የስፔን ተቃዋሚዎች በንጉሡና ንግሥቲቷ ላይ ጭቃ ወረወሩ

ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ለሞቱበት የስፔኑ የጎርፍ አደጋ የተሰጠው ምላሽ በቂ አይደለም ያሉ ተቃዋሚዎች በንጉሡና ንግሥቲቱ ላይ ጭቃ ወረወሩ።

ንጉሡና ንግሥቲቱ በከፋ የጎርፍ አደጋ የተመታችውን የቫሌንሺያ ግዛት ለመጎብኘት በሄዱበት ወቅት ነው የተቆጡ ተቃዋሚዎች ጭቃ እና ሌሎች ነገሮችን የወረወሩባቸው።

ንጉሣውያኑ ጥንዶች፣ የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትርና ሌሎች መሪዎች ፓይፖርታ የተሰኘችውን ከተማ እየጎበኙ ባለበት ወቅት “ነፍሰ ገዳይ” እና “እፈሩ” የሚሉ ስድቦችን ከተቃዋሚዎች ተሰንዝሮባቸዋል።

ንጉሥ ፌሊፔና ንግሥት ሌቲዚያ ፊታቸውና ልብሳቸው ጭቃ ተለውሶ ጉዳት የደረሰበትን ማኅበረሰብ ሲያጽናኑ ታይተዋል።

ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ የከፋ ነው በተባለው በዚህ ጎርፍ ከ200 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። የነፍስ አድን ሠራተኞች በሕይወት ያሉ ሰዎችን ለመታደግ እንዲሁም አስከሬኖችን ለማውጣት በመሬት ስር ባሉ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች እና መተላለፊያ ዋሻዎች ፍለጋቸውን ቀጥለዋል።

ጎርፉን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ አልነበረም በሚል እንዲሁም ለአደጋው የተሰጠው ምላሽ በቂ ባለመሆኑ ከፍተኛ ቁጣ ተፈጥሯል።

ንጉሡ ከመኪናቸው ወርደው በጠባቂዎቻቸውና በፖሊስ ታጅበው በእግረኛ መንገድ ላይ ሲጓዙ የተቆጡ በርካታ ተቃዋሚዎች ጭቃ እየወረወሩ፣ ዘልፈዋቸዋል፡፡

ጠባቂዎቻቸው እና ፖሊሶች ንጉሡን ከበው ቀለበት በመሥራት ከተቃዋሚዎቹ የሚወረወርባቸውን ጭቃ እና ቁሳቁሶች ለመከላከል ሙከራ አድርገዋል፡፡

ንጉሡ የሚወረወርባቸውን ጭቃ፤ ዘለፋና ስድብ ተቋቁመው በርካቶቹን አዋርተዋል፤ አለፍ ሲልም እያቀፉ አፅናንተዋል፡፡

የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ እና የቫለንሺያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ካርሎስ ማዘን በጉብኝቱ ላይ ንጉሣውያኑ ጥንዶችን ተቀላቅለው የነበረ ቢሆንም የተቃዋሚዎች ቁጣ መጠንከሩን ተከትሎ ከስፍራው በፍጥነት እንዲወጡ ተደርገዋል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You