አዲስ አበባ፦ በዘንድሮው በጋ ወቅት የተለያዩ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በመስኖ ለማልማት በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የጋምቤላ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳግም መላሽን ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በ2016 ዓ.ም በበጋ መስኖ ልማት በአነስተኛ አርሶ አደሮች እርሻ ከ3ሺህ 300 በላይ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የሰብልና ሆርቲካልቸር ምርቶችን ማምረት ተችሏል። በተያዘው ዓመት የምርት ዘመን 5ሺህ 868 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ለመሸፈን ታቅዶ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
ካለፈው ዓመት በተሻለ እቅዱ ከፍ ያለበት ምክንያት በግንባታ ላይ የነበሩና ነባሮቹ የመስኖ ልማት አውታሮች ተጠናክረው ወደ ሥራ የገቡበት መሆኑን አመልክተው፤ ከዚህም መካከከል ባሮ ፒንክዮ፣ ችቦኪር፣ ባዚየል፣ ኖር፣ ጊሎ ፖቻላ እና ኢሌይቾይ የመስኖ ልማት አውታሮች በዘንድሮ ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገቡ አቶ ዳግም ጠቁመዋል።
ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ የቦንጋ፣ የኩሚና ቶሊናቶካሊ ነባር የመስኖ ልማት አውታሮችን የማጠናከር ሥራ እንደሚሠራ ገልጸው፤ የተለያዩ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ማለትም በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ በርበሬ፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ሃብሀብና ሙዝ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አቶ ዳግም አውስተዋል።
ከሜካናይዜሽን ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ የሚገኙ ተግዳሮቶች እንዳሉ የጠቀሱት ምክትል ኃላፊው፤ በጋምቤላ የወይና ደጋና ቆላማ የአየር ሁኔታ በስፋት የሚስተዋል በመሆኑ ይህም ለሩዝና ለስንዴ ሰብሎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የመስኖ ልማት ሥራውን ቀደም ብለው የጀመሩ ወረዳዎች መኖራቸውን በማንሳት፤ በክልሉ የሚስተዋለውን የምርጥ ዘር እጥረት ችግር ለመፍታት ከግብርና ምርምር ተቋማት ጋር እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።
እንደ አቶ ዳግም ገለጻ፤ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቋቋም የተለያዩ አይነት የሰብል ምርቶችን ለማምረት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ በስፋት ለመሥራት ግብ ተቀምጧል።
በአሁኑ ጊዜም ከሰብል አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የኮምባይነር እጥረት በመኖሩ የሰው ጉልበት በመጠቀም ሰፊ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ያነሱት አቶ ዳግም፤ የበቆሎ፣ የሩዝ እና ሌሎች የሰብል ዓይነቶች እየተሰበሰቡ ያሉበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 13/2017 ዓ.ም