አካባቢያችን ያማረ እንዲሆን፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ጣቢያዎች፤ ንፁሕ የመጠጥ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ መንገዶች… በአጠቃላይ የተሟላ መሠረተ ልማት እንዲኖረን እንፈልጋለን፤ እንመኛለን። በሌሎች ሀገሮች ያየናቸው ቴክኖሎጂዎች የሥልጣኔ መንገዶች ሁሉ በሀገራችን ሆኖ ማየትን እንሻለን።
በውጪ ሀገራት በፊልምና በዶክመንተሪ ወይም ለጉብኝትና ለትምህርት በሄድንባቸው ሀገራት የምናያቸው የመንገድ መሠረተ ልማቶች በሀገራችን እንዲሆኑልን እንመኛለን። የግል መኖሪያ ቤት ባለቤት መሆንን እንፈልጋለን። መመኘት ብቻም ሳይሆን ለምን በእኛ ሀገር ብለን እንቆጫለን። መቼ ነው እኛም እንደ ውጪዎቹ የሠለጠንን የምንሆነው ብለን እናልማለን።
ሁሉንም የተመኘነውን ነገር ያሰብነውን ሁሉ ማድረግ ግን እንደሚቻል በቅርቡ ያየናቸው ጅምር ልማቶች ያሳዩናል። እነዚህን ነገሮች በተሟላ መልኩ ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባናል፤ ምን እንሥራ? እንዴት እንሥራ? ከእኔ ምን ይጠበቃል? እኔ ለማስበው የበለፀገች ሀገር ከእኔ የሚጠበቀው ምንድነው ብሎ ራስን መጠየቅ ደግሞ ያስፈልጋል። ሁልጊዜ ከድህነት ተስፈንጥረው የወጡ ሀገሮች ብለን የምንጠቅሳቸው አሉ። እነ ኮሪያ፣ ቻይና ሲንጋፖር … በዋናነት የምናነሳቸው ናቸው።
እነዚህ ሀገሮች የድህነትን ጥግ ያዩ ናቸው። አንዳንዶቹ ከእኛ ድጋፍ ያገኙ ሀገሮች መሆቸውን ታሪክ ጭምር ያሳየናል። እድገታቸው እኛ የሥልጣኔ በር ከፋች ከሆንባቸው ዘመን ባጠረ ጊዜ ነው። ታሪካቸው የቅርብ ጊዜ ነው። ሆኖም ግን አንድ ጀነሬሽን የሆነ ቦታ ላይ ቆም ብሎ በቆራጥነትና በትብብር አንድ በመሆን፤ ለለውጥ በመነሳት ተጠቃሽ ሀገር ለመሆን በቅተዋል። ምንም በልተው ምንም ሆነው ብቻ ዛሬ ለደረሱበት የእድገት ደረጃ በቅተዋል። የአደጉ ሀገራት የሚለውም መገለጫቸው ሆኗል። ከእነዚህ ሀገራት ምን እንማራለን ?
እኛስ እንዴት ወደ ብልፅግናው እንጓዝ ብለን ቆም ብለን ማሰብ አለብን። መጎነታተሉን፣ መሳሳቡን፣ ሴራን ትተን ሥራ ሠርተን ለሀገር መሥራት እንዳለብን ማወቅ አለብን። ከሙስና የፀዳ ሥራ መሥራት አለብን። ከሁላችን የሚጠበቅብንን ግብርና ታክስ ሌላውንም መክፈል አለብን። “የቄሳርን ለቄሳር…” እንደሚባለው ማለት ነው። ያኔ በሀገራችን የምንፈልገውን ልማት እናያለን ።
ያኔ ለምን መሠረተ ልማት አልተሟላላንም ብለን እንጠይቃለን። ይሠራልን ብለን ድምፃችንን ከፍ አድርገን መውቀስ እና መክሰስ እንችላለን። ማንም ሰው ሊኖር የሚችለው በአንድ አይነት መንገድ አይሆንም፤ የሁሉም የሀብት መጠን ይለያያል። ሁሉም መክፈል ያለበት ግብር በእዛው መንገድ ይሆናል። ሁሉም መክፈል ያለበት ታክስ፤ ቫት የሰበሰበውም የንግድ ማኅበረሰብ የሰበሰበውን በሐቀኝነት ወደ መንግሥት ካዝና ማስገባት አለበት። ይሄ ግዴታ ነው፤ በዚህ መንገድ ተሰብስቦ ወደ ኪስ ማድረግ ኃላፊነትን ካለመወጣትም በላይ በሕግም ያስጠይቃል። ከእምነት አስተምሕሮ አንጻርም ኃጢያት ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ሁሉም የሚጠበቅበትን እያደረገ ነው? ብለን ስንጠይቅ ደግሞ መልሱ አስደሳች አይሆንም። ምንም አይነት ልማት ሊመጣ የሚችለው ገንዘብ ከሰማይ ወርዶ አይደለም፤ በመሥራት ነው። ሥራን ሳይንቁ፣ ጊዜ ሳይቆጭቡ፣ ገንዘብ ገንዘብ ሳይሉ ነው። በተሰማሩበት ሙያና ኃላፊነት በታማኝነት በመሥራት ነው።
የንግዱ ማኅበረሰብን ልክ እንደ መንግሥት ሠራተኛው የሚጠበቅባቸውን ግብር ሳይደብቁና ሳይሰውሩ ሲከፍሉ ነው። በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ በግዢ፣ በግንባታና በሌሎች ምክንያት የሚባክን እና የሚሰረቅ ገንዘብ ለተገቢው አገልግሎት ማዋል ሲቻል ነው። እስካሁን የሚታዩት ነገሮች ከዚህ በብዙ የራቁ ናቸው።
በሠራተኞች በብዛት የሚፈለጉ የሥራ መደቦች አሉ። ለምን ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። በተማሪዎች የሚመረጡ የትምህርት ዘርፎች አሉ፤ የእጅ መንሻ የሚያስገኙ፣ ባለጉዳይ የሚበዛባቸው (ቢዝነስ ያለው)። የተማሪውም ሆነ የወላጅ ምርጫ መሆን ያለበት ተማሪው የተሻለ ዝንባሌ ባለበት የትምህርት መስክ ላይ እንዲሠማራ ግፊት መደረግ ነው።
ለሀገሩ በሙያው የተሻለ ሥራ መሥራት የሚችለውም በዝንባሌው ሲማር መሆኑን ማወቅ ይገባል። ይሄ ደግሞ ኮትኩቶ ከሚያሳድግ ቤተሰብ፣ ከሚያስተምር መምህር እና ከማኅበረሰቡ የሚጠበቅ ነው። ተማሪዎች ነጭ ወረቀቶች ናቸው። በአብዛኛው መምህራን በቀረጿቸው ልክ ነው የሚበቅሉት። ስለዚህ መምህራን ብቁና ንቁ ተማሪዎችን ለሀገር ማበርከት አለባቸው፤ በሥነምግባር የተቀረጹ ዜጎችን ማፍራት ይጠበቅባቸዋል።
አገልግሎት ፈልገን በምንገባባቸው የመዝናኛ ስፍራ፣ ምግብና መጠጥ ቤቶችም ሆነ ሌሎች የገበያ ቦታ “ደረሰኝ ሳይቀበሉ ሂሳብ አይክፈሉ” የሚል ማስታወቂያ አለ ። ይሄ ሕጋዊ የሆነ ግብይት እና አገልግሎት ማግኘትን ማረጋገጫ ነው። ምን ያህል ለዚህ ማስታወቂያ እራሳችንን ያስገዛን ነን?።
እኛም ደረሰኝ መቀበል መብታችን ቢሆንም ጠይቆ የመቀበል ልምድ የለንም ወይም ቸልተኛ ነን። አገልግሎት ሰጪውም ሂሳቡ ሲከፈለው ደረሰኝ መቁረጥ አይፈልግም። ከተገልጋዩ የሚሰበስበውን የመንግሥት ቫት እንኳን በአግባቡ ገቢ ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለም።
አብዛኛው የንግዱ ኅብረተሰብ ከመንግሥት ጋር አይጥና ድመት የሚጫወት ነው። አንዴ ገቢ በመቀነስና በመሰወር፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሰበሰበውን ታክስ ገቢ ባለማድረግ እየተጋለጠ የአደባባይ ምስጢር ነው። ለመንግሥትም ትልቅ እራስ ምታት የሆነ ማኅበራዊ ችግር ነው። የታማኝነት ችግር በንግዱ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን በደመወዝ በተቀጠረው የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞች ላይ የሚስተዋል ነው ።
ይሄ ደግሞ የትም አያደርስም፤ እድገትንም አያመጣም። የተሻለች ሀገር ፈጥረን ለትውልድ ለማስተላለፍ የምንችልበትን ዕድል የሚያበላሽ ነው። ከዚህ ሀገራዊ ችግር ለዘለቄታው ለመውጣት ሁሉም በተሠማራበት የሥራ መስክ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል፤ ይህን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው የበለፀገች ሀገር መፍጠር የምንችለው። ቸር እንሰንብት !
አዶኒስ (ከሲኤምሲ )
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም