ሩሲያ በመሬት ላይ ያለውን ከባቢያዊ የአየር ሁኔታ የሚቆጣጠሩ ሁለት ሳተላይቶቸን እና ከኢራን የመጡ ሁለት ሳይተላይቶችን ጨምሮ 53 ሳይተላይቶችን የተሸከመ ሶይዙ ሮኬት ማምጠቋን ሮስኮስሞስ ስፔስ ኤጀንሲ አስታውቋል።
ኤጀንሲው እንደገለጸው ከሩሲያ ቮስቶቺኒ ኮስሞድሮም የተነሳው ሶይዙ ሮኬት የመሬትን አዮኖስፌር ክፍል ለመከታተል የሚያስፈልጉ ሎኖስፌራ-ኤም ሳተላይቶችን ወደ ሕዋ አምጥቋል። እንደ አሜሪካው የጠፈር ምርምር ማዕከል ናሳ ከሆነ የመሬት ከባቢ አየር ከሕዋ ጋር የሚገናኝበት አዮኖስፌር ከመሬት ገጽ በላይ ከ80 እስከ 644 ኪሎሜትር ርቀት ይሸፍናል።
የእያንዳንዱ ሎኖስፌራ-ኤም ክብደት 430 ኪሎግራም ሲሆን የሚሠራበት ምሕዋር ወይም ኦርቢት 820 ኪሎሜትር መሆኑን ሮይተርስ የሩሲያውን ኢንተርፋክስ ዜና አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል። ሮስኮስሞስ እንደገለጸው ቀጣዮቹ ሁለት መሣሪያዎች እ.አ.አ. በ2025 ይላካሉ።
ከ53 አነስተኛ ሳተላይቶች ውስጥ የኢራኖቹ ከፍተኛ የምስል ጥራት ያለው ሳተላይት እና አነስተኛ የኮሙኒኬሽን ሳይተላይት እንዲሁም የመጀመሪያው የሩሲያ-ቻይና ተማሪዎች ሳተላይት ይገኙበታል ተብሏል።
ሩሲያ ባለፈው የካቲት ወር የኢራንን መልክዓ ምድር የሚያስስ ሳተላይት ወደ ሕዋ ማምጠቋን በወቅቱ ተዘግቦ እንደነበር አል-አይን ኒውስ ዘግቧል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም