ከነገ ማዶ …

ከዓመታት በፊት…

ወይዘሮዋ ነፍሰጡር መሆኗን አውቃለች። ይህ እውነት ለውስጧ ደስታን አቀብሏል። ነገ ስለምትወልደው ልጅ እያሰበች ነው። ሁሌም እንደ እናት መሆን የሚገባትን ታልማለች። የልጇ መልካም እድገት፣ የወደፊት ሕይወት ውል ይላታል። ይሄኔ ፊቷ ይፈካል፣ ውስጧ ይፍታታል።

እሷ ማርገዟን ካወቀች ወዲህ ስለራሷ ያላት ግምት ተቀይሯል። ዘወትር ታስባለች። ነገ ልጇን ወልዳ ስታቅፍ የሚያስፈልጋትን አታጣውም። ይህ እንዲሰምር ጤናዋን ትጠብቃለች፣ ጆሮዋ ሁሌም ለሌሎች ምክር ክፍት ነው። መልካም ሃሳቦች ይስቧታል። ውስጧ ነገን ሲያስብ አርቆ ያልማል። ነገ ለእሷ መልከ ብዙ ነው።

ሶስት ጉልቻ…

ጥንዶቹ በአንድ ጣራ ስር መኖር ከጀመሩ ቆይተዋል። እስከዛሬ ‹‹አንተ ትብስ አንቺ›› ይሉት እውነት በእነርሱ እውን ሆኗል። ለትዳራቸው ይተሳሳባሉ። አባወራው ከውጭ ሰርቶ ይገባል፣ ወይዘሮዋ የጓዳዋን፣ የቤቷን ጎዶሎ ትሞላለች። አሁን ደግሞ ፍሬ ሊያዩ በልጅ ሲሳይ ሊባረኩ ነው። ሁለቱም ደስ ብሏቸዋል።

ጊዚያት እየተቆጠሩ ነው። ጥንዶቹ ስለቤታቸው ድርሻቸውን አልዘነጉም። ዛሬን አልፈው ነገ ላይ ሲቆሙ የሚያሻቸውን ያውቃሉ። ነገ እንደትናንት አይደለም። ቤተሰብ ሲጨምር ቀዳዳው ይበዛል። መሽቶ በነጋ ቁጥር ኃላፊነቱ ይከብዳል።

ሙሉ ላቃቸው የሕይወት አጋጣሚ ከጎጃም አዲስ አበባ ካመጣት ወዲህ ኑሮዋ ‹‹ፉሪ›› ከሚባለው ሰፈር ሆኗል። አካባቢው ለእሷና ለባለቤቷ መልካም የሚባል ነው። በእነሱ መንደር ጉርብትና ትርጉም አለው። ሁሉም ተግባብቶ፣ ተስማምቶ ያድራል። በክፉ ቀናት ፈጥኖ ደራሹ፣ ዕንባ አባሹ ይበረክታል። ደስታ ባጋጠመ ጊዜ ስሜቱ የጋራ፣ ሆኖ ይከርማል።

አሁን የወይዘሮዋ መውለጃ ቀን ቀርቧል። ለቤቷ ፣ ለእንግዶቿ ፣ ለአራስ ጎኗ የአቅሟን አዘጋጅታለች። ከዚያ በፊት ግን ተጨማሪ ምርመራዎች ይቀሯታል። ቀጠሮዋን አስታውሳ ቀኑን አንድ ሁለት ብላ ቆጠረች። ጣቶቿ ዕለቱን አላዛቡም። በትክክል ከቀጠሮ ቀኗ አደረሷት።

አንድ ማለዳ እንደ ልምዷ ራሷን አዘጋጀች። የቀጠሮ ቀኗ ነበር። አላረፈደችም። በሰዓቱ ከጤና ጣቢያው ደርሳ ተራ አስኪደርሳት ተቀመጠች። ከጎኗ ያሉ እናቶች እርስ በርስ ያወጋሉ። ስለራሳቸው፣ ስለባሎቻቸውና ስለሌላም። ሁሌም የዚህ ቦታ ጨዋታ ተመሳሳይ ነው። ከእሷ የሚቀድሙ ምርመራቸውን አጠናቀው እየወጡ ነው። ሙሉ ስሟ እስኪጠራ ጆሮዋን ጥላ አዳመጠች።

አሁን ተራዋ ደርሶ ወደ ውስጥ ዘልቃለች። በየወሩ ሐኪም ባገኛት ቁጥር ከፊቷ እፎይታ ይነበባል። የነርሶቹ፣ የሐኪሞቹ ፈገግታ ፈገግታዋ ነው። ዕለቱን ግን ከምርመራዋ በኋላ ያየችው ገጽታ ፈጽሞ አላማራትም። ሐኪሙ በእጁ የደረሰውን ውጤት አተኩሮ እያየ ነው። ውስጡ ጥሩ አልመስል ቢላት መጨነቅ ያዘች።

ጥቂት ቆይቶ ሐኪሟ እውነታውን ገለጸላት። በሆዷ ያለው ጽንስ ችግር እንዳለበት ባሳወቃት ጊዜ በድንጋጤ ክው አለች። ሐኪሙ የምርመራውን ሐቅ አንድ በአንድ ለማስረዳት አልዘገየም። ሙሉ ስለ እርግዝናዋ እክል እውነቱን ካወቀች በኋላ አማራጩ ወዲያው ቀርቦላታል።

በሕክምና ታግዛ ጽንሱን ማስወገድ እንደምትችል ሰምታለች። እሷ ግን ይህን አማራጭ ‹‹እሺ›› ብላ ለመወሰን ልቦናዋ አልፈቀደም። ይህን ማድረግ በፈጣሪ ሥራ መግባትና እያወቁ ነፍስ ማጥፋት መሆኑን አምናለች። ልጇ በሕይወት ከተወለደ በይሁንታ ተቀብላ ለማሳደግ የወሰነችው ወዲያው ነበር።

ይህ የምርመራ እውነት በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ እናት ለምትሆን ሴት በእጅጉ ይከብዳል። ሙሉም ብትሆን ውስጧ ከዚህ ስሜት አልራቀም። እስከ ዛሬ ‹‹ወልጄ ጤነኛ ልጅ አቅፋለሁ፤ እስማለሁ›› ስትል ቆይታለች። እስከ አሁን በነበራት ምርመራም ጽንሱ ችግር እንዳለበት አልተነገራትም።

ነፍሰ ጡሯ ወይዘሮ ቤቷ ስትመለስ እንደ ቀድሞው እፎይታ ከእሷ አልነበረም። በሆነባት፣ በተነገራት ጉዳይ ተጨንቃና ተክዛ ነበር። ሙሉ ባለቤቷ ወደ ቤት ሲመለስ ከሐኪሞች የሰማችውን እውነት አንድ በአንድ ነገረችው። አባወራው ይህን በአወቀ ጊዜ ድንጋጤ ወረረው።

ከምክር በኋላ…

አሁን ባልና ሚስት ምክክር ይዘዋል። ይህ ጉዳይ የአንዳቸው ብቻ አይደለም። የጋራ ሕይወታቸውን፣ ቤት ትዳራቸውን ይቃኛል። ባል ሃሳቡ ልክ እንደሚስቱ ሆኗል። እግዜር በሰጣቸው ፍጡር ላይ ‹‹ይሙት በቃ››ን መወሰን አይሻም። ከፈጣሪ የተቸረን ስጦታ በምስጋና መቀበል ግድ ይላል።

ሚስት ሁሌም ባለቤቷን አክባሪ ናት። መቼም ከቃሉ አትወጣም። የሚላትን ትሰማለች። ለሃሳቡም ትገዛለች። ዛሬ ደግሞ ባሏ የእሷን ሃሳብ በጽኑ ደግፏል። ከጎኗ ሊቆም፣ ‹‹አይዞሽ፣ አለሁሽ›› ሊላት ቃል ገብቷል። ጥንዶቹ ልጃቸው ምንም ይሁን ምን በሰላም ተቀብለው ሊያሳድጉት ወስነዋል።

እነሆ የመጨረሻው ቀን ነው። የተረገዘው ሊወለድ ጊዜው ደርሷል። እናት ሙሉ ከሆስፒታል ገብታለች። ሴት ልጅ መውለዷን ባየች ጊዜ ስለሚሆነው ሁሉ አልጨነቃትም። አስቀድማ ሁሉን አውቃለችና ራሷን አዘጋጅታ ልጇን በፈገግታ ተቀበለች። ከምንም በላይ ጸሎት ምስጋናዋን አልተወችም። ሁሉም የሆነው በፈጣሪ ፈቃድ መሆኑን አምናለች።

ሕክምናው …

ሙሉ የልጇ ሕክምና የጀመረው ውሎ ሳያድር ነበር። ለቀናት ከሆስፒታል አልጋ የከረመችው እናት እንደ ወጉ ወደቤቷ በክብር አልገባችም። ስለልጇ ጤንነትና በሕይወት መኖር ጊዜያትን ከፍላ በቆይታ አሳለፈች። የትንሸዋ ልጅ የጤና ችግር በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የፎሊክ አሲድ እጥረት መሆኑ ተነግሯታል።

በአብዛኛው ይህ ዓይነቱ ችግር መኖሩ የሚታወቀው በእርግዝና የመጨረሻ ጊዚያት መሆኑ በጽንሱ ህልውና ላይ ለመወሰን የሚያስቸግር ይሆናል። ብዙ ጊዜ እንደ ሙሉ እውነታውን የሚያውቁ እናቶች በልጆቻቸው ሕይወት ላይ ለመወሰን ይቸገራሉ። ጥቂት የማይባሉትም ልጆቻቸው ወደ ምድር በሕይወት እንዲመጡ ይፈቅዳሉ። እንዲህ በሆነ ጊዜ ሕፃናቱ ከተወለዱ በኋላ በተገቢው ሕክምና እንዲታገዙ ማድረግ የግድ ይሆናል።

የነርቭ ዘንግ ክፍተት /ስፓይና ቢፊዳና ሀይድሮሴፋለስ/ ሕፃናት በእናታቸው ሆድ ሳሉ የሚከሰት የጤና ችግር ነው። በእርግዝና ወቅት ከሕፃኑ ጀርባ የመሀለኛው፣ የላይኛውና የታችኛው ክፍል፤ በጊዜው መዘጋት የነበረበት የሕፃኑ የራስ ቅልና የህብለሰረሰር ዘንግ ክፍተት ችግሩ እንዲከሰት ምክንያት ይሆናል። በጭንቅላት ውስጥ ከመጠን ያለፈ ፈሳሽ ሲኖርና ኢንፊክሽን ሲፈጠርም ይህ ችግር የሚያጋጥም ይሆናል።

 

ሙሉ ከወለደች በኋላ ሆስፒታል በቆየችባቸው ጊዚያት ሕፃኗ ተገቢውን ሕክምና እንድታገኝ ሆነ። ሕክምናው ግን ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ አልነበረም። ተደጋጋሚ ምልልስና ክትትልን ይፈልጋል። እናት አስቀድማ ራሷን አዘጋጅታለችና ይህን ማድረጉ አልከበዳትም። ስለ ልጇ መሆን የሚገባውን ሁሉ ለማድረግ ዋጋ እየከፈለች ነው።

ባለቤቷም ቢሆን ከሚስቱ ጋር ውሳኔውን በእኩል አሳልፏል። ልጃቸው ወደዚህች ምድር እንድትቀላቀል የፈቀደው በሙሉ ልብ ነው። አሁን ውሎ አዳር በሆስፒታል ሆኗል። እናትና ልጅ አልጋ ይዘው ወራትን ቆጥረዋል። ሙሉ በየዕለቱ በልጇ ላይ ለውጥ ማየት ጀምራለች። የሕፃኗ የጭንቅላት ክፍተት እየቀነሰ መሆኑ በባለሙያዎች ተነግሯታል። ይህን ባወቀች ጊዜ እፎይታ ይሰማት ይዟል።

ባለቤቷ የሚስቱና የሕፃኗ የሆስፒታል ቆይታ የተመቸው አይመስልም። ሕክምናው ጊዜ ፈጅቶ ወራት ማስቆጠሩ እያሳሰበው ነው። አስቀድሞ በልጁ ሕይወት ላይ ሲወስን ይህን ያህል ይከብድ አልመሰለውም። አሁን ግን ሁኔታዎች እያሳሰቡት መጨነቅ፣ መበሳጨት ጀምሯል።

የአባወራው ነገር …

ሙሉ የልጇን ሕክምና ጨርሳ ወደቤት ስትመለስ ባለቤቷ እንደቀድሞው አልቆያትም። በፍቅር አልባ ገጽታ ተቀበላት። ሁኔታው ፈጽሞ አልገባትም። በየምክንያቱ ያኮርፋል፣ ይናደዳል። የሕፃኗ ጤና ማጣት ባሰበው ልክ አለመሆኑ ሰላም ነስቶታል። ይህ እውነት በእሱ ውስጥ ብቻ አልቀረም። በሆነው ሁሉ ምክንያቱን በሚስቱ አሳቦ ተጠያቂነትን እየሸሸ ነው።

ሙሉ የባሏ አዲስ ባህሪ ቢከብዳትም ለምን አላለችም። ሁሉን ችላ ስሜቱን ልትረዳው ሞከረች። ሕፃኗ ከተወለደች ጀምሮ የቤቱ ሰላም ተናግቷል። ሳቅ ጨዋታ ጠፍቷል። የሕክምናው ውጤት በሕፃኗ ጭንቅላት ላይ መልካም ቢሆንም የጀርባዋ ላይ ክፍተትና ቁስል በቶሎ አልገጠመም። በየጊዜው ሆስፒታል የምትመላለሰው እናት ደከመኝ፣ ሰለቸኝ አላለችም። ጊዜና ጉልበቷን፣ ኑሮና ሕይወቷን ለልጇ አበርክታለች።

ሕፃኗ ስድስት ወር እንደሞላት አባወራው ቤቱን ጥሎ ወጣ። ምክንያቱን አሳምራ የምታውቀው ሚስት ‹‹እባክህ ፣ተመለስ›› አላለችውም። ውስጧ እያነባ፣ አንጀቷ እያረረ በዓይኖቿ ሸኘችው። አባወራው ትዳሩን በትኖ ከሄደ በኋላ ሙሉ የብቸኝነትን ሕይወት ጀመረች። ይህ ጊዜ የታመመች ልጅ ለያዘችው እናት ቀላል የሚባል አልሆነም።

ወይዘሮዋ በየጊዜው ሆስፒታል መመላለሱ አቅሟን ፈተነው። እሱን ትታ ጤና ጣቢያ ላይ ጀመረች። የቤት ኪራዩ፣ የዕለት ወጪው ጭንቀት ሆነባት። በወጉ ቁስሏ ያልደረቀ ልጇን አዝላ በየሰው ቤት መሥራት ጀመረች። የሕፃንዋ ህመም የዋዛ አልሆነም። የእናቷ ምቾት አልባ ኑሮ በየቀኑ እየፈተነ አሰቃያት።

የእናት ጉጉት…

ትንሽዋ ልጅ ማደግ ጀምራለች። እንደ ሕፃን ‹‹እማማ፣ አባባ›› ማለት እየሞከረች ነው። እናት አንድ ዓመት ሊሞላት አካባቢ እንደ እኩዮቿ መዳህ፣ መቆሟን ናፈቀች። እጆቿን ይዛ፣ ወገቧን ደግፋ ልታራምዳት ሞከረች። ምኞቷ ሁሉ ከንቱ ነበር። ሕፃንዋ እንዲህ ልትሆን አልታደለችም። እናት የልቧ፣ የሃሳቧ አልሞላም። ሙሉ የሕፃንዋ የጀርባ አጥንት በቀዶ ሕክምናው ወቅት መዛባቱን አውቃለች። መፍትሔ አልባው ችግር አብሯት ቀጥሏል።

የልጇ እድሜ ከፍ ማለት ሲይዝ የጀርባዋ ቁስል እየከፋ ሄደ። አተነፋፈሷና የሆዷ ቅርጽ እንደተለመደው አልሆነም። የሆዷ አቀማመጥ እንደተለመደው አይደለም። ተዛብቷል። የቤት ኪራይና የዕለት ጉርስ ጥያቄ አርፎ የሚያስቀምጣት አልሆነም። ስለኑሮ ግዴታ ልጇን አዝላ በየሥራው መንከራተቷን ያዘች። እንዲያም ሆኖ እናት ሙሉ ስለልጇ ሕክምና አብዝታ ትጨነቃለች።

ብዙ ጊዜ ሁኔታዋን ያዩ ጎረቤቶቿ ልጇን ትታ እንድትሄድ ይጠይቋታል። እሷ ግን ምን ቢቸግራት ይህን ለማድረግ አትወሰንም። የጭንቅላቷና የጀርባዋ ችግር የእሷን ጥንቃቄ ስለሚሻ አምና ጥላት ለመሄድ ይቸግራታል። እየጨነቃት ታመሰግናቸዋለች።

አንዳንዶች…

ሙሉ ልጅ ከወለደች ወዲህ የቅርብ የምትላቸው ዘመዶቿ ሳይቀሩ ፊታቸውን እያዞሩባት መሆኑን ተረድታለች። አንዳንዴ ለሰላምታ ስልክ በደወለች ጊዜ ሊያነሱላት አይወዱም። የእሷ ፍላጎት ገንዘብ ሊሆን ይችላል ያሉ በርካቶች ተደጋጋሚ ጥሪዋን እንዳላየ ያልፉታል። ሙሉ እንዲህ በአጋጠማት ጊዜ በልጇ ላይ ያሳለፈችው ውሳኔ ልክ አለመሆኑን እያሰበች ራሷን ትወቅሳለች።

ውሎ አዳሯ ከሆስፒታል አልጋ የሆነው እናት ኑሮ እየከበዳት ነው። ተከታታይ ሕክምና የሚሻው የልጇ አካል ያለእሷ ዋስትና አላገኘም። ችግሩ ሲከፋ፤ ኑሮ ሲወደድ ‹‹ነገን ምን እሆናለሁ›› ይሉት ሃሳብ እያስጨነቃት ነው። አንዳንዴ የልጇ አባት ዘንድ ደውላ ሁኔታውን ልታስረዳው ትሞክራለች። እሱ ገና ድምጽዋን ሲሰማ ጆሮዋ ላይ ይዘጋባታል።

ባል ከሚስቱ ከተለየ ጥቂት ጊዜ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ቤት መኖርና መመላስ ጀምሮ ነበር። ያልተመቸው ሕይወት ግን አብሮ ሊያዘልቀው አልቻለም። ሁሌም እሷን ብቻ ተጠያቂ ከማድረግ የማይዘለው አባወራ እናት ልጇን መጠቀሚያና መለመኛ እንዳደረገቻት ጭምር ያስባል። ለሙሉ ይህ ዓይነቱ ንግግር አብዝቶ ልቧን ይሰብረዋል። በየጊዜው አምርራ ታዝናለች፣ ትከፋለች።

አሁን ልጇ ሁለት ዓመት አልፏታል። ደስ ባላት ቀን በሳቅ እየፈካች ታጫውታለች። ባመማት ጊዜ ህመሟ የእናቷ ጭምር ነው። ቁስሏ ያደማታል፣ ስቃይዋ ይሰማታል። አንዳንዴ በእሷ ዕድሜ ያሉ ልጆችን ስታይ እንደ እነሱ መራመድ ፣ መሮጥ ያምራታል። እጇን ፊት ለፊት እየጠቆመች ታሳያታለች። እናት ሙሉ የሆዷን በሆዷ አድርጋ ፈገግ ትልላታለች።

ልጇ መቼውንም ቆማ መሄድ እንደማትችል የምታውቀው እናት ፍላጎቷ ሲገባት ስለእሷ ዕንባ ያንቃታል፣ የእናትነት አንጀቷ ይላወሳል። እንዲያም ሆኖ በሆነባት ነገር አምርራ አታዝንም። ልጇ የጀርባዋ ቁስል ከዳነና አዕምሮዋ ጤነኛ ከሆነ ‹‹ተመስገን›› ማለትን ትወዳለች። የእግሮቿ ጉዳይ ሌላው ችግር ቢሆንም ወደፊት በዊልቸር መጠቀም መቻሏ ያጽናናታል።

ሙሉ የልጇ አባት ቢከፋባትም ቤተሰቦቹ መልካም ናቸው። ችግሯን ይረዳሉ። ባላቸው አቅም ከጎኗ ሆነው ጎዶሎዋን ይሞላሉ። በተለይ ታላቅ ወንድሙ ስለእሷ ሀዘኔታው ይለያል። የወንድሙ ድርጊት ስለሚያበሽቀው አብዝቶ ተቃዋሚው ነው። ሁሌም ከልጆቹ አፍ ነጥቆ፣ ከቤት ከጓዳው አጉድሎ ያካፍላታል።

አንዳንዴ ሙሉ ለቤት ኪራይ እጅ ሲያጥራት ሀገር ቤት ያሉ ቤተሰቦቿ ዘንድ ትደውላለች። ችግሯን አስተዛዝና ስትነግራቸው አይጨክኑም። ያላቸውን አሰባስበው ይልኩላታል። ካገኘችው ብር ለቤት ኪራይ ከፍላ ጥቂት የሚቀራትን ለልጇ ፍላጎት ታውላለች።

መልካም ጎረቤቶች …

ሙሉ መልካም ጎረቤቶቿ የክፉ ቀናት አጋሮቿ ናቸው። በከፋት፣ ባዘነች ጊዜ ከጎኗ አይርቁም። ሕይወት ኑሮዋን ለመረዳት፣ ችግር ፈተናዋን ለመካፈል ወደኋላ አይሉም። የኑሮ ደረጃቸው ተመሳሳይ ቢሆንም ከእሷ ራሳቸውን ማስቀደም ልምዳቸው አይደለም። ወጥታ ስትገባ ቤቷን ከፍተው ይጠብቋታል። ይህን ስታይ ሙሉ ድካሟ ይጠፋል። እንደ ሁልጊዜው ደጋግማ ፈጣሪዋን ‹‹ተመስገን ›› ትላለች።

እናት ሙሉን የመሰሉ በርካታ ሴቶች ስለልጆቻቸው መኖር ሻማ ሆነው መቅለጣቸው ዕሙን ነው። ሁሉም ባይባሉም በርካቶቹ አባቶች የጤና ችግር ካለባቸው ልጆች ጋር መዝለቅን አይሹም። ቤታቸውን ትተው፣ ትዳራቸውን በትነው ሌላ ሕይወት ለመመስረት ይፈጥናሉ። እናት ሙሉ የመጀመሪያ ልጇ የሆነችውን ሕፃን ይዛ ዛሬም ስለጤናዋ፣ ስለሕይወቷ መትጋቷን ቀጥላለች። ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አታውቅም። ዘወትር መጪውን ጊዜ በሃሳብ እየሳለች ከነገ ማዶ ያለውን ተስፋ ታልማለች። ብርቱዋ ፣ ብቸኛዋ እናት ሙሉ ላቃቸው።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You