነ ግለሰብ ደብዳቤ በደረሰው በሁለት ቀናት ውስጥ እንዲያነሳ የሚደረግ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማያነሳ ከሆነ በደንብ ቁጥር 167/2016 መሠረት ቅጣት እንደሚቀጣ ጠቁመው፤ ባለማንሳቱ ምክንያት መንግሥት ለሚያወጣው የትራንስፖርትና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች እንዲከፍል የሚደረግ ይሆናል ብለዋል፡፡
በተለይም የኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ የተሠማሩ ተቋማትና ግለሰቦች በሃላፊነት ተረፈ ምርቶችን በማስወገድ ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውና የከተማ ጽዳት ሥራ የሁሉንም አካላት ትኩረት የሚሻ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም
ማህሌት ብዙነህ