ለማየት ከሚጓጉ ሰዎች የተወሰኑትን የብርሃን ወጋገን ያሳየ ተቋም ነው፡፡ ዘንድሮ 21ኛ ዓመቱን የሚያስቆጥረው የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር በአሕጉራችን ካሉ ሀገራት አኳያ የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማም በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት ማየት የተሳናቸውን ዜጎች መልሰው ብርሃን እንዲያገኙ ማድረግ ነው:: ይህ ዓላማውን ለማሳካትም ከለጋሽ ወገኖች ከኅልፈት በኋላ ብሌን በማሰባሰብ፣ ጥራቱንና ደኅንነቱን ጠብቆ ለንቅለተከላ ሕክምና ማዘጋጀት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
በጤና ሚኒስቴር የተደረገ ጥናትም በኢትዮጵያ ከ300 ሺ በላይ ዜጎች ከዓይን ብሌን ጠባሳ ጋር በተያያዘ ዓይነ ስውራን እንደሆኑ ይጠቁማል::
የኢትዮጵያ የደምና ኅብረሕዋስ ልገሳ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ በዛብህ እንደሚሉት፤ የዓይን ባንክ በኢትዮጵያ ሲቋቋም በባለሙያውም በኅብረተሰቡም ዘንድ የተለያዩ ስጋቶች ነበሩ:: ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣት በርካታ ወገኖች የዓይን ብርሃናቸውን ማግኘት እንደቻሉ ጠቁመዋል::
ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከሦስት ሺህ 500 በላይ ለሆኑ ሰዎች የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ በማድረግ ማየት እንዲችሉ ማድረጉን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ከ15ሺህ በላይ ሰዎችም ከኅልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመስጠት የቃል ኪዳን ሰነድ መፈረማቸውን ያስረዳሉ፡፡
ከዓይን ብሌን ጠባሳ ጋር በተያያዘ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ወገኖችን የዓይን ብሌን እንዲያገኙ ለማድረግ ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅም ይጠቁማሉ:: በቀጣይም የንቅለ ተከላ ባለሙያዎቹን እንዲሁም የዓይን ባንኩን ቁጥር ለመጨመር መታቀዱን ይጠቁማሉ:: ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ ኅብረተሰቡና ድርጅቶችም ይህንን የሕዝብ ባንክ በተለያየ መልኩ በመደገፍ ሀገራዊ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ይገልፃሉ፡፡
የዓለም የዕይታ ወርን በማስመልከትም የኅዳር ወር በሀገር አቀፍ ደረጃ የዓይን ብሌን ልገሳ ንቅናቄ ወር ተደርጎ እንደሚውል አስታውሰው፤ ኅብረተሰቡ ከኅልፈት በኋላ የዓይን ብሌኑን ለመለገስ ቃል እንዲገባም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ደምና ኅብረሕዋስ ባንክ አገልግሎት የዓይን ባንክ መሪ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ዶክተር አምሳለ ጌታቸው በበኩላቸው የዓይን ብሌን ማለት የዓይናችን ጥቁሩ ላይ ያለው እንደ መስታወት የሚያንፀባርቀው ስሱ ክፍል ነው:: እንደ እርሳቸው አባባል የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የገቡ ሰዎች ሕይወት አልፎ ይህ የዓይናቸው ክፍል በሚወሰድበት ጊዜ ፊታቸው ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም ይላሉ፡፡
የዓይን ባንኩ የዓይን ብሌን የሚሰበስብባቸውን መንገዶች በተመለከተም አንደኛው መንገድ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገብተው የነበሩ ሰዎች በሚያልፉበት ጊዜ መሆኑን ይገልፃሉ:: ሁለተኛውና በዋነኛነት ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ያለው ደግሞ ከቤተሰብ ውስጥ የአንድ ቤተሰብ አባል ሕይወት በሚያልፍበት ጊዜ ሕይወቱ ያለፈ ሰው የቤተሰብ አባል የሆነ ሰው ወደ ዓይን ባንክ ደውሎ ብሌኑ እንዲወሰድ በሚፈቅድበት ጊዜ ነው ያሉት::
በሦስተኛነትም ሰዎች በሆስፒታል ታክመው ሕይወታቸው በሆስፒታል ውስጥ በሚያልፍበት ጊዜ ቤተሰቦቻቸው የዓይን ብሌናቸው እንዲወሰድ ፈቃደኛ ሲሆኑ መሆኑን ያስረዳሉ:: የዓይን ባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት በዳግማዊ ምኒሊክ ቅጥር ጊቢ ውስጥ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በሆስፒታል ውስጥ ከሞቱ ሰዎች የዓይን ብሌን የሚወሰድበት አሠራር በጳውሎስ፣ በራስ ደስታና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች ብቻ እንደሚከናወን ይገልፃሉ::
የዓይን ብሌን ለመውሰድም ከአስር እስከ አስራ አምስት ደቂቃ የሚፈጅ በመሆኑ የቀብር ሥነ ሥርዓትን እንደማያስተጓጉል ይጠቁማሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ወደ አስራ ሁለት የሚጠጉ የዓይን ብሌን ቀዶ ጥገና ሐኪሞች አሉ የሚሉት ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ሕክምናው አዲስ አበባ ውስጥ በዳግማዊ ምኒሊክና በአምስት የተለያዩ የግል ተቋማት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በክልል ከተሞች በሀዋሳ፣ በጅማ በመቀሌ እና በጎንደር ሕክምናው እየተሰጠ እንደሚገኝ ያብራራሉ:: ማኅበረሰቡም ችግሩን ተገንዝቦ የዓይን ብሌን በመለገስ የዓይን ብርሃናቸውን ላጡ ወገኖች ብርሃን እንዲመለስ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ነፃነት ዓለሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም