ፖሊስ ‘ሕገወጥ የማዕድን ቆፋሪዎችን’ ከማዕድን ማውጫ ለማስወጣት ምግብ እንዲቋረጥባቸው አደረገ

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕገወጥ የማዕድ ቆፋሪዎችን ምግብና ውሃ በማቋረጥ ከነበሩበት የማዕድን ማውጫ እንዲወጡ በማስገደድ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጸ።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ሕገወጥ የማዕድን አውጪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በወሰደው ምግብና ውሃ የማቋረጥ ርምጃ 540 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆኑ ከሥራ ውጭ ከተደረገ የማዕድን ማውጫ እንደነበሩም ተገልጿል።

የፀጥታ ኃይሎች በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ማዕድን አውጪዎቹን ከጉድጓዱ ውስጥ ለማስወጣት ሲሉ ምግብ እና ውሃ እንዳይቀርብላቸው ከልክለዋል።

“ረሃብ እና የውሃ ጥም” ያጠቃቸው የማዕድን ቆፋሪዎች ከጉድጓዱ ለመውጣት መገደዳቸውን ፖሊስ ተናግሯል።

ከቅዳሜ ጀምሮ በሰሜን ኦርክኒ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው የማዕድን ማውጫው ውስጥ አንድ በአንድ መውጣት ጀምረዋል። አሁንም ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ በማዕድን ማውጫው ውስጥ እንዳሉ ይገመታል።

እሑድ ዕለት የሀገሪቱ የፖሊስ አዛዥ የፀጥታ ኃይሎች ከኃላፊነታቸው “ወደ ኋላ እንዳይሉ” እና “የሕግ የበላይነት መከበሩን እንዲያረጋግጡ” ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።

መግለጫው አክሎም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የፀጥታ ኃይሎች “ከሥራ ውጭ በተደረጉት የማዕድን ማውጫዎች አካባቢ ያሉ ማኅበረሰቦች ምግብ፣ ውሃ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለሕገ-ወጥ ማዕድን አውጪዎች እንዳያደርሱ አግደዋል” ብሏል።

ቅዳሜ ዕለት 225 ማዕድን አውጪዎች መውጣታቸወን ፖሊስ ገልጿል። አሁንም ግን “ሺህ እንኳን ባይሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ” ከመሬት በታች ናቸው ተብሎ ይታሰባል ሲል አክሎ ነበር።

ፖሊስ እሑድ ዕለት በሰጠው መረጃ ከማዕድን ማውጫው ውስጥ ተጨማሪ 340 ሰዎች መውጣታቸውን እና በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።

“ዛማ ዛማስ” (በዙሉ ቋንቋ ዕድላቸውን የሚሞክሩ እንደማለት ነው) በመባል የሚታወቁት በሺዎች የሚቆጠሩ ሕገ-ወጥ ማዕድን ማውጫዎች በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ።

የፖሊስ ኮሚሽነሩ ሌተናል ጀነራል ሻድራክ ሲቢያ እንደገለጹት ከሆነ ከታኅሣሥ 2023 ወዲህ በሰባት ግዛቶች ከ13 ሺህ 690 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

“283 ዶላር በጥሬ ገንዘብ እና ያልተቆረጡ እና 1.8 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ አልማዞች ይዘናል” ብለዋል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You