ቅድመ -ታሪክ
በፖሊሶች የምርመራ ክፍል ድንገት በር አንኳኩተው የገቡት ባለጉዳይ የሆነውን ሁሉ መናገር ጀምረዋል። አረፍ ብለው ሀሳባቸውን እንዲያስረዱ ወንበሩን ያሳያቸው መርማሪ በትዕግስት እያዳመጣቸው ነው።ሰውዬው በእጅጉ ስለመናደዳቸው ገጽታቸው ይመሰክ ራል። በአንገታቸው ቁልቁል የሚንቆረቆውን ላብ በእጃቸው እየሞዠቁ ጫን ጫን ይተነፍሳሉ።
መርማሪው አሁንም በትዕግስት እያያቸው የሚሉትን ለማዳመጥ ይሞክ ራል። ሰውዬው በጥቂት መስመሮች የተጻፈ ማመልከቻቸውን ከወዲያ ወዲህ እያወዛወዙ በንዴት የተዋዛ ንግግራቸውን ጀመሩ። ሁኔታቸውን ያስተዋ ለው መርማሪ ከእጃቸው ማመልከቻውን ተቀብሎ በአንድ ትንፋሽ አንብቦ ጨረሰ።
ለአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል በሚል ርዕስ የተጀመረው ጽሁፍ ጉዳዩን በማብራራት ቀጥሎ በአመልካቹ ሙሉ ስምና በፊርማው ማረጋገጫ ይጠናቀቃል። ሰውዬው ስማቸውን አቶ በድሉ መኮንን ሲሉ አስተዋወቁ። መተዳደሪያቸው አመታትን የተሻገረ የንግድ ስራ ነው። በዚህ የህይወት ጉዞ ወጥተውና ወርደው አግኝተዋል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ደስ ብሏቸው አልፏል። በማግኘት የመክብራቸውን ያህልም ውሏቸው ከኪሳራ ተዳምሮም በሀዘን ቆዝመው ተክዘዋል።
ይህ አይነቱ እውነት የስራው ባህርይ መሆኑን እያመኑ ለነገው መሻል ዛሬን ሲተጉ ቆይተዋል። የእሳቸው የንግድ ስራና የመኖራቸው መንገድ ሁሌም ጉራማይሌ እንደነበር አይዘነጉም። በዚህ ሁሉ አጋጣሚ ኑሮን እንደአመጣጡ እየተጋፉ በሙያው የዕድሜያቸውን ግማሽ ያህል ቆይተዋል። በእንዲህ አይነቱ የህይወት መስመር ደግሞ በርካቶችን አውቀው ከብዙዎች ተወዳጅተዋል። ተበድሮ መስራትንና አበድሮ መመለስን ጭምር ጠንቅቀው ያውቁታል።
አንዳንዴ ደግሞ የንግድ ስራ ውሎ በአለመተማመን ሳቢያ ሊፋረስ ይችላል።ይህ ደግሞ በሙያው ላይ የተለመደ መሆኑን አብዛኞች ይረዱታል። በገንዘብ ጣጣ መቀያየምና ከነአካቴው መቆራረጥ፣ባስ ሲልም በህይወት ጭምር መፈላለግ ይኖራል።ይህን እውነት እሳቸውን ጨምሮ አብዛኞቹ የንግድ ሰዎች አልፈውበታል። ዛሬን በዚህ ስፍራ ያቆማቸው ጉዳይ ግን ከሌሎች አጋጣሚዎች በእጅጉ የተለየ ነው።
አሁን «አምነዋለሁ »ባሉት የቅርብ ጓደኛቸው «ተክጃለሁ፣ ተታልያለሁ እያሉ ነው። እኚህ ሰው እስከዛሬ በነበሩ ጊዜያት ለሳቸው የተለዩ ነበሩ።ክፉና ደግ አጋጣሚዎችን ተጋርተው በርካታ የሚባሉ አመታትን በስራ አሳልፈዋል። በነዚህ አመታት መሀልም ያለው ከሌለው ተበድሮ አቅም ያጣው ለሌላው ብርታት ሆኖ ቆይቷል። እስካሁንም የአንዳቸው ችግር በሌላቸው የኪስ አቅም መላ ሲያገኝ ኖሯል።
እስከዛሬ ገንዘብ የቂምና የመቀያየም ምክንያታቸው አልነበረም። በዚህ ሰበብም ለክፉ የደረሱበት አጋጣሚ የለም። አሁን ግን አቶ በድሉ ይህ ሁሉ በ«ነበር» ቀርቷል።እያሉ ነው።«የቅርብ ወዳጄ» ያሏቸው አጋር የትናንቱን መልካምነት ረስተው ገንዘብን መርጠዋል። ቃላቸውን አጥፈውም ታማኝነ ትን ዘንግተዋል። ይህ እውነት ደግሞ ለእሳቸው ታላቅ ክህደት ነው።
አቶ በድሉ ዕንባ ባነቀው አንደበት መናገራቸውን ቀጥለዋል። ወዳጃቸው አቶ ቢሆነኝ ማሩ ከወራት በፊት ሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር እንደተበደሯቸው ያስታውሳሉ። በተነጋገሩት መሰረትም ባስቀመጡት የጊዜ ገደብ ቃላቸውን ጠብቀው ገንዘቡን ሊመልሱላቸው እንደነበር ይገልጻሉ። ይህ አይነቱ ልማድ ደግሞ በንግድ ሰዎች መሀል የተለመደና አሁንም ድረስ ያለ እውነት ነው።
እሳቸውም ቢሆኑ በወቅቱ ብሩን ሲያበድሩ ያለ አንዳች ስጋትና ጥርጣሬ ነበር።የዛኔ ባልንጀራቸው የጠየቋቸውን ገንዘብ አበድረው ወራትን ጠበቁ። እንደተባለው ሆኖ ግን ገንዘቡ በጊዜው አልተመለሰም።ይሁን እንጂ ያለመሰልቸት ጊዜ ወስደው ጠበቁ። ለውጥ ግን አልነበረም። ውሎ ሲያድር ነገሩ አሳሰባቸው። ከተበዳሪው አንዳች ምልክት ቢያጡ ደግሞ በአካል ቀርበው ጉዳዩን ሊያስታውሱ ሞከሩ።ባስ ባለ ጊዜም ገንዘባቸውን እንደሚፈልጉ ጠቅሰው እንዲመልሱላቸው ጠየቁ።
ተበዳሪው የባልንጀራቸው የአቶ በድሉን ጥያቄ በሰሙ ጊዜ ለመልሱ ፈጠኑ። እስካሁን በማቆየታቸው ተቆጭተውም ይቅርታ ጠየቋቸው። ጥቂት ቆይተው ደግሞ ባዘጋጁት የገንዘብ ቼክ የባንክ ቁጥራቸውንና ስማቸውን ከፊርማቸው ጋር አኑረው ገንዘቡን መውሰድ እንደሚችሉ ገለጹላቸው። በድሉ የተሰጣቸውን ቼክ በጥንቃቄ ከኪሳቸው አስቀምጠው ወደ ተባለው ባንክ ገሰገሱ።
አቶ በድሉ ይህን እውነት መለስ ብለው ሲያስታውሱ ይበልጥ ንዴታቸው ገንፍሎ ጥርሳቸውን ነከሱ። እልህና ቁጭትም በፊታቸው ይነበብ ያዘ።መርማሪው ፖሊስ ማስታወሻውን እያመቻቸ ቀጣዩን ታሪክ እንዲነግሩት ጠበቀ። አበዳሪው በድሉ የሆነውን ሁሉ ሊዘረዝሩ ትንፋሽ ወስደው ተረጋጉ።
የማመልከቻውን ፍሬ ሀሳብ አንድ በአንድ የቃኘው መርማሪ ዝርዝር ጉዳዩን በውል ማጤን ጀመረ። የሰውዬው ጽሁፍ ላበደሩት የገንዘብ ክፍያ ሲባል የተቆረጠላቸው ቼክ ደረቅ መሆኑን ያመለክታል።ይህም ስንቅ አልባ ሰነድ በባንኩ ባለሙያዎች ተመርምሮ ስለመረጋገጡ ጭምር ይጠቅሳል።አመልካቹ አያይዘውም ጉዳዩን ፖሊስ መርምሮ ለህግ ያቀርብላቸው ዘንድ በአክብሮት ጠይቀዋል።
የተበዳይን ጥያቄ በአካል ተቀብሎ ማመልከቻቸውን የመረመረው ፖሊስ ጉዳዩ በተገቢው የህግ አካል ይታይ ዘንድ ወደሚመለከተው አካል አስተላለፈ ።አቶ በድሉም በተሰጣቸው የህግ ምክር መሰረት ተገቢውን ክስ መስርተው መብታቸውን መጠየቅ እንደሚችሉ ተረድተው ከቢሮው ወጡ ።
ፖሊስና የምርመራ ጉዞ
አቶ በድሉ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ክፍል ቀርበው «አቤት» ካሉ ጀምሮ የፖሊስ ቡድን ተዋቅሮ የምርመራ ሂደቱ ቀጥሏል። በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 072/2000 የተደራጀው መዝገብም ጉዳዩን አስመልክቶ በየቀኑ የሚገኙ መረጃዎችን በአግባቡ ይመዘግባል። በምክትል ሳጂን ኤፍሬም በዳሳ መሪነት የሚካሄደው የምርመራ ሂደት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው።
አሁን ተበዳሪው አቶ ቢሆነኝ ማሩ ይገኙበታል በተባለ አድራሻ እየተፈለጉ ነው።ግለሰቡን በህግ አካል ይዞ ተገቢውን ምርመራ ለማካሄድም በህጋዊ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወደሚመለከተው ክፍል እንዲደርሱ ማድረግ ይጠበቃል። ፖሊስ ይህ ይሆን ዘንድ ተፈላጊውን ግለሰብ በመጥሪያ አፈላልጎ ለጥያቄ አቀረበ ።ተጠያቂው ለቀረበላቸው ፖሊሳዊ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ጀመሩ።
በአዲስ አበባ ከተማ የቀድሞው ወረዳ 1 ቀበሌ 09 ልዩ ስሙ ቶታል በሚባል አካባቢ የሚኖሩት የሰማንያ አምስት አመቱ አዛውንት አዲስ አበባን ከስልሳ አመታት በላይ ያውቋታል።የዛኔ ከተማዋን ሲያገኟት እንደዛሬው በዘመናዊነት ተቃኝታ አልነበረም።በወቅቱ ከትውልድ ሀገራቸው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት የመነሻ ምክንያታቸው በአቅማቸው የጀመሩት የንግድ ስራ ነበር።
እሳቸውና የከተማ ህይወት የተዋወቁት በአስራ ዘጠኝ ሰላሳዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነበር። ጊዜው ጣሊያን ሀገሪቱን የወረረበት ወቅት በመሆኑ ከጸጉረ ልውጦቹ ባዕዳን ብዙ ሙያዎችን መማር ችለው ነበር። ጠላት ለቆ ከወጣ በኋላ ደግሞ ራሳቸውን አበርትተው በርካታ ስራዎችን ሲሞካክሩ ቆይተዋል። የወጣትነት ዕድሜ አግዟቸውም በተሰማ ሩበት የንግድ ሙያ እየከበሩና እያደጉ መምጣትን አወቁ።
ቢሆነኝ ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ አቅማቸውን ሲያበረቱ በከተማዋ አንድ አካባቢ የነዳጅ ማደያ ከፍተው አመታትን ሰሩበት። በሌሎች የንግድ ሙያዎች ተሰማርተውም ትርፍና ኪሳራቸውን ለዩ። ዕድሜያቸውን በቆጠሩበት የንግድ ስራ ከበርካቶች ጋር ተዋውቀዋል። አበድረውና ተበድረውም እንደወጉ ሆነው ኖረዋል።
ቃል መስጠት
ፖሊስ አዛውንቱ ቢሆነኝ በተከሰ ሱበት የገንዘብ መበደር ጉዳይ ጥያቄ አቀረበላቸው። የእሳቸው ምላሽ « አዎ! በትክክል ገንዘቡን ተበድሬያለሁ » የሚል ሆነ ። የተበደሩትን ዕዳ በተባለው ቀን ሊመልሱ ቃል መግባታቸውንም ተናገሩ።ለገንዘቡ ዋስትና ይሆን ዘን ድም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራዳ ቅርንጫፍ በስማቸው ተመዝግቦ ህጋዊ ቁጥርና የፊርማ ማረጋገጫ ያለው ቼክ መጻፋቸውንም በቃላቸው አረጋገጡ።
ፖሊስ ከተበዳይ በደረሰው መረጃ መሰረት የተከሳሽን ሙሉ ቃል ተቀብሎ ማስፈር ጀመረ ። ለምርመራ ይበጁት ዘንድም ተገቢውን መረጃና ማስረጃዎች በወጉ ሰንዶ ያዘ።ተከሳሹ አቶ ቢሆነኝ ለተጠየቁት ሁሉ «አለኝ» የሚሉትን ምላሽ ከሰጡ በኋላ በአንድ ጉዳይ ላይ እንደማይስማሙ ገልጸው ሀሳቡን በግልጽ ተቃወሙ። ብድሩን ከግለሰቡ ወስደው በቼክ ለመክፈል መስማማታቸውን ቢያምኑም በጉዳዩ ተጠያቂ ያደረጋቸውን የደረቅ ቼክ ጉዳይ በተለየ እንደሚያዩት ጠቅሰው ተቃውሟቸውን በአሉታ አስቀመጡ።
ግለሰቡ በተጠየቁበት የቼክ ማጭበ ርበር ጉዳይ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን እየተናገሩ ነው። ስማቸው የጠፋውና ለክስ የቀረቡት በተገቢው መንገድ አለመሆኑን ጠቅሰውም በደረሰባቸው ተገቢ ያልሆነ ክስ ለእንግልት መዳረጋቸውን ማማረር ጀምረዋል። ከተጠየ ቁበት የወንጀል ድርጊት ነጻ የሚያደርጓቸውን ማስረጃዎች ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውንም በእርግጠኝነት እየተናገሩ ነው ።
ፖሊስ የተከሳሹን ሀሳብ በአግባቡ አጢኖ «አለኝ» ስለሚሉት ማስረጃ ማብራሪያ ጠየቀ። እሳቸውም ቼኩ የራሳቸው ስለመሆኑ አረጋግጠው በተከሰ ሱበት ጉዳይ ተጠያቂ የሚያደርጋቸውን የጽሁፍና የፊርማ ጉዳይ እንደማያምኑበት አስታወቁ። ለዚህ ያስቀመ ጡት ዋንኛ ምክንያት ደግሞ ፊርማውም ሆነ የእጅ ጽሁፉ የእርሳቸው አለመሆኑን ነበር።
የምርመራ ቡድኑ ከተከሳሹ የቀረበ ለትን የመቃወሚያ ሀሳብ ይዞ ጉዳዩን በጥልቀት ማጤን ጀመረ። አቶ ቢሆነኝ ላቀረቡት «ክሱን አልቀበለውም» የሚል ጥያቄ መከላከያ ይሆን ዘንድም ከሚመለከታቸው አካላት ማረጋገጫ ያቀርቡ ዘንድ መብቱን ሰጣቸው። አዛውንቱ ቢሆነኝ ለዚህም ቢሆን ተገቢውን ማስረጃ እንደሚያቀርቡ በመናገር በቂ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠየቁ።
አዛውንቱ ተከሳሽ ቀደም ሲል ይጠቀሙባቸው ከነበሩ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎችና ከሚኖሩበት ክፍለ ከተማ የፊርማ ማረጋገጫ ናሙናዎች ማቅረብ እንደሚችሉ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረትም ከሚመለከታቸው ክፍሎች ማረጋገጫዎቹ እንዲቀርቡ ዕድሉ ተሰጣቸው።
ቢሆነኝ በፍርድ ቤት ቀርበው ባመለከቱት መሰረትም በገቢዎች መስሪያ ቤትና በመኖሪያ ቀበሌያቸው እንዲሁም በባንኩ የመሀል አራዳ ቅርንጫፍ የሚገኙትን ጨምሮ ሌሎች ናሙናዎችን አሰባስበው ለማቅረብ የሚያስችላቸውን መረጃዎች ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ጠየቁ።
በፖሊስ አቅራቢነት፣ በአቃቤ ህግ ከሳሽነትና በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ለጥያቄ ከቀረቡት ግለሰብ ይኖራሉ የሚባሉ ማረጋገጫዎች ለማግኘት በየስፍራው እንቅስቃሴው ተጀመረ ።ፖሊስም ተገቢውን የህግ ማስረጃ ለማግኘት የሚያስችሉትን አሰራሮች ዘርግቶ በየስፍራዎቹ አቀና።
ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የተቀበሉት ተቋማት የተባሉትን ይፈጽሙ ዘንድ ግድ ሆነ።የተጠቀሱት ተቋማት ከግለሰቡ ጋር በነበራቸው የስራ ግንኙነት በየማህደሮቻቸው ያሰፈሯቸውን ፊርማዎችና የእጅ ፅሁፎች ናሙና በአግባቡ እየለቀሙ ለሚመለከተው አካል የመላክ ስራቸውን አጠናቀው ሰነዶቹን አዘጋጁ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ክፍል ከየስፍራው የተሰባሰቡትን የጽሁፍና የፊርማ ናሙናዎች ለይቶ በየመልካቸው አስቀመጠ። እውነታው በምርመራ ነጥሮ ምላሹ ይታወቅ ዘንድም ለፌዴራል ፖሊስ የወንጀልና ፎረንሲክ ዋና መምሪያ በመላክ የምላሹን ማብራሪያዎች ለመረዳት የሚያስችለውን ጊዜ ወስዶ ቀናትን ጠበቀ።
ጉዳዩን መመርመር የጀመረው የከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ማስረጃ ዎችን ማግኘት የሚያስ ችሉ ተቋማትን ለይቶ ትዕዛዙን አስተላ ልፏል። በአካል ቀርበው ምስክርነት መስጠት የሚችሉ አካላትን በመለየትም ምስክርነታቸውን በቃለ መሀላ እንዲያረ ጋግጡ የማድረግ ሂደትን ሲያከናውን ቆይቷል።
ፍርድ ቤቱ በተበዳይ የክስ ቃል መሰረትና በጠየቃቸው ማስረጃዎች በኢት ዮጵያ ንግድ ባንክ በግለሰቡ ስም የተከፈተ የባንክ አካውንት መዘጋቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃን ተቀብሏል። ፍርድ ቤቱ ለመረ ጃው ጥንካሬ የሚያግዙትን ተጨማሪ ሰነዶች በማከልም ተገቢ በሚባሉ አካላት ማረጋገጫዎች ያገኘውን መረጃ በማስረጃነት መዝግቦ አስፍሯል።
አሁን ለምርመራ ይሆን ዘንድ ከየተቋ ማቱ በትውስት የመጡት የጽሁፍና የፊርማ ናሙናዎች ተመርምረዋል።ህግና ደንቡ በሚያዘው መሰረትም ተገቢውን ውጤት ለሚመለከተው አካል የማቅረብ ስራው ተጠናቆ ምላሹ ለፍርድ ቤቱ ተልኳል።
ውሳኔ
ወራትን ሲያከራክር የቆየው የቼክ ማጭበርበር ጉዳይ በተከሳሽና በከሳሽ አቃቤህግ ቃል ተያይዞ በማስረጃዎች ተጠናክሯል።ተገቢው መረጃዎች፣አስፈላጊ ማስረጃዎችና የሰው ምስክሮችም ለክሱ ሂደት እንዲያግዙ ሆነው በተገቢው መንገድ ሲከናወኑ ቆይተዋል።በፎረንሲክ የምርመራ ስራዎች ተገቢው ማስረጃ የተገኘባቸው ማሳያዎች ለፍርድ ሂደቱ በአስረጂነት ቀርበው በዋቢነት ተይዘዋል።
ህዳር 30ቀን 2001 ዓም
እነሆ ! በዚህ ቀን የፌዴራል ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ዳኞች በስፍራው ተሰይመዋል።የከሳሽ አቃቤ ህግና የተከሳሹ የማስረጃ ማሰባሰብ ሂደት በወጉ ተጠናቆ ለፍርድ ውሰኔ ተቀጥሯል።ተከሳሹ በገንዘብ ብድር ምክንያት በፈጸሙት የቼክ ማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ መሆናቸው በህግ ተረጋግጧል።
ይህ ድርጊት በተገቢው ማስረጃዎች በመረጋገጡም ተከሳሹ አዛውንት አቶ ቢሆነኝ ማሩ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ የሚታሰብ የአንድ አመት እስራትና የ3000 ብር የገንዘብ ቅጣት፣ እንዲሁም ለሁለት አመታት ከማንኛውም ህዝባዊ መብቶቻቸው ታግደው እንዲቆዩ የሚያስችል የገደብ ቅጣት ተጥሎባቸው መዝገቡ ተዘግቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
መልካምስራ አፈወርቅ