የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የዜጎች ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ነው፡፡ ይህም ዜጎች በአገራቸው ላይ እኩል እድል አግኝተው የሚሰሩበትና ሃብት የሚያፈሩበትን መንገድ ማመቻትን ያካትታል፡፡ ይህ ከሚገለፅባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ደግሞ ለዜጎች የስራ እድልን ማመቻቸት ነው፡፡
በአንድ አገር ውስጥ የስራ አጥነት ችግሮች ከተስፋፉና አብዛኞቹ ዜጎች ከሃገሪቱ ሃብት የበይ ተመልካች ከሆኑ የዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ከመሰረቱ ይናጋል፡፡ ህዝብም በመንግስት ላይ እምነት ያጣል፡፡ ይህ ደግሞ በመንግስትና በህዝብ መካከል መተማመን እንዳይኖር ያደርጋል፤ የግጨት መንስኤም ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ለሚታዩ ችግሮችም ስራ አጥነት አንዱ መንስኤ ነው፡፡
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉና የህዝብ ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በሚገኝባቸው አገራት ይህን የሚመጥን የስራ እድሎችን በየጊዜው መፍጠር ካልተቻለና የስራ አጥ ዜጎች ቁጥር እየበዛ ከሄደ ሰላምን ማረጋገገጥ አዳጋች ይሆናል፡፡
የአገራችን ኢኮኖሚ ገና በማደግ ላይ ያለ በመሆኑ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ሰፊ የስራ እድሎች መፍጠር የሚያስችል አቅም አለመገንባቱ አንዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል 70 ከመቶ የሚሆነው ህዝቧ እድሜ ከ30 አመት በታች ነው፡፡ ይህ በወጣት የተገነባ ህዝቧ ደግሞ የስራ አጥ ቁጥሩን ያባብሰዋል፡፡
በየአመቱም ሁለት ሚሊዮን አዲስ ስራ ፈላጊዎች ገበያውን ይቀላቀላሉ፡፡ ከአርባ በላይ ከሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችም በየአመቱ ከ152 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይመረቃሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ አገሪቷ ተጨማሪ የስራ እድሎችን መፍጠር እንዳለበት የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ባለፉት አስር አመታት መንግስት በአገሪቷ ያለውን ስራ አጥነት ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ አማካይነት በተለይ ወጣቶችና ሴቶች ተደራጅተው ስራ እንዲፈጥሩ የተደረገው ጥረት አንድ ማሳያ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዘርፍ በሚጠበቀው ልክ ችግሩን ሊፈታ አልቻለም፡፡ ለዚህም የተለያዩ ተግዳሮቶች ይነሳሉ፡፡ በአንድ በኩል በዘርፉ ውስጥ የአሰራር ክፍተትና የመልካም አስተዳደር ችግር የነበረ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የስራ ባህላችን ደካማ መሆን ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ከዚህ አንፃር ስራ አጥ ዜጎችን በአግባቡ በመለየትና በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡና በመንግስት በኩል የገበያ እና የመስሪያ ቦታዎች እንዲመቻቹ አቅጣጫ ቢቀመጥም ይህንን የሚመሩ አካላት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ባለመምራታቸውና በዘርፉ ውስጥም በሚታዩ የጥቅማ ጥቅምና የዝምድና ስራዎች ስራ አጥ ወጣቶች ተገቢውን እድል ያላገኙባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን አንዳንድ ወጣቶች በመንግስት የተሰጣቸውን እድል በአግባቡ ሳይጠቀሙበትና በጊዜያዊነት ጥቅም ለማግኘት ሲሉ እድሉን አሳልፈው በመስጠት ስራው ዓላማውን የሳተበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡
ሁለተኛው መሰረታዊ ጉዳይ ደግሞ የስራ ባህላችን ደካማ መሆን ነው፡፡ በአገራችን ከትንሽ ስራ ተነስተው ሚሊየነር መሆን የቻሉ በርካታ ወጣቶች ቢኖሩም አነስተኛ ስራዎችን መስራት የማይፈልጉና ስራን የሚያማርጡ በርካታ ወጣቶችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በተለይ በአገራችን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ከትንንሽ ስራ ተነስተው ከማደግ ይልቅ የመንግስትና የቤተሰብ ጠባቂ የመሆን ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ የስራ አጥ ወገኖች ቁጥር እንዲያሻቅብ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
አሁን በአገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ በርካታ የስራ እድሎችን መፍጠር ነው፡፡ በዚህም መሰረት በቀጣዩ አመት ሶስት ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድሎችን ለመፍጠር አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ይህ እቅድ በአግባቡ ከተሳካና ለተከታታይ አመታት ማስቀጠል ከተቻለ ደግሞ አሁን በአገራችን የሚታየውን መሰረታዊ ችግር ከስሩ ለመፍታት እንደሚቻል ጥርጥር የለውም፡፡
ለዚህም መንግስት በ2012 በጀት አመት አብዛኛውን በጀት በድህነት ተኮር የልማት ስራዎች ላይ ለማዋል አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ በሆነው የግብርና ዘርፍ በቀጣዩ አመት 20 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በመመደብ በርካታ የስራ እድሎችን ለመፍጠር ያደረገው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በሌላም በኩል በአገራችን በተለያዩ ክልሎች በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር ባለሃብቶች የስራ እድሎችን እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል፡፡ የግል ባለሃብቱ ከተጠናከረ የስራ እድሎችን በመፍጠር የስራ አጥነት ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል፡፡
ህብረተሰቡም በዚህ ሂደት ውስጥ የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከት አለበት፡፡ በተለይ ቀደም ሲል እንደሚታየው ስራን ከማማረጥ ባህል ወጥተን ማኛውንም ስራ ሳንንቅ በመስራት ለአጠቃላይ አገራዊ ልማት በጋራ መረባረብ ይጠበቅበታል፡፡ በተገኘው የስራ እድል ሁሉ ተሰማርተን ራሳችንንና ቤተሰባችንን ብሎም አገራችንን ለመለወጥ እንትጋ፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2011