በኢትዮጵያ ለጨርቃጨርቅ ግብዓቶች ተስማሚ ከሆነው መሬት 30 በመቶው ብቻ ለምቷል

– በስድስት ዓመታት የጨርቃጨርቅ ወጪ ንግድ ገቢን አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዷል

አዲስ አበባ፡- የጨርቃጨርቅ ምርት ግብዓቶችን ለማምረት ምቹ ከሆነው መሬት 30 በመቶ ብቻ ማልማት የተቻለ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ። እ.ኤ.አ በ2030 የኢትዮጵያን የጨርቃጨርቅ ወጪ ንግድ ገቢን አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ መታቀዱም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከኪንግ ደም ግሩፕ ሆልዲንግ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት “ዓለም አቀፍ የበፍታህ ጨርቃጨርቅ ፎረም 2024”ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ምርት ግብዓቶችን ለማልማት ተስማሚ የሆነ ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት አላት። ኢትዮጵያ ለጨርቃጨርቅ ምርት ግብዓቶች ተስማሚ ከሆነው ከአምስት  ሄክታር መሬት ውስጥ ማልማት የቻለችው 30 በመቶ ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ያላት ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት በዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅ ኢንቨስትመንት ተመራጭ እያደረጋት መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በሚፈለገው ደረጃ በማልማት ጥቅም ላይ ማዋል እና ተመራጭነቷን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ወጪ ንግድ ካለፉት ጊዜያት መሻሻል ማሳየቱን አመልክተው፤ እ.ኤ.አ. በ2030 የኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ወጪ ንግድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ሲሆን፤ መንግሥትም የግሉን ሴክተር ለማበረታታት ምቹ የንግድ ከባቢን የመፍጠር እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቀዋል።

አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን የመክፈት፣ የተከለከሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን የመፍቀድ እንዲሁም የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች አዋጅ የማፅደቅ፣ በሎጂስቲክስ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎት፣ በነፃ ንግድ እና በሌሎች ዘርፎች ላይ የግል ሴክተሩን የሚያበረታቱ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ የተካሄደው ዓለም አቀፍ የበፍታህ ጨርቃጨርቅ ፎረም የኢትዮጵያን ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ እድገት ራዕይ ለመግለፅ እና በጨርቃ ጨርቅ ዘርፎች ውስጥ ያሉትን ልዩ ዕድሎች ለማስተዋወቅ ወሳኝ መድረክ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ያላት የአየር ንብረት እና የአፈር ሁኔታ ለተልባ ምርት ተስማሚ በመሆናቸው በማደግ ላይ ባለው ጨርቃጨርቅ ገበያ ውስጥ ተሳታፊ እንድንሆን ዕድል ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል።

በኪንግደም ኢትዮጵያ ድርጅት የሎጂስቲክስ ማናጀር ቤተልሔም ቃሲም በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኪንግደም ኢትዮጵያ የተልባ ግንድን ወደ ክር ቀይሮ የሚያመርት በአፍሪካ የመጀመሪያው ድርጅት ነው።

ድርጅቱ የተልባ ግንድን ከፈረንሳይ አስመጥቶ ለሽመና አገልግሎት የሚውል ሊነን የሚባል ክርን አምርቶ ወደ 27 የተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚልክ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሊነን ክር ለዓለም ሀገራት ለማስተዋወቅ እና ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሀገር መሆኗን ለማስተዋወቅ የሚረዳ ዓለም አቀፍ የበፍታህ ጨርቃጨርቅ ፎረም አዘጋጅተን በአዲስ አበባ አካሂደናል ብለዋል። ፋብሪካው ሥራ ከጀመረ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ለአንድ ሺህ 200 ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የፋብሪካውን ጥሬ እቃ ለማምረት ምቹ የተፈጥሮ ሀብት ያላት በመሆኑ በሀገር ውስጥ ለመተካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ህዳር 13/2017 ዓ.ም

Recommended For You