ልዩ ምርመራ ቢፈቀድ የሰዎችን መብት ሊጥስ ይችላል – ተወያዮች

ልዩ ምርመራ ከተከለከለ ወደ ፍርድ ቤት የምናደርሰው ጉዳይ አይኖርም ፍትሕ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ :- ‹‹በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል›› ረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ አስቻይ ያልሆኑ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ሁኔታ ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጭ ልዩ ምርመራ እንዲፈቀድ የተቀመጠው ድንጋጌ በምክር ቤት ጥያቄ አስነሳ፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር በበኩሉ ከልዩ ምርመራ ጋር ተያይዞ በድንጋጌው እንደተካተተው የእግድ ሁኔታ አሁን በረቂቅ አዋጁ በሰፈረው መልኩ የማይቀመጥ ከሆነ ወደ ፍርድ ቤት የምናደርሰው ጉዳይ (ወንጀል) አይኖርም ብሏል፡፡

በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ተብሎ የነበረው ስያሜ ግልጽ ማድረግ በማስፈለጉ ‹‹በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል›› በሚል እንዲቀየር መደረጉን የረቂቅ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

ረቂቅ አዋጁን በሚመለከት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው ሕዝባዊ ውይይት፤ ልዩ ምርመራ ቢፈቀድ የሰዎችን መብት ሊጥስ፣ አላስፈላጊ የኢኮኖሚ ልውውጦችን የማገድ እና እና ጣልቃ ገብነትን ሊያበረታታ የሚችል ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችል ስጋት ተነስቶበታል፡፡

ከዚህ መነሻነትም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከልዩ ምርመራ ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮች በደንብ ሊታዩ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር የተወከሉት ዋለልኝ አምባነህ እንደገለጹት፤ ልዩ ምርመራ በፍርድ ቤት ፍቃድ እስከ 90 ቀናት የሚፈቅድ ሃሳብ በረቂቅ አዋጁ ተቀምጧል፡፡ በፍርድ ቤት መፈቀዱ ተገቢ ቢሆንም ጊዜው ስለሚበዛ እንዲታይም አሳስበዋል፡፡

የአንድ ተጠርጣሪ ቤቱን፣ ኮምፒውተሩንም ሆነ ሌሎች ነገሮችን ለመመርመር ይህንን ያህል ጊዜ የማይፈጅ መሆኑን በመገንዘብ በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው ጊዜ ማጠር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ አሁናዊ የዲጂታል እና የኢኮኖሚ ሁኔታን የሚመጥን ሲሆን ባግባቡ ሊታይ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡ ከሀገር ደኅንነት፣ ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ቀጣና አንጻር እና ከሽብርተኝነት አዝማሚያ ጋር ሊቃኝ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ የምርመራ ሥራን እና እግድን ለፍርድ ቤት ብቻ መስጠት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ምርመራ ራሱን የቻለ ሕግና እና ሥርዓትን ተከትሎ በፍርድ ቤት በአስቸኳይ ሊደረግ የሚችልበትን ሥርዓት መዘርጋት ይገባል ያሉት አቶ ዋለልኝ፤ በረቂቅ አዋጁ ልዩ ምርመራ ማካተት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አሸነፈች አበበ በበኩላቸው፤ ከምርመራ ሥራ ጋር ተያይዞ የፍርድ ቤትን ጉዳይ እየሸራረፉ ለዐቃቤ ሕግ የመስጠት ሁኔታ ይስተዋላል ብለዋል:: በመሆኑም ረቂቅ አዋጁ ከዚህ ጋር ተያይዞ ባግባቡ ሊታይ እንደሚገባ አሳስበዋል::

ሕጎች ሲዘጋጁ ጥራታቸውን ጠብቀው ቢያንስ አስር ዓመታት ያህል ሊያገለግሉ የሚችሉ ሆነው ሊዘጋጁ እንደሚገባና በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል የሕግ ዝግጅትም ባግባቡ ታይቶ መዘጋጀት እንዳለበትም ነው የተናገሩት::

ለፖለቲካ ተፅዕኖ የተጋለጠ በሚል በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው ድንጋጌ ከባድ ትርጓሜ መሆኑን አንስተዋል:: እየተነሳ ያለው የወንጀል ጉዳይ ነው፣ ወንጀል ደግሞ በባሕሪው ግላዊ በመሆኑ ‹‹ለፖለቲካ ተፅዕኖ የተጋለጠ ሰው፣ ቅርብ ቤተሰቡና ማንኛውም ሰው” በሚል የተቀመጠው ግልጽ ሆኖ ሊቀመጥ ይገባዋል ብለዋል::

ለምርመራ ተብሎ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ጥሩ ሆኖ ሳለ በበቂ ጥርጣሬና ምክንያት የተያዘን ሰው አራት ወራት ያህል ማቆየቱ ተገቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል::

በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጄኔራል አዲስ ጌትነት በበኩላቸው፤ ልዩ ምርመራ ጋር ተያይዞ በድንጋጌው መካተቱ በወንጀል የተገኘን ሃብት በሚመለከት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የእግድ ሁኔታ አሁን በረቂቅ አዋጁ በተቀመጠው መልኩ የማይቀመጥ ከሆነ ወደ ፍርድ ቤት የምናደርሰው ሁኔታ አይኖርም፣ ብዙ ጉዳዮችን እናጣለን ብለዋል::

ይሄ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ሲኖሩ በልዩ ሁኔታ የተመላከተባቸው እንጂ፤ በመርሕ ደረጃ የሚሠራበት አይደለም ብለዋል:: አስቻይ ያልሆኑ ሁኔታዎች አሉ ብለዋል::

እንደዓቃቤ ሕግ የሚሠራው በዋናነት ፍትሕን የማረጋገጥ ሥራ ነው ያሉት አቶ አዲስ፤ እንደዓቃቤ ሕግና ፖሊስ ሥራችንን ስንሠራ ሰብዓዊ መብትን በጠበቀ አግባብ ሆኖ፤ በዚህ ሂደት ግን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚለው መረሳት የሌለበት ነው ብለዋል::

የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቴ፤ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነው፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢኮኖሚ ወንጀሎች በጣም ውስብስብ ናቸው ብለዋል:: በዚህ ዘርፍ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች ከሽብርተኞች ጋር ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ የእነዚህ አካላት እንቅስቃሴ እንዲገታ ረቂቅ አዋጁን በዚህ ልክ መገንዘብና መተባበር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል::

ዘለላም ግዛው

አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You