ዘውዴ መታፈሪያ በጠና ታሟል፤ መቀመጥ አቅቶታል። በሽታው ብዙ ከመቀመጥ እና በቂ ውሃ ካለማግኘት ጋር ተያይዞ የሚመጣው የኪንታሮት በሽታ ነው። ድርቀትን ተከትሎ የመጣበት ይኸው በሽታ እያሠቃየው ይገኛል። ገብረየስ ገብረማሪያም ይህቺን ሕመም በደንብ ያውቃታል። መንግሥቱም የአንድ ሰሞን ተጠቂ ነበር።
ሁለቱም ይህንን በሽታ መዳን የቻሉት ሐኪም የሚላቸውን ሰምተው በመፈፀማቸው ነው። ሁለቱም ውሃ መጠጣት፤ ጥራጥሬ እና ቴምር እንዲሁም ድርቀት እንዳይመጣ የሚከላከሉ ምግቦችን በመመገብ እና ቅባት በመቀነስ በተጨማሪ የተሰጣቸውን መድኃኒት በአግባቡ በመውሰዳቸው ከኪንታሮት በሽታ ተላቀቁ።
ዘውዴ ግን ሥራ ቀርቶ ቤት መዋል ከጀመረ ውሎ አድሯል። ገብረየስ እና መንግሥቱ ምንም እንኳ ቤታቸው ከዘውዴ በእጅጉ የራቀ ቢሆንም፤ ሕመሙ እንደፀናበት ሲሰሙ ሊጠይቁት ቤቱ ድረስ ሔዱ። ገብረየስ ገብረማሪያም እና መንግሥቱ፤ ዘውዴን በደንብ ተረድተውታል። ነገር ግን የዘውዴ ሕመም በጣም የከበደ መሆኑ ትንሽ ግር አሰኝቷቸዋል።
መንግሥቱ ገና እንደገባ፤‹‹ ወንድሜን ምን ነካህ? ›› አለው። ዘውዴ እንደምንም ከተኛበት ቀና ብሎ ‹‹ጋዜጠኞችን ሰምቼ ጉድ ሆንኩኝ›› እያለ ለሰላምታ እጁን ዘረጋ። ገብረየስም በበኩሉ፤ ‹‹አይዞን ! ምን ጉድ ነው ? … ይሔ ነገር ከባድ በሽታ ሆነብህ፤ ለመሆኑ ሕክምና ቦታ ሔደሃል?›› ሲል ጠየቀው።
ዘውዴ ሕክምና ቦታ ሄዶ ነበር። ነገር ግን ኪንታሮቱን ለማስወገድ ቀዶ ጥገና ያስፈልግሃል በመባሉ ሕክምናውን አቋርጦታል። ስለዚህ የሕክምና ክትትል አድርጌያለሁ ወይም አላደረግኩም ለማለት ተቸገረ። በግልፅ ሐኪም ቤት ሄዶ የተባለውን አልነገራቸውም። ‹‹የባሕል ሕክምና አድርጌያለሁ። ነገር ግን ከመሻል ይልቅ ጭራሽ ባሰብኝ። ›› ሲል ምላሽ ሰጠ።
መንግሥቱ በስጨት አለ። ‹‹አንተ የተማርክ እና ብዙዎችን የምታስተምር ሰው ሆነህ እንዴት የባሕል ሕክምና ለመውሰድ ተነሳህ?›› ሲል በቁጣ ድምፅ ጥያቄ አቀረበ። ዘውዴ አልጋ ላይ መቀመጥ እንኳ አቅቶት ነበር። ከዘውዴ ቀድሞ ገብረየስ ምላሽ ሰጠ። ‹‹የባሕል ሕክምና ምንም አያድንም ብለህ እንዳትከራከር። ›› ሲል ተግሳፅ በሚመስል ድምፅ ተናገረ።
መንግሥቱ ‹‹እንግዲህ እንደጋዜጠኞቹ ምርጥ የባሕል ሕክምና አለ፤ በሳንጃ የተወጋን እናድናለን፤ ለሰላቢ እና ለምቀኛም መድኃኒት አለን። እያልክ ማስታወቂያ ለምን አትሠራም?›› ሲል፤ ገብረየስ በመንግሥቱ ንግግር ሳያስበው ሳቁ አመለጠው። ዘውዴ ግን የመንግሥቱ ንግግር ቢያስቀውም ሕመሙ እንዲስቅ አልፈቀደለትም። ሳቁን ተቆጣጥሮ ፈገግ አለ።
ዘውዴ ከግራ ወደ ቀኝ የሚላወሰው በግድ ነው። መንግሥቱ እና ገብረየስ ሲያዩት ፈሩ እና ተያዩ። መንግሥቱ፤ ‹‹ እባክህ ጓዴ ሐኪም ቤት እንውሰድህ? ›› ሲል ጥያቄ አቀረበ። የዘውዴ ሚስት ተዋበች በፍጥነት፤ ‹‹ እባካችሁ… ሊሞት እኮ ነው። ሐኪም ቤት ውሰዱት። እኔ ሐኪም ቤት ይሻልሃል ማለት ከጀመርኩ ቆይቼያለሁ አልሰማ አለኝ። ›› ስትል አቤቱታ መሰል ሃሳብ በመሰንዘር ድጋፏን ገለፀች። ንግግሯ ባሏ ዘውዴ ሐኪም ቤት አልሔድም ብሎ እጅግ እንዳስቸገራት የሚያሳብቅ ነው።
ዘውዴ በበኩሉ ሐኪም ቤት መሔድ አልፈለገም። ነገር ግን የሚስቱ እና የጓደኞቹ ጭንቀት እርሱንም አስጨነቀውና ሐኪም ቤት ለመሔድ ተስማማ። ሚስቱ በፍጥነት ነጠላ ጫማ እና ጋቢ አቀረበች። መንግሥቱ እና ገብረየስ ዘውዴን ደግፈው ከአልጋ ላይ ሲያነሱ ሱሪው በደም ተጨማልቆ ነበር። መቀመጥ አቅቶት እንደምንም ሱሪውን ቀይሮ መኪና ውስጥ አስገቡት።
መንግሥቱ እና ገብረየስ በዘውዱ መታመም ይበልጥ ተሳቀቁ። ሚስቱ የእነርሱን ሁኔታ እያየች በመሸማቀቅ ‹‹ የባሕል ሕክምና እያለ ለመሞት ጫፍ ደረሰ እኮ!›› አለች። በመኪና ተከታትለው ኮሪያ ሆስፒታል ደረሱ። መንግሥቱ ፈጠን ብሎ ካርድ አወጣ። ዘውዱ ጭራሽ ባሰበት። በዊልቸር ሐኪም ፊት ቀረበ። ሐኪሙ አስፈላጊውን ምርመራ ካካሄደ በኋላ፤ ዘውዴ ተኝቶ መታከም እንዳለበት እና መለስ ካለለት በኋላ ቀዶ ጥገና እንደሚደረግለት ተናገረ።
ሐኪሙ ሚስቱ ተዋበችን ጠርቶ፤ ‹‹የሚዲያው ማስታወቂያ ሰምታችሁ መጠኑ የማይታወቅ ነገር መድኃኒት ነው በሚል ሲሰጠው እና እርሱም አምኖ ተቀብሎ ሲቀባ ሰውነቱ በስብሶ ሞት አፋፍ ላይ እስከሚደርስ ምን እየሠራሽ ነበር?›› ሲላት የምትሰጠውን መልስ አጣች።
መንግሥቱ ለዘውዴ ሕክምና ከፍተኛ ገንዘብ ቢጠየቅም ከመክፈል ወደ ኋላ አላለም። ክፍያውን ጨርሶ፤ ዘውዴ አልጋ ያዘ። ወዲያው ግሉኮሱን ጨምሮ የመድኃኒት መዓት ታዘዘ። ነርስ እና ሐኪሞቹ በጥድፊያ ይንከባከቡት ጀመር። ‹‹ አይ ገንዘብ ደጉ፤ ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› እንደሚባለው፤ ቅልጥፍና የተሞላበት እንክብካቤ ሲደረግለት፤ እነመንግሥቱ ዘውዴ ሕክምና እያገኘ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ የዘውዴ ሚስት ምግብ እንድትበላ እና እነርሱም አረፍ ለማለት ከሆስፒታሉ ወጥተው በአቅራቢያው ወደሚገኝ ምግብ ቤት መሄድ ጀመሩ።
ወደ ምግብ ቤት በዝግታ ሲራመዱ፤ ገብረየስ ከመንግሥቱ እና ከተዋበች መሐል ሆኖ ሁለቱንም እጆቹን ሁለቱም ኪሶቹ ውስጥ ጨምሮ በዝግታ አቀርቅሮ እየተራመደ ‹‹የባሕል ሕክምና መጥፎ አይደለም። ነገር ግን ሕክምናውን መስጠት ያለበት ትክክለኛ የባሕል ሕክምና በሚያውቅ ሰው ብቻ ነው። እነቻይና በባሕል ሕክምና ትልቅ ውጤት አምጥተዋል። በዩኒቨርስቲዎቻቸውም ሳይንሳዊ ሳይሆን የባሕል ሕክምናን ብቻ ለ10 ዓመታት የሚማሩ እና የተማሩ የባሕል ሐኪሞች አሏቸው።
በኢትዮጵያ ግን የባሕል ሕክምናው የሚተላለፈው በውርስ መልክ ከአባት ወይም ከእናት ወደ ልጅ ነው። ልጅ ደግሞ ፍላጎት ላይኖረው ይችላል። በተጨማሪ ቢያለማምዱትም በደንብ አያውቅ ይሆናል። በደንብ የማይችል የባሕል ሐኪም ሕክምና አደርጋለሁ ብሎ ሲንቀለቀል ሰዎች ላይ ሞት ሊያስከትል የሚችል ችግር ያስከትላል።›› አለ። ተዋበች ምንም አላለችም። መሬት መሬት እያየች እርሷም ከባሏ ጓደኞች ጋር እርምጃዋን ቀጠለች።
መንግሥቱ ‹‹በምንም መልኩ የባሕል ሕክምና ብሎ ነገር አይዋጥልኝም። ሙሉ ነገሩ ድፍረት የተሞላበት ነው። በዕውቀት ሳይሆን በድፍረት ሐኪም ነኝ ብሎ መድኃኒት ማዘዝ ማዳን ሳይሆን መግደል ነው። …›› ብሎ ያጋጠመውን ሊናገር ሲል፤ ገብረየስ ዕድል አልሰጠውም።
‹‹በጭፍን መደገፍም ሆነ መቃወም ትክክል አይደለም። የባሕል ሕክምና ላይ ጥናት እና ምርምር በማካሄድ ከሳይንሱ ጋር አዋሕዶ ሕክምና የሚሰጥበትን ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም። ከዛ ውጪ ሕጋዊ ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸትም ያስፈልጋል። በደፈናው ይቅሩ ማለት ያለንን ትልቅ ሃብት እንደማባከን ወይም እንደማጣት ነው። በሳይንስ ያልተገኙ ብዙ መድኃኒቶች በባሕላዊ መንገድ ተገኝተው ስንቱን በሽታ እየፈወሱ ነው የሚለውን ማወቅ የግድ ነው። ›› በማለት ገብረየስ መንግስቱን ለመገሰፅ ሞከረ።
ወደ ምግብ ቤቱ ገብተው ሲቀመጡ፤ ተዋበች ‹‹ አሁን አሁን በየመገናኛ ብዙኃኑ የሚተዋወቀው የባሕል ሕክምና ብቻ ይመስላል። የታመመ ሰው ደግሞ የሚፈልገው መዳን ነው። ማስታወቂያውን አይቶ ምናልባት እድን ይሆናል ብሎ ይጓጓል። በሚዲያ የተነገረ ሁሉ እውነት የሚመስለው ብዙ ሰው አለ። ›› አለች።
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹በእርግጥ ሚዲያዎቹ የሚያዩት የሚከፈላቸውን ገንዘብ ብቻ ነው። ሕጋዊ ማረጋገጫ የሌለውን ተቋምም ሆነ አገልግሎት እንዳያስነግሩ ለእነርሱም መመሪያ መስጠት ያስፈልጋል። የዘውዴ መጥፎ አጋጣሚ ነው። ነገር ግን ደግሞ ብዙዎች በሳይንሳዊ ሕክምና ሳይድኑ በባሕላዊ መንገድ ታከመው የዳኑ ብዙ ናቸው። ›› አለ።
ምግብ ካዘዙ በኋላ፤ መንግሥቱ፤ ‹‹እኔ ለባሕላዊ ሕክምና ጥላቻ ያደረብኝ እንዲሁ በደፈናው በጭፍን አይደለም። አብሮ አደግ ጓደኛዬን ያጣሁት በዚሁ ምክንያት በመሆኑ ነው። መድኃኒት ብለው ቀምመው ሲሰጡት የነበረው ነገር ለሞት አበቃው። አሁንም ሐኪሞቹ እንደተናገሩት ዘውዴ ከዚህ በላይ ቢቆይ ኖሮ ለሞት ይቀርብ ነበር። በተጨማሪ አሁንም ቢሆን ቁስሉ አስጊ ነው። የካንሰር ምርመራ እናደርግለታለን እያሉ ነው። በጊዜ ዘመናዊ ሕክምና ባለመውሰዱ ከፍተኛ ዋጋ ሊከፍል ይችላል። ይህ እየታየ ባሕላዊ ሕክምናን መውደድ ለእኔ ጤነኝነት አይደለም። ›› ሲል ምላሽ ሰጠ።
መንግሥቱ ቀጠለ፤ ‹‹ሰው ያለው አቅም ውስን ነው። ቅድም እንደነገርኳችሁ ለበሽታዎች ሁሉ መድኃኒት አለን እያሉ ማስነገር፤ ለማለት ያህል እንጂ በዓለም ላይ ያሉ ታዋቂ የሕክምና ባለሙያዎችም ለመላው ሕመም መድኃኒት አለን አላሉም። እንኳን ለመላው ለሁለት እና ለሦስት ሕመም እንኳ ተለማምደው፤ ከሌሎች ተሞክሮ ወስደው፤ ምርምር አድርገው ሂደቱን ጨርሰው መድኃኒት ለመስጠት ብዙ ጊዜ መውሰዱ የማይቀር ነው። ስለዚህ ለእኔ ከላይ እንደጠቀስኩት ባሕላዊ ሕክምና ብሎ ነገር ድፍረት የተሞላበት በስህተት የታጀበ ሰዎችን ማወናበጃ እና ገንዘብ የመሰብሰቢያ መንገድ ነው።›› በማለት ሃሳቡን ደመደመ።
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹አንተ በእርግጥም ጭፍን ጥላቻ ውስጥ ነህ። ዳማከሴ ለብዙ ነገር መድኃኒት ሲሆን አይቻለሁ። በተደጋጋሚ እኔም ሞክሬው ሐኪም ቤት ሳልሔድ ድኛለሁ። ዝንጅብል እና ነጭ ሽንኩርት፤ ጥቁር አዝሙድ እና ፌጦን የመሳሰሉ ባሕላዊ መድኃኒቶች ባሉበት ሀገር ሳይንሳዊ ሕክምናን ብቻ ሙጥኝ ማለት ትርፍ የለውም። ሁሉንም በልክ ማየት ያስፈልጋል። ›› አለ።
ተዋበች እንደመንግሥቱ የባሕል ሕክምና መልካም ነው ብላ አታምንም። እርሷም በተመሳሳይ መልኩ የኪንታሮት በሽታን በባሕላዊ መድኃኒት እናጠፋለን በሚሉ አወናባጆች የአጎቷ ሕይወት እንዲጠፋ አድርገዋል። ባሏም የአጎቷ ዕጣ እንዳይደርሰው ሰግታለች። ተዋበች የአጎቷን ተሞክሮ ለእነገብረየስ ነገረቻቸው።
የተዋበች አጎት ለሕመሙ ብሎ የወሰደው የባሕል መድኃኒት ሰውነቱን አበስብሶት ሐኪም ቤት ሲሔድ፤ መፀዳዳት ተስኖት የበላው ምግብ ሆዱ አካባቢ በጎን በኩል ተቀዶ በቱቦ ሲጠቀም እንደነበር አስታውሳ ሁኔታውን እያንገሸገሻት ነገረቻቸው። ይህ ነገር ባሏም ላይ እንዳይደርስ ፀሎት ስታደርግ መቆየቷን እና በኋላም እነርሱ መጥተው ሐኪም ቤት ስላደረሱት መደሰቷን ገልፃ ለሁለቱም ምስጋና አቀረበች።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም