ዜና ሐተታ
ያይኔአበባ አስፋው ትባላለች፡፡ ትውልድና እድገቷ በአሁኑ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ከተማ ዙሪያ ወረዳ ነው፡፡ የተማረችው እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ ነው፡፡ ቀደም ሲል ይህ ነው የሚባል ሥራ አልነበራትም፤ የዕለት ምግቧን ለመቻል ሌት ተቀን መንገድ ላይ በሳፋ ሙዝ በመያዝ ከአርባ ምንጭ ከተማ ለሚገቡና ለሚወጡ መንገደኞች ትሸጥ ነበር፡፡
ያይኔአበባ ከልጅነቷ ጀምሮ ሥራ ወዳድና ለመለወጥ ጽኑ ፍላጎት ነበራት። አንድ ቀን የራሷን ሥራ ከፍታ ለበርካቶች የሥራ ዕድል እንደምትፈጥር ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ አልነበራትም። ይህን ሕልሟን እውን ለማድረግ የአርሶ አደር ማሳን በመከራየት የሙዝ ልማት ሥራ ጀመረች። ይህም ቢሆን በምትፈልገው ልክ ለውጥ ሊያመጣላት ባለመቻሉ ሥራ እንደምትወድና ዕድሉ ቢሰጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደምትለወጥ ለክልሉ የኢንቨስትመንት ቢሮ ተማፅኖዋን አሰማች። ጥረቷን የሚያውቁት አመራሮች ጥያቄዋን ተቀብለው፤ በአርባ ምንጭ ከተማ ዙሪያ 10 ሺህ ሄክታር መሬት እንድታገኝ አደረጉ። ዛሬ ላይ ባለሀብት ሆናለች፤ ወደፊትም ብዙ ሕልሞች አሏት።
ያይኔአበባ አስፋው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጸችው፤ የሥራ ፍላጎቴን በመመልከት የጋሞ ዞን የኢንቨስትመንት መምሪያ 10 ሺህ ሄክታር የኢንቨስትመንት ቦታ ሰጥቶኛል። በ10 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቀደም ሲል ቲማቲም በማምረት ተጠቃሚ መሆን ችያለሁ። አሁን ላይ የሙዝና ሀባብ ምርት በስፋት አመርታለሁ። ቀደም ሲል ቲማቲም በ10 ሄክታር መሬት ላይ በማልማት እስከ ቶጎጫሌ በመላክ እስከ 32 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቷን ገልጻለች። በአሁኑ ጊዜም በድምሩ 40 ሚሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግባለች።
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ላይ ምርቷን በማቅረብ ለዋጋ መረጋጋት የበኩሏን አስተዋፅዖ መወጣቷን ገልጻለች። የማለማው የሙዝ ዝርያ የተዳቀለው በመሆኑ ውጤታማ ነው ትላለች።
ቀደም ሲል በመንገድ ላይ ሙዝና ማንጎ ትሸጥ እንደነበር የምታስታወስው ያይኔ አበባ፤ ሙዝና ማንጎን ለመንገደኞች በመሸጥ የዕለት ጉርስን ለማግኘት ትግል ነበር። ነገር ግን ባለፉት አምስት ዓመታት የኢንቨስትመንት ቦታ በማግኘቴ ከፍተኛ ገቢ እያገኘሁ ነው። የኑሮ ደረጃዬ በሚገባ ተሻሽሏል። ቀደም ሲል ተከራይቼ ነበር የምኖረው፤ አሁን ዘመናዊ ቪላ ቤት ገንብቻለሁ። እንዲሁም በአርባ ምንጭ ከተማ አራት ቦታዎችን አፍርታለች። ለማረስ፤ መከስከሻና ቦይ ለማውጣት አገልግሎት የሚውል የግሏ ትራክተር አላት። ምርቷን ለማጓጓዝ ሲኖትራክ መኪና ገዝታለች።
ሥራ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ለበርካታ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረችው አልሚዋ፤ አሁን ላይ 62 ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሏት። ከእነዚህ ውስጥ 12ቱ በግብርና የተመረቁ ናቸው። ከዚህ ቀደም ግብርና የወንድ እንጂ የሴት ነው የሚል አስተሳሰብ ባለመኖሩ በዘርፉ ብዙ ሴቶች ሲሰማሩ አይስተዋሉም። ነገር ግን ከለውጡ ወዲህ ለሴቶች በተሰጠው ትኩረት ብዙ ሴቶች በግብርናው መስክ በመሰማራት እራሳቸውን ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት በማላቀቅ ለብዙዎች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ነው ስትል ትገልፃለች።
ከባዱ ሥራ ግብርና ነው የምትለው በግብርና ተሰማርታ ውጤታማ የሆነችው ያይኔአበባ፤ ለሁሉም ሥራ ብርታትና ሥራ ወዳድነት መሠረታዊ ነው። ከሙዝ በተጨማሪ በብዛት ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያና የአበሻ ጎመን አመርታለሁ። በቀን ውስጥ ለመሥራት ያሰብኩትን ሳላሳካ ወደ ቤት አልገባም፤ የእርሻ ልማቴን ለአፍታም ቢሆን አልነጠለውም። እስከ ምሽት ስድስት ሰዓት ድረስ በሥራ የማሳልፍበት ጊዜ አለ። ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለመውጣት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸውም ትመክራለች።
ሴቶች የራሳቸውን ሥራ እንዲጀምሩ ድጋፍ እያደረኩ ነው የምትለው ያይኔአበባ፤ ተቀጥረው ለሚሠሩ ሴቶች የሙዝ ችግኝ እየሰጠሁ ነው። ወደፊት ከቅጥር ሥራ ተላቀው የራሳቸው የሙዝ ልማት እንዲኖራቸው ለማድረግ ምክር ጭምር እሰጣለሁ። ለአርሶ አደሮች የተዳቀለውን የሙዝ ዝርያ በመስጠት ማኅበራዊ ኃላፊነቴን እየተወጣሁ ነው ስትል ትገልጻለች።
የተዳቀለው የሙዝ ዝርያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለገበያ መቅረብ ይችላል። እንዲሁም ምርታማ ነው፣ ሥራው እንደሌሎች የሙዝ ዝርያዎች አድካሚ አይደለም። ውሃን ለረጅም ጊዜ የመያዝ አቅም ስላለው ድርቅን እንደሚቋቋም ገልጻለች። ወደፊት በአርባ ምንጭ ከተማ ትልቅ የገበያ ሞል የመገንባት እቅድ አለኝ፤ አሁን ላይ ለክልሉ መንግሥት ጥያቄዬን አቅርቤያለሁ ብላለች።
ሞገስ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 13/2017 ዓ.ም