ከረሃብ ነፃ የሆነች ዓለምን ለመፍጠር የተባበረ ዓለም አቀፍ ምላሽ ይፈልጋል!

ረሀብ ዓለማችንን ክፉኛ ከሚፈታተኗት ችግሮች መካከል የሚጠቀስ ነው ። ችግሩ በድሀና ኋላ ቀር ሀገራት ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም፤ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች በሚታዩባቸው የዓለም አካባቢዎችም በስፋት ይስተዋላል። በችግሩም ለሞት እና ለስደት የሚዳረጉ ሰዎችም ቁጥር በቀላሉ የሚታይ አይደለም ።

ዓለም የሰውን ልጅ መመገብ የሚያስችል በቂ አቅም እንዳላት ይታመናል፤ ይህንን አቅም በኃላፊነት መንፈስ በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ዝግጁነት መፍጠር ባለመቻሉ፤ ቴክኖሎጂ ከፍ ያለ እመርታ ባሳየበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ረሀብ የዓለማችን አጀንዳ እንደሆነ ቀጥሏል።

በአንድ በኩል የሰው ልጅ ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ትኩረት ከመንፈጉ ጋር በተያያዘ እየተፈጠሩ ያሉ የድርቅ አደጋዎች፣ በሌላ በኩል ሰው ሰራሽ በሆኑ ችግሮች ፣ ግጭቶች እና ጦርነቶች የተነሳ መሬት ጦሙን ማደሩ ፣ ሰዎችም ህይወታቸውን ለማቆየት አካባቢያቸውን ለቀው መሰደዳቸው ለረሀብ አደጋዎች መከሰት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።

የኢኮኖሚ እድገትን ታሳቢ ያደረገ የሥነ ሕዝብ ምጣኔ አለመኖር ፣ ምርት እና ምርታማነትን መሰረት ያደረጉ የግብርና ፖሊሲዎችን መተግበር የሚያስችል ቁርጠኝነት ማጣት ፣ ለጠባቂነት የሚያጋልጡ ብዙ ድካም እና ልፋት የማይፈልጉ ፖሊሲዎቻቸው ጥገኛ መሆን ለችግሩ ሌለኞቹ ምክንያቶች ናቸው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተጨባጭ የትብብር መድረኮች አለመፈጠር ፣ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚጠይቀው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ለችግሩ ሰለባ ለሆኑ ኋላቀር የዓለማችን ሀገራት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” መሆኑ ከችግሩ ለዘለቄታው ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል።

የምግብ እህል በራሱ አንድ የፖለቲካ ጫና ማሳረፊያ መሳሪያ እየሆነ የመምጣቱም እውነታ ፤በምግብ እህል እጥረት ውስጥ ያሉ ፣ ለረሀብ ተጋላጭነት ያላቸው ሀገራት ከችግሩ ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት ተገቢውን ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዳያገኙ ተጨማሪ ተግዳሮት እንደሆነባቸውም ይታመናል።

እነዚህን ውስብስብ ችግር ፈትቶ ከረሀብ ነፃ የሆነ ዓለም ለመፍጠር፤ ከሁሉም በፊት የተትረፈረፈ ምርት በሚመረትበት ፣ ገና ብዙ ማምረት በሚቻልበት ዓለም አንድም ሰው በየትኛውም ሁኔታ በረሀብ መሞት እንደሌለበት የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ወሳኝ ነው።

ችግሩን ለዘለቄታው ለመሻገር ፣ የግብርናውን ዘርፍ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ አቅሞችን/ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋት ፣ በተለይም ኋላቀር የሆኑ ሀገራት በቀላሉ ቴክኖሎጂዎችን በቅናሽ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና ለዚህ የሚሆን ዓለም አቀፍ ትብብር መፍጠር ተገቢ ነው።

ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ትኩረት መስጠት፣ ሰውሰራሽ በሆኑ ችግሮች ፣ ግጭቶች እና ጦርነቶች የተነሳ መሬት ጦሙን እንዳያድር ፣ ሰዎችም አካባቢያቸውን ለቀው እንዳይሰደዱ ግጭቶችን መከላከል የሚያስችል የተሻለ ዓለም አቀፍ የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን ማበጀት እና መተግበርን ይጠይቃል።

ሀገራት የግብርናውን ዘርፍ ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ ለሚቀርጿቸው ብሔራዊ ፖሊሲዎች ስኬታማነት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ፣ ለሚገኙ ውጤቶችም እውቅና መስጠት፣ የምግብ እህል አቅርቦትን የፖለቲካ መሳሪያ ከማድረግ መቆጠብ ፣ጉዳዩን ከሰብአዊነት አኳያ ማየት የሚያስችል አዲስ ምልከታ መፍጠር ያስፈልጋል።

ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የመንግሥታትን ፣ የሲቪል ማህበራትን ፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ፣የግሉን ዘርፍ እንዲሁም የግብርና ቴክኖሎጂ አምራች ኩባንያዎችን በአጠቃላይ የመላው ዓለም የጋራ ትብብር ወሳኝ ነው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ በተካሄደው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ጉባዔ ላይ ከረሃብ ነፃ የሆነች ዓለም ለመፍጠር የተባበረ ዓለም አቀፍ ምላሽ ይፈልጋል ማለታቸው።

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You