የመም ውድድሮችን ያነቃቃል የተባለው ‹‹የግራንድ ስላም›› ፉክክር

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በረጅም ርቀት የመም (ትራክ) ውድድሮች በዓለም ላይ እየቀነሱ መሄዳቸው የርቀቱ ከዋክብት አትሌቶች ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ በግልፅ ታይቷል። በዚህ ምክንያት በርካታ የትራክ አትሌቶች በጊዜ ፊታቸውን ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች ለማዞር ተገደዋል። ይህም እንደ ኢትዮጵያና ኬንያ ያሉ ሀገራት ዓለም አቀፍ የመም ውድድሮች ላይ ያላቸውን ውጤት በማቀዛቀዝ ረገድ ትልቅ ተፅዕኖ እንዳሳደረ የብዙዎች እምነት ነው። ይህም ኦሊምፒክንና የዓለም ሻምፒዮናን በመሳሰሉ ውድድሮች ታይቷል፡፡ ከዚህም ባለፈ የረጅም ርቀት በተለይም የ5 እና 10 ሺ ሜትር ውድድሮች ከኦሊምፒክ የመሰረዝ አደጋ እንደ ተጋረጠባቸው ሲነገር መቆየቱ ይታወቃል፡፡

ሰሞኑን ከወደ አሜሪካ የተሰማው ዜና ግን የመም ውድድሮችን ያነቃቃል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ በመም ውድድሮች ታሪክ ከፍተኛ ሽልማት የሚያስገኘው ‹‹የግራንድ ስላም›› ውድድር በመጪው ሚያዚያ ወር በአሜሪካ እንደሚጀመር ይፋ ተደርጓል፡፡

ይህ ውድድር በቅርብ ዓመታት በውድድር ቁጥር ማነስ ምክንያት እየተቀዛቀዘ የነበረውን የትራክ ሩጫ ያነቃቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በቀድሞው የአራት ጊዜ የኦሊምፒክ አሸናፊ አትሌት ማይክል ጆንሰን የተመሠረተ ነው፡፡ የትራክ ግራንድ ስላም ውድድር እ.ኤ.አ በመጪው ሚያዚያ 2025 የትራክ እና የሜዳ ተግባራት ፉክክሮችን አካቶ እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡

ውድድሩ የተነደፈው የመም ተፎካካሪ አትሌቶች የመታየት እና የስፖንሰርሺፕ ዕድሎችን እንዲያገኙ ለመርዳት ሲሆን፣ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ከሚካሄደው ኦሊምፒክ በተቃራኒው የግራንድ ስላም ትራክ ሊግ በዓመት አራት ጊዜ ይካሄዳል። ይህም ትልልቅ አትሌቶች በተደጋጋሚ እርስ በእርስ እንዲፎካከሩና የተለያዩ ዕድሎችን እንዲያገኙ ዕድል ይከፍታል ተብሎ ታምኖበታል።

ውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች ከ100 ሜትር እስከ 5 ሺህ ሜትር ድረስ የሚሮጡ አትሌቶች በውድድር ዓመቱ ባስመዘገቡት የተሻለ ሰዓት መሠረት ተጋብዘው ወይም በማኔጀሮቻቸው አማካኝነት የመካፈል ዕድል እንዲያገኙ ይረዳል።

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፅጌ ገብረሠላማ በዚህ ውድድር ላይ አስቀድማ በመመዝገብ የመጀመሪያዋ አትሌት መሆኗ ታውቋል፡፡ ልክ እንደሷ ሁሉ ከመም ውድድሮች ወጥተው በጎዳና ላይ ውድድሮች ትኩረታቸውን ያደረጉና ለማድረግ ያሰቡ በርካታ ከዋክብት አትሌቶችም ወደ ትራክ ውድድሮች እንደሚመለሱ ይጠበቃል፡፡

በተደጋጋሚ የትራክ ውድድሮች ቁጥራቸው እየቀነሰ ነው ለሚሉ አሠልጣኞች እና አትሌቶች ይህ ውድድር የተሻለ ዕድል ይዞ እንደመጣም የተለያዩ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡

በአጠቃላይ 96 አትሌቶች የሚካፈሉበት አዲስ የትራክ ግራንድ ስላም ሊግ በአራት ግራንድ ስላም ውድድሮች የመጀመሪያ ዓመት እስከ 12.6 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ማዘጋጀቱ ተዘግቧል፡፡ በእያንዳንዱ ውድድር በድምሩ 3 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለሽልማት ቀርቧል።

በሎስአንጀለስ ከተማ መቀመጫውን ያደረገው የትራክ ግራንድ ስላም ውድድር ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቬስትመንት ለውድድሩ እንደሚያዘጋጅም አረጋግጧል።

ሌትስ ረን የተባለው የአትሌቲክስ ድረ ገፅ ባሳለፍነው መስከረም ወር ባወጣው መረጃ መሠረት ውድድሩ በሎስንጀለስ፤ ኒውዮርክ፣ ጀማይካ ኪንግስተን እና በእንግሊዝ በርሚንግሃም በሚያዚያ ወር ሁለት ሳምንት እና በግንቦት ወር ሁለት ሣምንት እንደሚካሄድ ዘግቧል።

የትራክ ግራንድ ስላም ውድድር አትሌቶች በአንድ የውድድር ዘርፍ አራቱን የግራንድ ስላም ሊጎች ቢያሸንፉ 400 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያገኛሉም ተብሏል። በአንድ ሊግ የግራንድ ስላም የሽልማት ገንዘብ 1ኛ 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ 2ኛ 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ 3ኛ 30 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ 4ኛ 25 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ 5ኛ 20 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ 6ኛ 15 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ 7ኛ 12 ሺህ 500 የአሜሪካ ዶላር፣ 8ኛ 10 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደሚሆን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ቦጋለ አበበ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You