አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ማኅበራዊ ሚዲያን ልታግድ ነው

የአውስትራሊያ መንግሥት ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት የትኛውንም ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያግድ ሕግ ሊያወጣ ነው። ለሀገሪቱ ፓርላማ በሚቀጥለው ሳምንት የሚቀርበው ረቂቅ ሕግ ማኅበራዊ ሚዲያ በአውስትራሊያ ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት “ለመከላከል” ያለመ እንደሆነ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ ተናግረዋል።

“ይህ ሕግ ለአባቶች እና ለእናቶች ነው። እንደእኔ ወላጆች በኢንተርኔት ላይ የልጆቻችን ደኅንነት አሳምሞናል። የአውስትራሊያ መንግሥት በዚህ ሕግ ከጀርባችሁ ነኝ እያለ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የረቂቅ ሕጉ ዝርዝር ለፓርላማ ቀርቦ ክርክር የሚደረግበት ቢሆንም እገዳው ቀድሞውኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሉ ታዳጊዎች ላይ እንደማይተገበር መንግሥት አስታውቋል።

ሆኖም ወላጆች ፍቃድ ቢሰጧቸውም ከተጠቀሰው ዕድሜ በታች ያሉ ህጻናት ማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም አይችሉም። ህጻናቱ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እንዳይጠቀሙ ለመከላከል ተገቢ እርምጃዎችን መውሰድ የማኅበራዊ ሚዲያ ባለቤቶች ኃላፊነት እንደሚሆንም መንግሥት አስረድቷል።

አልባኔዝ በህጻናቱ ተጠቃሚዎች ላይ ምንም ዓይነት ቅጣት አይኖርም ቢሉም ሕጎቹን ማስከበር የአውስትራሊያ የኢንተርኔት ተቆጣጣሪ ኢ-ሴፍቲ ኮሚሽነር እንደሚሆን ገልጸዋል። ይህ ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ የሚያግደው ሕግ ከጸደቀ ከ12 ወራት በኋላ ተግባራዊ ይሆናል የተባለ ሲሆን፣ በየጊዜውም ግምገማ ይደረግበታል ተብሏል።

አብዛኞቹ ባለሙያዎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች የታዳጊዎችን አዕምሯዊ ጤንነት ሊጎዱ እንደሚችሉ ቢስማሙም ሙሉ በሙሉ ይታገድ በሚለው ላይ ተከፋፍለዋል። አንዳንዶች እገዳዎች ውስብስብ የሆነውን የኢንተርኔት ዓለም እንዴት ማሰስ እንደሚችሉ ከማስተማር ይልቅ እንደ ቲክቶክ፣ ኢንስታግራም እና ፌስቡክ ላሉ መተግበሪያዎች ያላቸውን ተጋላጭነት የሚያዘገይ እንደሆነ ይተቻሉ።

ቀደም ሲል የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ህጻናትን ከማኅበራዊ ሚዲያ ለመገደብ የተደረጉ ሙከራዎች አልተሳኩም ወይም አተገባበራቸው ፈታኝ ሆኗል። ለዚህም ደግሞ አንደኛው ምክንያት የዕድሜ ማረጋገጫ መስፈርቶችን ሊያሳልፉ የሚችሉ መተግበሪያዎች በመኖራቸው ነው።

መንግሥት ያቀደውን እገዳ በሀገሪቱ ካሉ የህጻናት መብት ተሟጋች ቡድኖች ትልቁ የሆነው የአውስትራሊያው የህጻናት መብቶች ግብረ ኃይል ተችቶታል። ግብረ ኃይሉ ከ100 በላይ ምሁራን እና 20 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የፈረሙበት ግልጽ ደብዳቤ ለመንግሥት ያስገባ ሲሆን፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ከማገድ ይልቅ “የደኅንነት መመሪያዎችን” እንዲያስተዋውቁ ጠይቋል።

ቡድኑ በተጨማሪም ኢንተርኔትን ለመቆጣጠር የተነደፉ “ብሔራዊ ፖሊሲዎች” ህጻናት የዲጂታል ከባቢያቸው ጋር እንዲገናኙ እና ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ መረጃዎችን እንዲያገኙ ዕድል መስጠት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ምክርን ጠቁሟል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You