የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አምስት ሚሊዮን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ በቅርቡ ማስጀመራቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢንሼቲቩ ሰልጣኞችን ዘመኑን በዋጀው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል።
የኢትዮጵያ የነገ ተስፋዎች የሆኑ ወጣቶችም ሥልጠናውን በጥሞና በመከታተል ሥራ እና ኩባንያ ፈጣሪ እንዲሁም በዓለም ገበያ ተወዳድረው የሚቀጠሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል ለዚህም ይህንን ትልቅ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ይገባቸዋል ብለዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ክህሎት በዲጂታል የታገዘ ማህበረሰብ ለመፍጠር እና አዳዲስ የሥራ እድሎችን ለማመቻቸት ወሳኝ እየሆነ መጥቷል። ነገር ግን ኢትዮጵያ በተመሳሳይ የእድገት ደረጃ ጋር ካሉ ሀገራት ጭምር ስትወዳደር በዲጂታል ክህሎት ወደ ኋላ ቀርታለች።
አዲሱ ትውልድ የዲጂታል ክህሎትን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን ካልቻለ ደግሞ እንደ ሀገርም ተወዳዳሪነት አደጋ ላይ ይወድቃል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በዲጂታል ክህሎት ያለባትን ክፍተት ለመሙላት የመሠረታዊ የኮሞፒውተር እውቀትና ሁለንተናዊ የዲጂታል ክህሎት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ለወጣቶች ተደራሽ ለማድረግ በማቀድ ወደ ሥራ ተገብቷል። ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ወጣቶች ተገቢውን የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማድግ የአምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ ፕሮግራም ተቀርጾ ፋይዳው ከፍተኛ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው።
‹‹አምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ›› ፕሮግራም በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግሥታት መካከል በተደረገ ስምምነት የተነደፈ የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና መርሃ ግብር ነው። የመርሃ ግብሩ አላማ ወጣቱ ትውልድ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ የሚያስችለውን የዲጂታል ክህሎት እንዲኖረው ማስቻል ነው።
መርሃ ግብሩ ለሁሉም ተደራሽ የሆኑ የኦንላይን ኮርሶችንና ሌሎች ደጋፊ የሆኑ አገልግሎቶችን በማቅረብ እ.ኤ.አ በ2026 አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ እና አንድሮይድ ልማት መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ማስታጠቅን ግብ ያደረገም ነው።
በኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ስዩም መንገሻ እንደሚናገሩት፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ላይ ከተቀመጠው ዋና ነገር አንዱ የዲጂታል ውስንነት መሙላት ነው። ለዚህ ደግሞ ብዙ ቁጥር የሚያሳትፍ እንደ ኢትዮጵያን ኮደርስ አይነት ፕሮግራሞች ተግባራዊ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው።
በዚህ ፕሮግራም የሚሰጡ ኮርሶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው የሚሉት አቶ ስዩም፤ የሚሰጡ ኮርሶች መሠረታዊ ናቸው ማለትም ዳታ ሳይንስ፣ ፕሮግራሚንግ፣ አንድሮይድ ፕሮግራሚንግ ላይ የኢትዮጵያ ኮደርስ ፕሮግራም በዋናነት ይሰጣሉ እነዚህ ኮርሶች አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ነው ይላሉ።
የሥልጠናዎቹ ይዘቶች የሚቀርቡት ዓለም አቀፍ የዲጂታል ክህሎቶችን በኦንላይን (በማስተማር ስመጥር ከሆነው ከዩዳሲቲ ፕላትፎርም ጋር በመተባበር ስለመሆኑ የሚናገሩት አቶ ስዩም፤ ፕላትፎርሙ የተለያዩ የፕሮግራሚንግ የዌብ ልማትን እና ሌሎች በፍላጎት ላይ የተመሰረቱ የኮዲንግ ሥልጠናዎችን እንደምሰጥ ይናገራሉ። በፕላትፎርሙ የሚሰጡት ኮርሶች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው እና ከኢንዱስትሪውም ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ናቸው። ለመነሻም ሥልጠናዎቹ በአራት የሥልጠና ዘርፎች ላይ የሚሰጥ ሲሆን፤ ሰልጣኞች በተዘጋጀው በፕላትፎርም በመመዝገብ ኮርሶቹን በኦንላይን የሚወስዱ ይሆናል።
እንደ አቶ ስዩም ገለፃ፤ አንዱ ኮርስ እስከ ስድስት ሳምንት ሊወስድ ይችላል። በኦንላይን ለየኮርሶቹ አማካሪዎችና ውይይት የሚያደርግ የኦንላይን ማህበረሰብም ይኖራል። አሁን ለመነሻ ከቀረቡት የስልጠና ይዘቶች በተጨማሪ በቀጣይ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን መሠረት ያደረጉ ተጨማሪ ይዘቶች የሚካተቱ ይሆናል።
እነዚህን ኮርሶች ማንኛውም ሰው መውሰድ አለበት የግድ የኮምፒውተር ባለሙያ መሆን አይጠበቅም የሚሉት አቶ ስዩም፤ የኮርስ አሰጣጡም ቀለልና ለየት ያለ ነው በቪዲዮና በጽሑፍ የሚሰጠውን ትምህርት በማዳመጥና በማንበብ የሚሰጡ ጥያቄዎችን በመመለስ ብቁ የመሆን ዕድል የሚሰጥ ነው ነገር ግን ዝም ብሎ ብቁ የመሆን ዕድል የለም ሰርተፍኬት ለማግኘት ከሚሰጡ ጥያቄዎች 60 በመቶ የሚሆኑትን መመለስ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
ሥልጠናውን በገንዘብ መውሰድ ቢፈለግ ክፍያው በዶላር ስለመሆኑ የሚናገሩት አቶ ስዩም፤ ይህ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው ነገር ግን ለኢትዮጵያውያን በነፃ ቀርቧል ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በቤታቸው ሆነው በፈለጉት ሰዓት ኮርሱን መውሰድ ይችላሉ ይህ በቀላሉ የማይገኝ ዕድል በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ከ259 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሥልጠናውን እየወሰዱ እንዳለ የሚነገሩት አቶ ስዩም፤ ከእነዚህ ውስጥ ከ35 ሺህ በላይ ሰልጣኞች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መውሰዳቸውን ተናግረዋል። ይህንን ፕሮግራም በበላይነት የሚያስተባብር ተቋም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሠራተኞች ጭምር በፕላትፎርሙ የሚሰጡ ኮርሶችን ተከታትለው ብቁ እንዲሆን እየተሰራ ስለመሆኑ የሚገልፁት አቶ ስዩም፤ ሌሎችም የፌዴራል ተቋማት ሠራተኞቻቸው የዲጂታል ዓለሙን ተገንዝበውና በቂ እውቀት ኖሯቸው ሥራዎችን መሥራት እንዲችሉ ይህንን ሥልጠና እንዲወስዱ መበረታታት እንደሚገባቸው ይናገራሉ።
በዚህ ፕሮግራም ሰልጥነው ብቁ የሆኑ ሰዎች ባሉበት ሆነው ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንደሚችሉ የሚናገሩት አቶ ስዩም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ አውሮፓ ላይ ላለ ድርጅት ሥራ መሥራት ይቻላል ይህ በአንድ የገቢ ምንጭ ብቻ ጥገኛ የሆነ ኑሮ ያለውን ሰው ሕይወቱን መለወጥ የሚችልበት አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ይላሉ።
የሥልጠና ፕሮግራሙ በመላው ሀገሪቱ ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ የሚናገሩት አቶ ስዩም፤ የሁሉም ክልል ፕሬዚዳንቶች ኃላፊነት ወስደው የሚመሩት ይህንን የሥልጠና ፕሮግራም አፈፃፀም የሚከታተል ኮሚቴ አለ ይህ ኮሚቴ የሥልጠና ሂደቱን ውጤታማነት ይገመግማል፣ ችግሮች ከሉ እነርሱን በመለየትና እንዲፈቱ በማድረግ ፕሮግራሙ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።
የኢንተርኔት መሠረተ ልማት ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙና ይህንን ሥልጠና መውሰድ የሚፈልጉ ሰዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት በመሄድ ሥልጠናውን መከታተል እንዲችሉ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መግባባት ላይ ስለመደረሱ ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የመንግሥት አገልግሎቶች ዲጂታል እንዲሆኑ ግብ ተቀምጦ እየተሠራ እንዳለ የሚናገሩት አቶ ስዩም፤ አገልግሎት አሰጣጡ ዲጂታል ሆኖ ህብረተሰቡ መጠቀም ካልቻለ ጥቅም የለውም ለዚህ ደግሞ እንደ ሀገር የዲጂታል ክህሎት ያስፈልጋል አገልገሎት ሰጪና ፈላጊ አካላት በቂ የቴክኖሎጂ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል። ከዚህ አኳያ በዚህ ሥልጠና በንቃት መሳተፍ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።
የቴክኖሎጂ ባለሙያና የፋርስ ቴክኖሎጂ ኩባንያ መሥራች ወጣት ኤልያስ ይርዳው በበኩሉ እንደሚናገረው፤ ዓለም ከዲጂታላይዜሽን አልፎ ወደ ሰው ሠራሽ የቴክኖሎጂ ምርምር ተሸጋግሯል ከዚህ አኳያ ነገሮችን መረዳት የሚችሉ ከተረዱ በኋላ ደግሞ የመፍትሔ ሃሳብ ማምጣት የሚችሉ ወጣቶችን ለማፍራት ይህ የኢትዮጵያን ኮደርስ ፕሮግራም ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚኖረው ይናገራል።
ከዚህ በፊት በፋርስ ቴክኖሎጂ አማካኝነት መሰል የቴክኖሎጂ ሥልጠና የወሰዱ ወጣቶች በአሁኑ ወቅት በሀገራቸው ውስጥ ሆነው አውሮፓና አሜሪካ ለሚገኙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ እንዳለ የሚናገረው ወጣት ኤልያስ፤ ይህ የኢትዮጵያን ኮደርስ ፕሮግራምም ሰፊ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ተናግሯል።
በቀጣይ ሥራ በመሥራት እራሴን፣ ቤተሰቤንና ሀገሬን መጥቀም እፈልጋለሁ የሚል ማንኛውም ሰው በእንደዚህ ዓይነት የቴክኖሎጂ ሥልጠናዎች እራሱን ማብቃት ግዴታ ይኖርበታል የሚለው ወጣት ኤልያስ፤ በተለይ ወጣቶች ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ራሳቸውን ለመለወጥ መዘጋጀት እንዳለባቸው ይናገራል።
በአሁኑ ወቅት ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከሚያስገባው ዶላር በላይ በቴክኖሎጂ ልማት የተሰማሩ ድርጅቶች ወደ ሀገር ውስጥ እያስገቡ ነው የሚለው ኤልያስ፤ አሁን ያለነው እውቀት ገንዘብ የሆነበት ዘመን ላይ ነው ከዚህ አኳያ ይበልጥ እንደ ሀገር ተጠቃሚ ለመሆን በዚህ ዓይነት ሥልጠና የበቁ ወጣቶች እንደሚያስፈልጉ ይናገራል። ለአብነት ህንድ ከሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርቷ ከ230 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የበቁ ወጣቶች የትም ሳይሄዱ ባሉበት ሆነው ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሚሰሩት ሥራ አማካኝነት እንደምታገኝ ተናግሯል
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጥናት መሠረት ይህ ዘርፍ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚያመነጨው ገቢ ወደ አምስት ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ከዚህ አኳያ ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን መዘጋጀት እንደሚገባ ያስረዳል። በሀገር ውስጥም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ስለመምጣቱ የሚናገረው ኤልያስ፤ እነዚህ ድርጅቶች የግድ ብቁ የቴክኖሎጂ እውቀትና መረዳት ያላቸውን ወጣቶች ይፈልጋሉ ስለዚህ ወደፊት ለሚጠብቀው ዕድል ከአሁኑ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ይላል።
መንግሥት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውን ይህን ዓይነት የሥልጠና ዕድል በነፃ ማቅረቡ የሚያስመሰግነው ነው የሚለው ኤልያስ፤ በተለይ ከሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ወጣት በመሆኑ ይህንን ሰፊ ቁጥር ያለው ወጣት ተደራሽ ለማድረግ በየዓመቱ የሚቀጥል ፕሮግራም መሆን አለበት ይላል።
ይህ የኮደር ፕሮግራም ኢትዮጵያ ለማሳካት ያቀደችውን ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ውጥን ከግብ ለማድረስና በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሰው ከፍተኛ ገቢ ተከፋይ ለመሆን ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ይናገራል።
ወጣት ኤልያስ እንደሚያስረዳው፤ በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም ሁሉም ቴክኖሎጂ እየታጠቀ ነው ቴክኖሎጂ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና ዘርፍ ተግባራዊ እየሆነ ነው። ይህንን ቴክኖሎጂ ደግሞ ተረድቶ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ በቂ እውቀት ሊኖር ይገባል ከዚህ አንፃር መዘጋጀት ለነገ የማይባል ነው።
በአጠቃላይ አስተያየት ሰጪዎቹ እንደተናገሩት፤ የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ በወጣቶች እጅ በመሆኑ የነገዋን ኢትዮጵያ የሚቀርፁት የፈጠራ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች እነዚህ ወጣቶች ናቸው። በመሆኑም የኢትዮ ኮደርስ ፕሮግራም ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በዲጂታል ሥነ ምህዳሩ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችላቸውን ክህሎትና እውቀት በማስታጠቅ አዳዲስ እድሎች እንዲፈጠርላቸው እና ሀገሪቱ በቴክኖሎጂው መስክ ወደፊት እንድትገሰግስ በር የሚከፍት በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም