- የማዕድን ሀብታችንን በአግባቡ ብንጠቀም ኢትዮጵያ የበለጸገች ትሆናለች
አዲስ አበበ፡- የማዕድን ሀብታችንን በአግባቡ ብንጠቀም ኢትዮጵያ የበለጸገች ትሆናለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋምቤላ ክልል የተገነባውን ኢትኖ ማይኒንግ የወርቅ ፋብሪካ ትናንት መርቀው ከፍተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ከለውጡ በኋላ መንግሥት ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።፡ በዚህ ዓመትም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወርቅ ብቻ እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ይህ እቅድ ኢትዮጵያ ካላት ሀብት አንጻር በጣም ውስኑ ነው፡፡ በርትተን ብንሠራ፣ ለጠላት መሳሪያ ባንሆን፣ የማዕድን ሀብታችንን ብንጠቀም፣ ሰላማችንን ብንጠብቅ ኢትዮጵያ ለማኝ ሳትሆን ሰጪ፤ ችግርተኛ ሳትሆን የበለጸገች ሀገር ትሆናለች ብለዋል፡፡
መንግሥት ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት የበለጸገች ሀገር መሆኗን በመረዳት ያላትን ጸጋ ወደ ልማት ለመለወጥ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የግሉ ሴክተር በማዕድን ዘርፍ ላይ እንዲሳተፍም ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ገልጸው፤ በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ የኢትኖ ማይኒንግ የወርቅ ፋብሪካ አንዱ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዲማ የወርቅ ንግድ ያለባት ቦታ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ላለፉት 30 ዓመታት ወርቅ በባህላዊ መንገድ እየወጣ ጥቅም ላይ መዋሉ የጋምቤላ ክልል በወርቅ ሀብት የደረጀ መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በባህላዊ መንገድ የምናወጣው የወርቅ ሥርዓት አብዛኛው ብክነት ነው፡፡ በገበያ ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን የአወጣጥ ሥርዓቱ በራሱ ከአንድ ቶን ሊገኝ የሚገባውን ወርቅ አናገኝም፡፡ ጥቂት አግኝተን አብዛኛው ይባክናል ብለዋል፡፡
የኢትኖ ማይኒንግ የወርቅ ማምረቻ ሥራ መጀመር ይባክን የነበረውን ወርቅ ወደ ጥቅም ለመቀየር፣ በወርቅ ንግድ የሚስተዋለውን ሕገወጥነት ለማስቀረት እና ሌሎች በርካታ ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኝ አስታውቀዋል፡፡
በዲማ አካባቢ በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ ሰዎች ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርገውን ኢትኖ ማይኒንግ የወርቅ ፋብሪካ የገበያ ማዕከላቸው ሊያደርጉ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ኢትኖ ማይኒንግ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ፋብሪካውን ገንብቶ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ እንደዚህ ዓይነት ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ፋብሪካው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃም ዘመናዊ በመሆኑ ከአንድ ቶን የምናመርተው የወርቅ መጠን ከየትኛውም የአፍሪካ ሀገር ከሚመረተው ከፍ ያለ ምርት ይገኛል ነው ያሉት፡፡
እንደዚህ ዓይነት ዘመናዊ ፋብሪካ ይባክን የነበረውን ወርቅ ለማምረት እና ወደ ገበያ ለማውጣት ያግዛል። አሁን የተመረቀው ፋብሪካ አቅም ስላለ በአጭር ጊዜ ውስጥ የወርቅ ምርቱን ሁለትና ሦስት እጥፍ ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
ይህ አዲስ ኢንቨስትመንት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ እና ደረጃውን የጠበቀ የወርቅ ምርት ከማስገኘቱም በላይ በሕገወጥ የማዕድን ሥራ ለተጋረጠው ፈተና ምላሽ ይሰጣል ብለዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ለጋምቤላ ክልል ያለውን እምቅ ሀብት ለሕዝቡ እና ለክልሉ ጠቀሜታ የማዋል፤ ያለውንም ተነሳሽነት የሚያሳይ በመሆኑ፤ ፋብሪካውን መጠበቅ እና እንዲስፋፋ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ፋብሪካው የመጀመሪያችን እንጂ የመጨረሻችን አይሆንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቅርቡም ተጨማሪ ፋብሪካዎችን እናስመርቃለን ሲሉ ተናግረዋል።፡
በጋምቤላ ክልል በዲማ ወረዳ የለማው ትልቅ ኢንቨስትመንት ለጋምቤላም ሆነ ለኢትዮጵያ ትልቅ ሲሳይ ስለሆነ ሁላችንም እንኳን ደስ አለን ብለዋል፡፡
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ኅዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም