የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ሰባት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ ትናንትና ባካሄደው 40ኛ መደበኛ ስብሰባው በቅድሚያ የተወያየው የመካከለኛ ዘመን (2017-2021) የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማሕቀፍ ላይ ነው፡፡ ማሕቀፉ በሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚከናወኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችንና የመንግሥት የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እና ለ2017 የፌዴራል መንግሥት ተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ መነሻ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተቃኝቶና ተሻሽሎ የቀረበ መሆኑን ገልጿል፡፡ ምክር ቤቱም በማሕቀፉ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ታውቋል።

በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በፌዴራል መንግሥት የተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ አዋጅ ላይ ነው። ይህ የማስተካከያ አዋጅም የተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያው የተሻሻለውን የ2017-2021 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማሕቀፍ ማስፈጸም በሚያስችል መልኩ የመንግሥት የፋይናንስ አቅምና ተጠባቂ ገቢዎችን ታሳቢ በማድረግ፣ የተጨማሪ በጀት ታሳቢዎችንና የወጭ ታሳቢዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት መዘጋጀቱን ተጠቅሷል።

በዚሁ መሠረት ለመደበኛ ወጪዎችና የወጪ አሸፋፈን ለማስተካከል የሚውል 581,982,390,117 /አምስት መቶ ሰማንያ አንድ ቢሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሁለት ሚሊዮን ሶስት መቶ ዘጠና ሺህ አንድ መቶ አስራ ሰባት ብር/ ተጨማሪ በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል። ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀትና የወጪ ማስተካከያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።

በሦስተኛ ደረጃ የተወያየው በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሣብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው። ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብዓቶችን በማከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።

የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረቂቅ አዋጅ ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ ነው። ደረቅ ቆሻሻ በአካባቢ እና በሰዎች ደኅንነትና ጤና ላይ እያስከተለ ያለውን ተፅዕኖ እና ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ምክር ቤቱም በአዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።

ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ደንብን ለማሻሻል በወጣ ደንብ ላይ ነው። ተቋሙ በሕግ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት መወጣት እንዲችል ማቋቋሚያ ደንቡን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል። ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።

የውሃ አካል ዳርቻ አከላለል፣ ልማት፣ እንክብካቤና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ ምክር ቤቱ የተወያየበት ስድስት አጀንዳ ነው። የውሃ አካላት ዳርቻ መከለልና በዘላቂነት ማልማት፣ መንከባከብና ጥበቃ ማድረግ የውሃ ሥነ-ምሕዳር አገልግሎትን ከማሻሻል ባሻገር ለአካባቢው ማኅበረሰብ ተጨማሪ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን የሚያስገኝ በመሆኑ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል። ምክር ቤቱም በአዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።

ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር ማስፈጸሚያ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው። የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደርን በተፋሰስ ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ ስትራቴጂካዊ አመራር መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል። ምክር ቤቱም በአዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 13/2017 ዓ.ም

Recommended For You