“የስታርት አፕ” ምሰሶዎች

ዜና ትንታኔ

“ስታርት አፕ” ኢትዮጵያ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ የተመቸ ከባቢን በመፍጠር ችግር ፈቺ የሥራ መስኮችን ለመክፈት ያለመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጋቢት 2016 ዓ.ም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ስታርት አፖች ከ50 እንደማይበልጡ አውስተው፣ አሁን ላይ ከ900 በላይ ስታርት አፖች መኖራቸውን ነው የተናገሩት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ወጣቶች በፈጠራ ሃሳብ የተሞሉ የሀገሪቱ አንቀሳቃሽ ሞተሮች መሆናቸውን በመቀበል ሀሳባቸውን ወደ ተግባር የሚለውጡበት የዘርፉ ፖሊሲ ድጋፍም እጅግ አስፈላጊ ነውም ብለዋል፡፡

በተለይ በቀደሙ ጊዜያት የነበሩ የአሠራር ማነቆዎች፣ የሚገጥሟቸውን የፋይናንስ እጥረት በማስወገድ በሥራ ሂደት የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ መቶ በመቶ ለራሳቸው እንዲጠቀሙ እንዲሁም ምርቶቻቸውን በቀላሉ የሚሸጡበት የኢ-ኮሜርስ ዕድል ተመቻችቷል ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡

በቅርቡም 16ኛው የዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት በኢትዮጵያ ከኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ሁነቶች መካሄዱን ቀጥሏል፡፡ ይህ ጅማሮ ታዲያ በኢትዮጵያ በኢኮኖሚው፣ በቴክኖሎጂ እና በዲጂታሉ ዘርፍ ሁለንተናዊ እንዲሁም ዘላቂ ለውጥ እንደሚያመጣ የስታርት አፑ ዘርፍ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል፡፡

በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች (“ስታርት አፕ”) በተለይ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው የዘርፉ ምሑራን ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ ስታርት አፕን ለማሳደግና በዘርፉ የሚገኘው ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምን መደረግ አለበት ሲል ኢፕድ የዘርፉ ተዋናዮችን አነጋግሯል፡፡

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ሀብታሙ ለገሠ እንደሚሉት፤ ስታርት አፕ የሥራ ባሕል የሚቀይር፣ አዲስ የኢኮኖሚ ዓውድ የሚፈጥር፣ በቀላሉ ማደግና መስፋፋት የሚችል፣

የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታ፣ ቴክኖሎጂን መርሕ ያደረገ እንዲሁም ዓለም አቀፍም መሆን የሚችል ዘርፍ ነው ይላሉ። የስታርት አፑ ዘርፍ የሀገሪቱ የወደፊት ዋነኛው የኢኮኖሚ ዋልታነቱን ለማስመስከርም የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ሥልጠና፣ የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ መጠናከርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ትግበራ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ ።

በተለይ የካፒታል ገበያ የስታርት አፕ ምሰሶ ነው የሚሉት ተመራማሪው፤ ካፒታል ገበያ ገንዘብ ያላቸው አካላትና ሃሳብ ያላቸው አካላት የሚገናኙበት ነው። ስታርት አፕ በሀገር ኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ከሚያስገኘው ተጠቃሚነት ጎን ለጎን የውጭ ምንዛሪም ለማስገኘት፣ ሌሎች ተቋማት አምራች እንዲሆኑ እንዲሁም ወጣቶች በቀጥታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ውስጥ እንዲቀጠሩ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት።

ኢንቨስትመንት ባንክ ተቋቁሞ ስታርት አፖች በካፒታል ገበያው ላይ እንዲካተቱ ከተደረገ፣ በቅንጅት መሥራት እንዲሁም የአሠራር ሥርዓቱ ማዘመን ከተቻለ የተሻለ ውጤት ማግኘት የሚቻልበት ቢሆንም በዓለም ባለው ልምድ 90 በመቶ ውጤታማ ላይሆን የሚችልበት ሁኔታ በመኖሩም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋልም ባይ ናቸው።

እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ ከዚህ በፊት ባለው ልምድ የቢዝነስ ሃሳብ ያላቸውና ጀማሪ ሰዎች ያለ ማስያዥያ ብድር ሊያገኙ አይችሉም። ሀብት ያላቸው ሰዎች ብቻ ተጨማሪ ሀብት እንዲሠሩ የሚያበረታታ ነበር፤ ለአብነትም ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ከተሰጠ ብድር 23 በመቶ የሚሆነው አስር ተቋማትና ግለሰቦች ብቻ መውሰዳቸውን የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ያሳያል።

ኢትዮጵያ አዳዲስ ቢዝነስ ለመጀመር ከሚያበረታቱ ሀገራት በዓለም 159ኛ ደረጃ ላይ እንደሆነች መረጃዎች ይጠቁማሉ የሚሉት ተመራማሪው፤ ፈቃድ ለመውሰድ ያለው እንግልት፣ ቢሮክራሲ፣ ሙስናና ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከሚፈጥሩ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ያመላክታሉ።

ለስታርት አፕ አዲስ ጅማሮ በመሆኑ የበለጠ ከባድ እንዳይሆን የተለያዩ ማሻሻያዎችና የአሠራር ሥርዓቶች ቀድሞ መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።

የስታርት አፕ ዘርፉን ለማሳደግም የስታርት አፕ ጉዳዮችን ብቻ የሚያይ ተቋም መመሥረት ካለም አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ግንዛቤ መፍጠር፣ ሃሳቦችን የሚያስተናግድ በየክልሉ ቢሮ መክፈት፣ ሥልጠና መስጠት እንዲሁም በጀት የሚመቻችበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በ16ኛው የዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለስታርት አፖች የሚሆን ግልጽ የፖሊሲ እና የፋይናንስ ድጋፋ ማሕቀፍ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ነው።

የተለወጠች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንዲቻል በፈጠራ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ማሳደግ የግድ ይላል የሚሉት በለጠ (ዶ/ር)፤ የስታርት አፕ ዘርፍ ማጎልበት ለዚህ ወሳኝ መሆኑን ይጠቁማሉ።

የተሻለ ሀገር ለመገንባትም በፖለቲካል ኢኮኖሚ ውጤታማ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት ልምድ መውሰድ ተገቢ ስለመሆኑ ያክላሉ።

እንደ በለጠ (ዶ/ር) ገለጻ፤ በስታርት አፑ ዘርፍ ለሥራ ፈጣሪው በፖሊሲ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር የቻሉ ሀገራት የተሻለ ኢኮኖሚ ማስመዝገብ ችለዋል። ሥራ ፈጣሪው ሃሳቡን አደራጅቶ ወደ ሥራ መግባት የሚችልበትን ዓውድ ማመቻቸት እንዲሁም አስፈላጊውን ሀብትና የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

በለጠ (ዶ/ር)፤ የትኛውም ዘርፍ በቴክኖሎጂ መደገፍ ካልተቻለ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደማይቻል ጠቅሰው፤ የስታርት አፕ ዘርፉ ሀገሪቱ ወደ ኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማስገባት የሚችል ነው ይላሉ።

የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ መጠናከር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚና ፈጠራ ዘርፍ መጎልበት ከፍተኛ ሚና አለው የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል ናቸው።

የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ መጠናከር የውጭ ኢንቨስትመንት ከማሳደግ ጎን ለጎን በየዘርፉ ፈጠራ ላይ ለተሰማሩ ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግና ለፈጠራ እንዲነሳሱ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑንም ነው የሚያስረዱት።

በተለይ ስታርት አፕ ከፍተኛ የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ የሚሻ ነው የሚሉት አቶ ወልዱ፤ የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባው በተጠናከረ ቁጥር የሥራ ፈጣሪዎች የማበረታታት ዕድል አለው።

በተጨማሪም በስታርት አፑ ዘርፍ የሚሰማሩ አካላትም የባለቤትነት መብቱ አግኝተው በፍጥነት የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበት ዕድል መመቻቸቱን ያብራራሉ።

እንደ አቶ ወልዱ ገለጻ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ኢኮኖሚ የገነቡ ሀገራት በአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባቸው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ናቸው። በተፈጥሮ ሀብት ብቻ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ መወዳደር አይቻልም፤ የአዕምሯዊ ንብረት በማይዳሰስ ሀብት ውስጥ ሆኖ ከፍተኛ ልዩነት እየፈጠረ ያለ ዘርፍ ነው።

መንግሥት ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን /ስታርት አፖችን/ በተሻለ ሕግና የአሠራር ሥርዓት ለመደገፍ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገለጹት የ’’ስታርት አፕ ኢትዮጵያ’’ ፎረም በዓድዋ ድል መታሰቢያ መጋቢት ወር ላይ በተካሄደበት ወቅት ነው።

በወቅቱም የአይሲቲ ዘርፍ ከአምስቱ የብዝኃ ኢኮኖሚ አዕማዶች አንዱ ሆኖ በትኩረት እንዲሠራበት መደረጉ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን /ስታርት አፖችን/ ለማበረታታት የተወሰደ እርምጃ ማሳያ መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ከለውጡ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ስታርት አፖች ከ50 እንደማይበልጡ ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ከ900 በላይ ስታርት አፖች መኖራቸውን ነው የተናገሩት።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ህዳር 13/2017 ዓ.ም

Recommended For You