በሳንኩራ ወረዳ የገተም ጉርቤ ሁለተኛ ደረጃ መምህር ነው:: መምህር ሮባ ሙክታር:: ይህ ወጣት መምህር ለሲሚንቶ ማቡኪያ የሚያገለግል ማሽን ፈጥሯል:: የፈጠራ ባለሙያው ለሲሚንቶ ማቡኪያ የሚያገለግለውን ማሽን የሠራው የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም ነው:: ማሽኑን ለመሥራት ያነሳሳው የሀገሪቱ የግንባታ ማሽን ፍላጎት በመጨመሩ እና የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት አስቦ መሆኑን ይናገራል::
የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑን ለመሥራት አንድ ወር ጊዜ ብቻ ፈጅቶብኛል የሚለው መምህር ሮባ፤ አሁን ላይ ማሽኑን ሥራ ተቋራጮች እየተጠቀሙበት ነው:: ማሽኑን በቀላሉ በእጅ በማንቀሳቀስ እና በኤሌክትሪክ መጠቀም እንደሚቻልም ያስረዳል::
መምህር ሮባ ከራሱ አልፎ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲሠሩ ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ ተግባር ተኮር ትምህርት እንደሚያስተምራቸው ይናገራል:: ሌሎች መምህራንም ንድፈ ሀሳብ ብቻ ከማስተማር ይልቅ ተግባር ተኮር ትምህርቶችን ለተማሪዎቻቸው እንዲያስተምሩ መልእክቱን ያስተላልፋል::
ኢትዮጵያ የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑን ከውጭ በዶላር ገዝታ የምትጠቅም መሆኑ ይታወቃል የሚለው መምህሩ፤ በሀገሪቱ ግንባታ እየተስፋፋ በመሆኑ ማሽን መጠቀሙ የግድ መሆኑን ገልጿል::
ፋሲካ ታደሰ ትባላለች:: የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት:: በእጅ የሚሠራ የለውዝ መፈልፈያ ማሽን ሠርታለች:: በአካባቢዋ የሚገኙ እናቶች በብዛት የሚተዳደሩት ለውዝ በመፈልፈል ነው:: ተማሪ ፋሲካም በአካባቢዋ የሚገኙትን እናቶች ሥራ ሊያቀል የሚችል ማሽን ሠርታለች::
ማሽኑን ለመሥራት የተጠቀመቻቸው ግብዓቶች በቀላሉ በአካባቢዋ የሚገኙ እና ሁለት ወር ጊዜ መፍጀቱን ገልጻ፣ ማሽኑ ለአጠቃቀም ቀላል እና በአንድ ጊዜ ብዛት ያለው ለውዝ መፈልፈል እንደሚችል ታስረዳለች::
ሌሎች ተማሪዎችም በመደበኛው የትምህርት ጊዜ ከሚያገኙት የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ባለፈ በእስቴም ማዕከላት በመግባት የተግባር ትምህርቶችን መከታተል እንዳለባቸው መልእክቷን ታስተላልፋለች::
ሌላኛው የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን የሠራው ተማሪ ዑመር ዓሊ ሲሆን፤ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነው:: ኢትዮጵያ በወተት ምርት ዝቅተኛ ከሚባሉ ሀገራት መካከል ናት:: ዝቅተኛ የሆነችበት ዋናው ምክንያትም የተመጣጠነ የመኖ አቅርቦት ባለመኖሩ ስለሆነ የመኖ ማቀነባበሪያ መሥራት ችያለሁ ይላል::
በቀላሉ በአካባቢው ያገኛቸውን ግብዓቶች ተጠቅሞ ማሽኑን የሠራው በሁለት ወር ጊዜ ሲሆን፤ ማሽኑ በሰዓት አምስት ኩንታል መኖ ማምረት ያስችላል:: የአካባቢው ማኅበረሰብ ማሽኑን በመጠቀም የእንስሳት መኖ እጥረትን መቅረፍ እንደሚችሉ ያስረዳል::
በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የሀገርን ዕድገት የሚያሳልጡ እና ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን የሚሠሩ በርካታ ተማሪዎችን ለማፍራት እየተሠራ ይገኛል::
የፈጠራ ሀሳብ ባለቤቶች በሀገሪቱ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሉ መልካም ዕድሎችን በመጠቀም ሀሳቦቻቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ መልካም ዕድል እየተፈጠረ በመሆኑ ተማሪዎችና መምህራን ዕድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል ነው ያሉት::
በእስቴም ፓወር ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ እስቴም ፓወር ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የኢንጂነሪንግ፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ሂሳብ (እስቴም) ማዕከላትን በማቋቋም ተማሪዎች የተግባር ትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እያስቻለ ነው::
ለተማሪዎች ተግባር ተኮር ትምህርቶችን በማስተማር የአካባቢያቸውን ችግሮች ቴክኖሎጂን እና የፈጠራ ሀሳቦችን ተጠቅመው መፍታት እንዲችሉ የማድረግ ሥራዎችን በትኩረት ነው ይላል::
ዘጠነኛው ሀገራዊ የሳይንስ እና የምሕንድስና ፈጠራ ሥራዎች ውድድር በመምህራን እና በተማሪዎች መካከል መደረጉን ገልጸው፤ አሸናፊዎች ተለይተው በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑ ገልጿል::
ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት እንዲችሉ፣ መፍትሔ የማፈላለግ እና ውሳኔ የመስጠት ልምምድን እንዲያዳብሩ ጥረት እየተደረገ ይገኛል:: የትምህርት ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሀገራዊ የሳይንስና የምሕንድስና ቀን በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል::
ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ እስቴም ማዕከላት እና በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ከየክልሉ ተወዳድረው ያሸነፉ ተማሪዎች እና መምህራን የፈጠራ ሥራ ውድድር ዐውደ ርዕይ ላይ ተሳትፈዋል::
ተማሪዎች የሚሠሩትን የፈጠራ ሥራዎች ተግባር ላይ ለማዋል እና ወደ ገበያ ለማስገባት የሚያስችል ማዕቀፍ መኖሩንም ያመላክታሉ::
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም