መደበኛ ትምህርትን ለማጠናከር – የተጓዳኝ ትምህርት

ተጓዳኝ ትምህርት የመደበኛ ትምህርቱ አካል ነው የሚለው አያከራክርም። መደበኛ ትምህርቱም ያለ ተጓዳኝ ትምህርት ድጋፍ ልክ አይመጣም። በመሆኑም ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ የመሆናቸው ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። ችግሩ ሁለቱ ተነጣጥለው ከታዩና አንዱን የአንዱ ባዳ አድርጎ ማሰብና ማስላት ከተጀመረ ነው።

በተወሰኑ የትምህርት ዓይነቶች ክፍል ውስጥ በሚሰጥ ትምህርት ብቻ ብቁ የሆኑ ዜጎችን ማውጣት እንደማይቻል የሚያብራራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት አፈፃፀም መመሪያ፣ (2007 ዓ.ም) እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ “ተማሪዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በኪነጥበብ፣ በስፖርት፣ በተፈጥሮና ማኅበራዊ ሳይንስ፤ እንዲሁም፣ በሌሎች ዘርፎች በንቃት በመሳተፍ ጊዜያቸውን በቁም ነገር ላይ ሊያሳልፉ ይገባል ይላል። ይህ ሲሆን የዕውቀት አድማሳቸው፣ ክህሎታቸውና አመለካከታቸው በሚፈለገው ደረጃ ይዳብራል። ከዚህ አንፃር የተጓዳኝ ትምህርት ፕሮግራሞችን ከመደበኛው የክፍል ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደት ጎን ለጎን በማደራጀት የተማሪዎችን ሁለንተናዊ እድገት ለማሟላት እንዲቻል እንደሌሎች አገሮች ሁሉ በኢትዮጵያም ዘመናዊ የትምህርት ስርዓት ከተጀመረ አንስቶ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀትን በመጠቀም በሚፈለገው መጠን ውጤታማ ስራዎችን ሰርተዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡”

ይኸው ሰነድ “የተጓዳኝ ትምህርት ከክፍል ውጭ በተማሪዎችና በመምህራን ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ ከመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም ወይንም የክፍል ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደት ውጭ ባለው ሰዓት የሚፈፀም ነው። የተጓዳኝ ትምህርት ትርጉም በእንግሊዝኛው ቋንቋ የተለያዩ ስያሜዎች የተሰጠው ሲሆን የተወሰኑ አገሮች ‘co-curricular′ ሲሉት ሌሎች ደግሞ ‘Extra-class′፣ ‘extra-curricular′፤ እንዲሁም ‘Student Activities′ ይሉታል፡፡” ካለ በኋላ “ቴክኖሎጂ እያደገ የአስተሳሰብ አድማስም እየሰፋ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የሀገራችን የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ የተጓዳኝ ትምህርትን ያካተተና ከመደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት በተጨማሪ እነዚህ ተግባራት የሚከናወኑበት የራሱ ጊዜ የተመደበ በመሆኑ የተጓዳኝ ትምህርትን ሊገልፅ የሚችለው የእንግሊዝኛ ቃል ‹‹co-curricular›› የሚለው ገላጭ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡” በማለት ለጽንሰ ሀሳቡ ብያኔ ይሰጣል።

ይህ ሰነድ እንደሚለው “ስለተጓዳኝ ትምህርት ጠቀሜታ አሰራርና አፈፃፀም በቂ ግንዛቤ ያላቸው ትምህርት ቤቶች የተሻለ በመስራት ውጤት ለማስመዝገብ የቻሉ ሲሆን ሌሎች የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት አሰራርና አፈፃፀም በተገቢው ግንዛቤው የሌላቸው ግን በሚፈለገው ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ” አልቻሉም።

“‘Co-curricular′ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በሀገራችን ‘የተጓዳኝ ትምህርት′ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ይህም ከክፍል ውስጥ ትምህርት ውጭ በመደበኛው የትምህርት አሰጣጥና ስልት መሠረት ከሚፈፀሙ ተግባራት በተጨማሪ የተማሪዎችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የሚከናወን ተግባር ነው፡፡” በመሆኑም በሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚገኙ መምህራን ተማሪዎችን እንደ ዝንባሌያቸው በማስተባበርና የተጓዳኝ ትምህርትን በመምራት በተማሪዎች ዘንድ የሚፈለገውን የባህሪ ለውጥ እንዲፈጠር ለማድረግና ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ በትምህርት ቤቶች የማመቻቸቱ ተግባር የመምህራን ይሆናል።

የተጓዳኝ ትምህርት “የተዘጋጀውን ሥርዓተ ትምህርት ተማሪዎች የበለጠ እንዲረዱትና ወደ ተግባር እንዲለውጡት” ያስችላቸዋል የሚለው ሰነድ “የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት፣ አመጣጥ፣ አሠራርና ጠቀሜታ በተለያዩ አጋጣሚዎችና ሰነዶች ሲገለጽና ሲቃኝ የኖረ ነው። ሆኖም በሀገራችን ብሎም በአዲስ አበባ የሚጠበቀውን ያህል ስኬታማ ነው ለማለት ያዳግታል፡፡” ሲልም የላይኛውን ሀሳቡን የሚያጠናክር ሲሆን፤ ያለውን እጥረትና ክፍተትም:-

  • አደረጃጀታቸውም ሆነ አፈፃፀማቸው በእውቀት፣ በተጠያቂነትና በአሳታፊ መዋቅር ላይ የተመሠረተ ነው ለማለት ያዳግታል፤
  • በእቅድ የተያዘና በመርሀ ግብር የታገዘ የአፈፃፀም፣ የክትትልና ድጋፍ ከፍተኛ እጥረት ይታይበታል፤
  • የተደራጀ ወቅታዊ ተገቢ የመረጃ አያያዝ ችግር ይንፀባረቃል፣ በአደረጃጀት፣ በአተገባበርና በተጨበጠ ስኬት ላይ የተመሠረተ የማትጊያ የእውቅና መስጫ ጠንካራ ሥርዓት የለውም፤
  • የግብዓት እጥረት፣ በጀት አለመመደቡና በፍትሃዊነት ያለመጠቀም ችግሮች ይታያሉ፤
  • ከባለድርሻ አካላት ጋር ተገቢ የሆነና ዘላቂነት ያለው የትስስርና የመዋቅር ግንኙነት ክፍተት አለበት፤
  • የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀትና አተገባበርን በየጊዜው ከሚስተዋለው የሣይንስና የቴክኖሎጂ እድገትና ለውጥ ጋር እየፈተሹ፣ እያሻሻሉና እያደራጁ አለመጓዝ ወዘተ ቁልፍ አመላካች እጥረቶች በየጊዜው ይስተዋላሉ፡፡

 

በማለት ይዘረዝራል። እነዚህን ችግሮች “ለመፍታት በቢሮ ደረጃ አንድ ወጥና ግልፅ የሆነ ማንዋል ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡”

“በመሆኑም ቀደም ሲል በ1989 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀውን የተጓዳኝ ትምህርት የአፈፃፀም መምሪያ (ማኑዋል) መነሻ በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሚመራቸው የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ትምህርት ቤቶች እንዲጠቀሙበትና ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር እንዲችሉ” አንድ ራሱን የቻለ የአፈፃፀም መምሪያ ማዘጋጀቱን ትምህርት ቢሮው አስታውቋል። የመምሪያውን ዓላማም:-

  • ከትምህርት ቢሮ እስከ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ አመራሮች አደረጃጀቱን፣ አሰራሩንና አፈጻጸሙን በዕውቀት ለመምራት እንዲችሉ አቅም መፍጠር፤
  • በተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀቶች ተሳትፎ የሚያደርጉና ቀጥታ የሚመለከታቸው መምህራንና ተማሪዎች መምሪያውን እየተጠቀሙ ዕቅድን፤ መረጃን፣ ሂደትንና ውጤትን መሠረት ያደረገ ስራ እንዲሰሩ ማስቻል፤
  • ተማሪዎች የሥራ የአመራር ባህልንና የተለያዩ ክህሎቶችን አዳብረው ዝግጁ በመሆን ለህብረተሰቡ ጠቀሜታ ሊሰጡ በሚችሉ ስራዎች ላይ በቂ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማድረግ፤

 

በማለት ዘርዝሯል።

የትምህርቱን ቅርፅና ይዘት አስመልክቶ ባሰፈራቸው አንቀፆች ስር የትምህርቱን መነሻ በተመለከተም:-

“የተጓዳኝ ትምህርት ምንጭ ከማህበራዊ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ባህልና ስነጥበብ፣ ስፖርትና ቱሪዝም ወዘተ… የተገኘ ነው። መሠረታዊ ሀሳቡ በክፍል ውስጥ ሊሰጥ ከተዘጋጀውና ከዚያም ውጭ ባሉ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች የሚወሰድ በመሆኑ ወደ ተግባር የሚለወጥና ጠቀሜታ ያለው አሰራር ሲሆን በማንኛውም የትምህርት ቤት ደረጃና የመማር ማስተማር ስራ አጋዥ እንቅስቃሴ ነው።

“ትምህርት ቤቶች እንደ ራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ስርዓተ ትምህርቱን ወደ ተግባር ይለውጡታል ተብሎ የሚታመንባቸውን ጉዳዮች በመለየት በተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀቶች እንዲታቀፉ ያደርጋሉ። አደረጃጀቱ ለአመራር እንዲመችና የነበረውን የክበባት ያለ ልክ መለጠጥ ለማስቀረት በትምህርት ቤት ደረጃ የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት ቅርፅ በዚህ መምሪያ (ማንዋል) ላይ ለማስቀመጥ ተሞክሯል። በየአደረጃጀቱ ስር ተያያዥነት ያላቸው ተጨማሪ ተግባራትንና ክበባትን ማዋቀር የሚቻል ሲሆን በመምሪያው የቀረበው መነሻ ሃሳብ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል፡፡” ሲል አስፋፍቶ ይገልፀዋል።

መመሪያው የተጓዳኝ ትምህርት የሚደራጅበት ዓላማ ከአጠቃላይ ትምህርት ማሕቀፉ ፋይዳ ተነጥሎ የሚታይ ባለመሆኑ በተገቢው መንገድ የተደራጀና ተግባር ውስጥ የገባ አደረጃጀት(ቶች) የሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተሉት መሆናቸው ይዘረዝራል።

  1. በክፍልውስጥየሚሰጠውንየንድፍሃሳብትምህርትበተግባርመረዳትእንዲችሉበማድረግየግልናየማህበራዊዕድገትንያፋጥናል፤
  2. የሰብዓዊግንኙነትክህሎትንበማዳበርሌሎችንምየማክበርናየመከባበርስርዓትንይማሩበታል፤
  3. ራስንየመግለፅ፣ከሰዎችጋርየመወያየት፣የማመንናየማሳመን፣የማወቅናየማሳወቅ፣የውይይትስነስርዓቶችንየማወቅ፣ውሣኔየመስጠትንናበውይይትየመተማመንንሂደት፤እንዲሁም፣አመራርን፣ኃላፊነትን፣ተጠያቂነትንሁሉእንዲማሩበትናእንዲለማመዱትያግዛል፤
  4. የመቻቻልባህልንበማዳበርቅራኔዎችንበውይይትየመፍታትንሕግናደንብስርዓትእንዲማሩበትያግዛል፤
  5. ለሥራአክብሮትመስጠትን፣የጊዜንጠቀሜታመረዳትን፣ሥራማህበራዊመሆኑንየመገንዘብናየቡድንሥራንእንዲለማመዱይረዳል፤
  6. የፈጠራችሎታበማሳደግለቴክኖሎጂዕድገትመሠረትየሚጥሉየተማሪዎችልዩልዩፈጠራዎችናተሰጥዖእንዲጎለብትያደርጋል፤
  7. በትምህርትአቀባበላቸውደከምያሉተማሪዎችእንዲታገዙበትያደርጋል፤
  8. የትምህርትቤቱንናየህብረተሰቡንግንኙነትይበልጥያጠናክራል፤
  9. የወደፊትሥራንናሙያንየማስተዋወቅጠቀሜታአለው፤
  10. አካባቢያዊ፣ክልላዊ፣አገራዊናዓለምአቀፋዊየሆኑጉዳዮችንናአዳዲስክስተቶችን፤እንዲሁም፣ችግሮችንናግኝቶችንየማስተዋወቅጠቀሜታአለው፤
  11. ጤናማዜጋበትምህርትቤቶችለማፍራትያስችላል፤
  12. በስነምግባራቸውየበቁየተሻለውጤትባለቤትሊሆኑየሚችሉተማሪዎችንኮትኩቶለሀገርዕድገት፣ለዲሞክራሲስርዓትግንባታናለመልካምአስተዳደርመስፈንአስተዋፅዖሊያደርጉየሚችሉዜጐችንማፍራትያስችላል።

ከዚህ በላይ ሰፋ አድርገን የሄድንበትን ተጓዳኝ ትምህርት መሬት ላይ፣ በየትምህርት ተቋማቱ ያለው ወቅታዊ ይዞታ ምን ይመስላል? የሚለውን ለማወቅ በተወሰኑና ይወክሉልናል ባልናቸው የትምህርት ተቋማት ተዘዋውረን ለመመልከት ሞክረናል። በዚሁ ሙከራችንም የተለያዩ የክበባት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አይተናል።

የአራት ኪሎው የዳግማዊ ምኒልክ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ ደረጃ፣ መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተመለከትናቸው ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው።

በዚሁ ትምህርት ቤት ተገኝተን እንደ ተመለከትነው በተቋሙ ውስጥ 21 ክበባት ያሉ ሲሆን፣ ተማሪዎች እንደየ ፍላጎታቸውና ዝንባሌያቸው በክበባቱ ይሳተፋሉ፤ በአንድም ይሁን በሌላ የማይሳተፍ ተማሪ የለም።

ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ቀርበን መረዳት እንደ ቻልነው እነዚህ 21 ክበባት በሙሉ ከላይ (ከትምህርት ቢሮ) የወረዱ ሲሆን፤ ወጥ በሆነ መልኩ በከተማ መስተዳድሩ ስር በሚገኙ፣ በሁሉም ትምህርት ተቋማት እየተተገበሩ ይገኛሉ።

ስማቸው እንዳይገለጽ ምስላቸውም እንዳይታይ የነገሩንና መረጃውን የሰጡን ምንጮች እንደነገሩን፤ ወቅቱን ያገናዘቡና ተጨባጭ ሁኔታዎችን ሊያሰርፁ የሚችሉ ክበባት በተጓዳኝ ትምህርት ስር ተካተዋል። ይህም ተጓዳኝ ክበብን ከወትሮው የተለየ አድርጎታል። የክበባቱ ውቅር በአቀራረባቸው ከሕይወት ጋር የተቆራኙ፣ በርካታ ተግባራትን ያቀፉ ጭብጦች ያሏቸው፣ ከተለያዩ የትምህርት መስኮች ጋር የተገናኙ ዕውቀት፣ ግንዛቤና ክህሎቶችን ያዋሀዱና ተማሪዎች በተሻለ ጥራት እውቀት እንዲገበዩ የሚያስችሉ ሆነው የተደራጁ ናቸው ማለት ይቻላል።

ካገኘነው መረጃ መረዳት እንደቻልነው፣ ባህል እና ኪነጥበብ፣ የመንገድ ደህንነት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ የግብርናና የእንስሳት ርባታ፤ የእጅ ስራ፣ የአካባቢ እንክብካቤ፣ ሥነ-ምግብ፣ ፀረ-ሙስና፣ ግብረ-ገብ፣ የመማክርት ክበብ ወዘተ እና የመሳሰሉት የተጓዳኝ ክበባትን ከድሮዎቹ ለየት፣ ሰፋና በርከት ያሉ ይሆኑ ዘንድ አድርገዋቸዋል።

በአጠቃላይ፣ የትምህርት ተቋማት ከቀለም እውቀት ባሻገር ተማሪዎች በርካታ ግንዛቤዎች የሚጨበጡባቸው፤ የተለያዩ ክህሎቶች የሚዳብሩባቸው፤ ጠንካራ ማህበራዊ ሕይወት የሚመሰረትባቸው፤ ክፉና ደጉን የሚለዩባቸው፤ የወደፊት ሕይወታቸውን መሰረት የሚጥሉባቸው፤ በርካታ መልካም ትዝታዎችን ከወዲሁ የሚሰንቁባቸው፤ የአኗኗር፣ የአመራር፣ የአሰራር ወዘተ ብቃታቸውን የሚያጎለብቱባቸው፤ ኃላፊነቶችን መሸከምና መወጣትን ከወዲሁ የሚለማመዱባቸው፤ ከሁሉም በላይ ዝንባሌና ፍላጎታቸውን በመገንዘብ የወደፊታቸውን ከወዲሁ የሚያማትሩባቸው ልዩ ስፍራዎች ናቸው። ከእነዚህ አንዱ ደግሞ ተጓዳኝ ትምህርት ነው። በመሆኑም፣ ሁሉን አቀፍ በሆነና በተሟላ መልኩ ተደራጅተው ብቁ ዜጋ ማፍራቱ ላይ ሊዘናጉ አይገባም።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You