የምግብና የመሬት ሥርዓት ሽግግርን በማቀናጀት አካታች የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት ይገባል

አዲስ አበባ፦ የምግብና የመሬት ሥርዓት ሽግግርን በማቀናጀት አካታች ኢኮኖሚያዊ እድገት ማምጣት እንደሚገባ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። በኢትዮጵያ የግብርና ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር አዘጋጅነት በኢትዮጵያ የመሬት ማሻሻያና በምግብ ሥርዓት ላይ ያተኮረ ውይይት ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የግብርና ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር አዘጋጅነት በኢትዮጵያ የመሬት ማሻሻያና በምግብ ሥርዓት ላይ እየተካሄደ ባለው ውይይት ላይ ፤በግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪና የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ሽግግር ዋና አስተባባሪ ጌታቸው ዲሪባ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሕዝቡን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ትልቁን ሚና ይጫወታል።

ከዛሬ 50 ዓመት በፊት መሬት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተብሎ ሲታወጅ ተስፋ የተጣለበት የነበረ ቢሆንም፤ አጋጣሚው ያንን ዓላማ የሚያሟላና ሁሉም ደሃ እንዲሆን የተደረገበት ሁኔታ እንደነበር ጠቁመው፤ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ ይህንን አካሄድ ለማስተካከል ብዙ ጥረት ተደርጓል። ከወራት በፊት የተደረገው የገጠር መሬት አስተዳደር ማሻሻያ አዋጅም አሁን ላይ ጥሩ ለውጦች እያመጣ ይገኛል ብለዋል።

እንደ አማካሪው ገለጻ፤ በዚህም ገበሬው መሬቱን የማስተላለፍ፣ የማስያዝ፣ ለልማት የማዋል፣ ክላስተር አድርጎ የማረስ እድሎችንም አግኝቷል። የኢትዮጵያ የምግብ ፍላጎት በየቀኑ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ይህንን የሚመጥን የቴክኖሎጂ እድገትና ፈጠራ ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ የእርሻ መሬት የተበጣጠሰ በመሆኑ ሜካናይዜሽንን በመተግበር የሚፈለገውን ምርትና ምርታማነት ለማምጣት አስቸጋሪ ነው ያሉት ጌታቸው (ዶ/ር)፤ በአሁኑ ወቅት መሬትን በክላስተር በማረስ ከፍተኛ ምርት የማግኘት እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ፍሬው ተገኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሙያ ማህበራት ጽንሰ ሃሳቦችን ወደ ተግባር በመተርጎም በጥናትና ምርምር ውጤቶች በማስደገፍ ለለውጥ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን እንደሚያመነጩ በመግለጽ፤ ተቋማቸው የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ለሚመለከታቸው አካላት የመፍትሄ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል።

ኢንስቲትዩቱ በግብርናና በሌሎችም ዘርፎች 400 የሚጠጉ ተግባር ላይ ያተኮሩ የምርምር ሥራዎችን ሠርቷል። ከእነኝህ ጥናቶች ውስጥም 26 በመቶ የሚሆነው ለሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ እቅድ ዝግጅት ድጋፍ ያደረገ ነው፤ የተቀረው ለመንግሥት ውሳኔ ሰጭነት ማገልገሉን ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የመሬትን ምርታማነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በሰፊው እየሠራበት ይገኛል ያሉት ፍሬው (ዶ/ር)፤ በኮሜርሻላይዜሽንና በክላስተር ዘርፍ የሚስተዋለው የመሬት መበጣጠስ፣ ቴክኖሎጂዎችን አለመተግበርና ሌሎችም ክፍተቶችን ለመሙላት አዲሱ የገጠር መሬት አስተዳደር አዋጅ ያግዛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የግብርና ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት እንደሻው ሀብቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ደህንነትን በማረጋገጥ ዜጎችን መመገብ የመንግሥት ቀዳሚው የትኩረት አቅጣጫ ነው። በዚህም የመሬት ሚና ቀላል የሚባል አይደለም።

መሬት ለኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚም ፖለቲካም ጭምር መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ መሬት ባለፉት ጊዜያት በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ማህበሩ አቅምን ለማጎልበትና በግብርናው ዘርፉ ላይ የሚያተኩሩ መድረኮችን በማዘጋጀት ተገቢ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለማዘጋጀት አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You