የሶፍት ዌር ምሕንድስና ተማሪዋ ጂቱ እውነቱ

የዛሬዋ እንግዳችን ጂቱ እውነቱ ትባላለች:: ያገኘናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ12ኛ ጊዜ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባዘጋጀው “ታዳጊ ሴቶች ላይ መስራት የነገን የተሻለች ሀገር መገንባት ነው “በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የታዳጊ ሴቶች ቀን፤ የታዳጊነት እና የዩኒቨርሲቲ ተሞክሮዋን ለታዳጊዎች ለማካፈል በመጣችበት ወቅት ነው::

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአምስተኛ ዓመት የሶፍት ዌር ምህንድስና ተማሪ ናት:: በታዳጊነት እድሜዋ የወደፊት ህልሟን አስረግጣ ስትናገር ሴት በመሆኗ ልታሳካው አትችልም በሚል እሳቤ በአካባቢዋ ያሉ ሰዎች ይዘብቱባታል:: ይህን የማህበረሰቡን ጫና ተቋቁማ ከፍተኛ ውጤት አምጥታ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ ያልጠበቀችው ፈተና ገጥሟታል:: ይህን መነሻ በማድረግ የማህበረሰብ ተጽኖ ተቋቁመው እንዴት ማለፍ እንደሚችሉ ምክሯን ትለግሳለች::

ውልደቷ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን መንዲዳ በምትባል ትንሽዬ ከተማ ነው:: ቤተሰቦቿ በስራ ምክንያት ወደ ጅማ ከተማ በመሄዳቸው፤ የሁለት ዓመት ልጅ እያለች ወደ ጅማ ከተማ መጥታ አደገች:: የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው እዛው ጅማ ከተማ ነው::

ጂቱ በትምህርቷ ቀለመቀንድ የምትባል አይነት ተማሪ ናት:: የወላጆቿም ድጋፍ ተጨምሮ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ስትከታተል ሁሉንም የክፍል ደረጃዎች ተሸላሚ ሆና አጠናቅቃለች:: የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤቷም ከትምህርት ቤቱ ሁለተኛው ከፍተኛ ውጤት ነበር::

ለሳይንስ ትምህርት ከፍተኛ ፍቅር እንደነበራት የምትገልጸው ጂቱ፤ “አሁን ለምማረው የትምህር ዘርፍ እና ለቴክኖሎጂ ያለኝ ፍቅር እየጨመረ የመጣው ከፍ እያልኩ ስመጣ ነው:: በፊት ‹አስትሮኖሚ› የሚባሉ ቃላቶችን ስለምሰማ ስለቴክኖሎጂ ለማወቅ ጉጉት ነበረኝ::” ስትል ትናገራለች::

ዝንባሌዋ ወደ ቴክኖሎጂ እንዲሆን የቻለበትን አጋጣሚ ስታስታውስ፤ እንዲህ ትላለች፤ “በአጋጣሚ አባቴ ‹አይ ቪ ኤም› የሚባል ኮምፒውተር ነበረው፤ የኮምፒተር እውቀት ባይኖረኝም ዝምብዬ እነካካው ነበር:: እያደኩ ስመጣ ቴሌቪዥን እና ስልክ ማየት ጀመርኩ::” ትላለች::

“በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ ሴት ስትሆኚ ማህበረሰቡ ይገድባል:: ፍላጎትሽን ለመምረጥ ይሞክራል፤ አትችይም፤ ይሄ ላንች አይሆንም የሚሉ ድምጾች ሲበዙ ወደዚህ ዘርፍ ለመግባት ይበልጥ ጓጓሁ:: ይቅርብሽ የሚሉ ሀሳቦች ሲበዙ፤ ይሄ ነገር ምን ቢሆን ነው? በሚል ይበልጥ እልህ ውስጥ ልገባ ቻልኩ::” ስትል ታስረዳለች::

አንድ ሰው በማህበረሰብ ውስጥ እስከ ኖረ አብሮ መብላቱ፣ አብሮ ማውራቱ አይቀርም:: ጂቱ ከሰዎች ጋር ቀርባ ስታወራ ምን መሆን እንደምትፈልግ ሲጠይቋት፤ ፍላጎቷ መሀንዲስ መሆን እንደሆነ በልበ ሙሉነት እና በየዋህነት ስትናገር፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የራሳቸውን ፍላጎት ለእሷ እንደሚሆን በማሰብ ይሄኛው አይሻልሽም ሲሏት ትበሳጭ እንደነበር ትናገራለች::

ሌላው ከዚህ በፊት በዚህ ዘርፍ ስኬት ላይ የደረሰ አራያ የሚሆን ሴት አለመኖሩን በመግለጽ፤ ከዚህ በፊት ያሳኩት ስለሌሉ እሷም እንደማይሳካላት ተስፋ አስቆራጭ አንደበታቸውን አዛኝ መስለው ይናገሯት እንደነበርም ታስታውሳለች:: እሱ ብቻ ሳይሆን “ትምህርቱ ረጅም ዓመት የሚወስድ ስለሆነ ሴት ስለሆንሽ እድሜሽ ይሄዳል:: ከዛ ስትወጪ ማን ያገባሻል” የሚሉ ስሜቷን የሚነኩ ንግግሮች እንደነበሩም ትናገራለች::

“ጥሩ ነገር አይደለም እያልኩ ባይሆንም፤ ሴት ስትሆኚ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚጠበቀው ቶሎ ወጥተሸ እንድታገቢ እና እንደወትወልጂ ነው:: ሁሉም ሰው በሚፈልገው ጉዳይ ሴቶችን ሊመራ ይፈልጋል:: “በማለት ትገልጻለች::

ዩኒቨርሲቲ እስከምትገባ ሶፍት ዌር መሀንዲስ ለመሆን ውስን እና የተደራጀ ህልም አልነበራትም:: ነገር ግን ህልምና ዝንባሌ ነበራት:: ህልሟ መሀንዲስ መሆን ሲሆን፤ ዝንባሌዋ ለኮምፒውተር ያላት ፍቅር ነው:: ሁለተኛ ደረጃ ስትደርስ ባደገችበት ከተማ እንደ አዲስ አበባ ብዙ ቴክኖሎጂን የተመለከቱ ዝግቶች እና ስልጠናዎች ባለመኖራቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ ጊቢ የገባቸው መሰረታዊ የኮምፒውተር እውቀቶችን ብቻ ይዛ ነበር::

“ወደ ምህንድስና ትምህርት መጀመሪያ ሲገባ የሚሰጥ “ኮርስ” አለ:: የዛኔ ነው ስለ ሶፍት ዌር በደንብ ማወቅ የቻልኩት:: ከተነሳ አይቀር ሌላው የተሳሳተ ግንዛቤ ደግሞ “ኮዲን” ቀድመሽ የማታውቂ ከሆነ ሶፍት ዌር መሀንዲስና ይከብድሻል፤ የሚገቡት ቀድመው ብዙ ያወቁ ሰዎች ናቸው የሚሉም አልታጡም::” ትላለች

“እውነታው ግን እንደዛ አይደለም፤ ወደ ትምህርት ዘርፉ ከተገባ በኋላ ሁሉንም ነገር ከአንድ ጀምሮ መማር ይቻላል:: እኔ ከሶፍት ዌር እና “ኮዲንግ” ጋር ተያይዞ እያንዳንዷን ነገር ያወኩት ወደ ትምህርቱ ከገባሁ በኋላ ነው:: የግድ ቀድሞ “ጂኔስ ” መሆን አይጠበቅም:: “ስትል ታብራራለች::

“ይህ ነገር የብዙ ሴቶችን ተነሳሽነት ሲገድል ስለምመለከት ነው:: አንድ ሰው ፍላጎቱ ካለው እና መማር እንደሚፈልግ ካወቀ በስድስት ወራት ውስጥ ሊረዳው የሚችለው ነው:: ” ትላለች::

ቴክኖሎጂ እንደየግለሰቡ አጠቃቀም ገዳይም፣ ትንሳኤም ነው:: ጂቱ የቴክኖሎጂን አቅም ለትንሳኤ አድርጋዋለች:: ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ስትማር የጥናት ፕሮግራሟ አሰልቺ እንዳይሆን እና ከመምህሮቿ ከምታገኘው እውቀት ውጭ የተለያዩ እውቀቶችን ፍለጋ እንድትሰበስብ የቴክኖሎጂ ሚና ከፍተኛ ነው::

“12ኛ ክፍል ስማር የንባብ ፕሮግራሜን የማስኬድበት የራሴ መንገድ አለኝ:: በአንድ ጊዜ ብዙ አላነብም:: የማስኬደው ቀስ እያልኩ ነው፤ መጻፍ ሳነብ ከሰለቸኝ፤ ዩቱብ ላይ የሚለቀቁ የፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ እና የሂሳብ ትምህርቶችን ለረጅም ሰዓት እከታተላለሁ:: ከዛን ቀድሞ የተሰሩ የፈተና ጥያቄዎችን እሰራለው::” ስትል ትናገራለች::

“እንዳይሰለቸኝ የማነበው እየቀያየርኩ ነው:: ምክንያቱም ማጥናት፤ አጥኚ እንደሚባለው ቀላል አይደለም:: እኔ 12 ክፍል በነበርኩበት ጊዜ ደግሞ በኮረና ምክንያት ትምህርት ተቋርጦ፤ ሞዴል ፈተናም አልወሰድንም ነበር:: ያመጣውት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤቴ 570 ነው:: በወቅቱ በትምህርት ቤታችን ሁለተኛው ከፍተኛ ውጤት ነው::” ትላለች::

ጂቱ ውጤት አምጥታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተመደበች በኋላ፤ ሴት በመሆኗ ከአካባቢው እርቃ መሄዷ ጥሩ ስለማይሆን እዛው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ብትማር መልካም እንደሚሆን አንዳንድ ሰዎች እናቷን ሲመክሯት ተደብቃ ትሰማ እንደነበር በማንሳት፤ ማህበረሰቡ ሴት ልጅ መሀንዲስ እሆናለሁ ከአካባቢዬ ርቄ መሄድ እችላለሁ ስትል ‹‹አትችይም›› ይላል:: ነገር ግን ወንድ ልጅ በሰማይ ላይ እራመዳለሁ ቢል የሚሰጠው ምላሽ አወንታዊ ነው:: ስትል ገልጻለች::

አንድ ተማሪ ተሳክቶለት ዩኒቨርሲቲ ሲገባ መጀመሪያ ከቤተሰቦቹ እና ካደገበት አካባቢ ተለይቶ የሚወጣበት እና አዲስ ጓደኛ አዲስ የኑሮ ዘይቤ የሚማርበት ነው:: ተብሎ ይታመናል:: ከነገሮች አዲስ መሆን ያለፈ ከቤተሰብ መራቅን ተከትሎ የተለያዩ ፈተናዎች የሚያጋጥሙበት ጊዜ ነው:: ይህ በወንድም በሴትም ላይ ያለ ነው:: ነገር ግን ይህ ፈተና ደግሞ ሴቶች ላይ ጠንከር የሚል መሆኑን መካድ አይቻልም::

አንዳንዶች ያጋጠማቸውን ተግዳሮት አሸንፈው እራሳቸውን በመገንባት ወደ አዲስ አስተሳሰብ እና የሕይወት ምዕራፍ ሲሻገሩ፤ ሌሎች ደግሞ ከቤታቸው ሲወጡ የነበራቸው ሰብእናም ጭምር ተጎድቶ ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ነጋሪ የማያስፈልገው እውነት ነው::

ጂቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ ያጋጠማት ፈተና ከጠበቀችው በላይ እና ከተለመደው የተለየ እንደነበር በመግለጽ፤ “ከታች ክፍሎች አንድ ችግር ካጋጠመ እሮጠን ቤታችን እንገባለን፣ እናታችን ጋር ገብተን ማልቀስ እንችላለን:: እቤት እያለው የማውቀው ጓደኞቼን እና ቤተሰቦቼን ነው:: ጊቢ ግን የምንኖረው ከተለያዩ አካባቢ ከመጡ ሰዎች ጋር ነው:: ” ትላለች::

“እናም ሳልወድ በግዴ የሰዎችን ባህሪ መልመድ አለብኝ:: እቤት ውስጥ እህት ወንድሞቼ እኔ በመሆኔ የሚችሉት ባህሪ ይኖራል:: ነገር ግን ዩኒቨርሲቲ ስገባ እንደዛ አይደለም፤ እንደፈለጉ መሆን አልችልም፡ መተው ያለብኝ ባህሪ ይኖራል:: ለኔ የሰዎችን ባህሪ መልመድ ትንሽ ከብዶኝ ነበር:: በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲ ሕይወትን ተምረን የምንወጣበት ተቋም ነው::” ስትል ታስረዳለች::

“አብዛኛው ሰው የሴት ልጅ ጥቃት ሲባል የሚያውቀው መደፈርን ብቻ ነው:: እንዲ ካላደረግሽ እንዲህ አደርግሻለው የሚል ዛቻ፤ መንገድ ላይ የሚላከፍ ሰው እና በጣም ብዙ ጥቃት አለ:: ለዚህ ደግሞ መክሰስ አይቻልም::” ትላለች ::

“እንደዚህ አይነት ነገር ቀላል አይደለም፤ በጣም ከባድ ነው:: የስነልቦና ጫናው ትምህርትም ላይ የሚፈጥረው ተፅኖ ከፍተኛ ነው:: ለምሳሌ አንድ ሰው ሴት ስለሆንኩ ተናግሮኝ ፊት ነስቼው፤ ቀጣይ ቀን ዝቶብኝ ክፍል ውስጥ ገብቼ ተረጋግቼ ልማር የምችለው እንዴት ነው? ለሕይወቴ መፍራት ይመጣል:: እናም ሊሰማ የሚችለው በገዛ ሕይወቴ ላይ ስልጣን እንደሌለኝ ነው:: ” ስትል ትናገራለች::

በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ እንደዚህ አይነት ነገሮች በመጀመሪያዎቹ ሶስትና አራት ዓመታት ተግዳሮት ሆነውባት እንደነበር በማስታወስ፤ እንደዚህ አይነት ነገር ዩኒቨርሲቲ ላይ የተለመደ ነው ትላለች:: አያይዛም በራስ አቅም ችግሩን ለመቅረፍ በመጣር ደህንነታቸው የተጠበቁ አካባቢዎች መምረጥ ይሻላል፤ እንጂ አንድ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ምንም ማድረግ እንደማይቻል ትመክራለች::

“መጀመሪያ ላይ ትምህርቱን ስንጀምር የነበረን ሴቶች ቁጥራችን ጥቂት ነበር:: ሁለተኛ፣ ሶስተኛ ዓመት እየሆንን ስንመጣ ቁጥራችን ጭራሽ እየመነመነ መጣ:: አራተኛ እና አምስተኛ ዓመት ስንደርስ ደግሞ ልጨርሺ ነው እንዴ፤ ለምን ንግድ ጀምረሽ አተይውም ይሉኝ ነበር:: ምናልባት ንግድ ህልሜ ቢሆን ጥሩ፤ ግን ሴት ስለሆንኩ አትችልም ብሎ ማሾፍ ፍታዊ ነው ብዬ አላምንም::” ስትል ትገልጻለች::

‹‹አሁን የመጨረሻ ፕሮጀክት እየሰራን ነው:: ለፕሮጀክቱ የመሰረት ነው ቡድን ውስጥ ብቸኛ ሴት እኔ ነኝ:: ብዙ ሴቶች በዘርፉ ከሌሉ እንዲአይነት ቡድኖች ውስጥ ብቸኛ ሴት የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው:: ›› ትላለች::

“ታዳጊ ሴቶች ሰው ህልማቸውን እንዲቀይር መፍቀድ የለባቸውም” የምትለው ተማሪ፤ አንድ ሰው ወዶም ይሁን ሳይወድ እሱ ይጠቅማል የሚለውን ነገር ለመናገር ይሞክራል:: ግን እንደዛ መሆን የለበትም ታዳጊ ሴቶች ማድረግ እንደሚችሉ እንዲያምኑ መፍቀድ ያስፈልጋል ትላለች::

“ጓደኛቸው ስላቆመች፣ ጓደኛቸው ስላልሆነች፣ እነሱ አይሆኑም ማለት አይደለም:: አርዓያ የሚሆን ሰው ባይኖራቸው እንኳን እራሳቸው ለታናናሾቻቸው አርዓያ መሆን እንደሚችሉ ማመን ትልቅ ነገር ነው::” ስትል ለታዳጊ ሴቶች መልክቷን ታስተላልፋለች::

የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ በሚያጠኑበት ወቅት አልገባኝም ብለው ለሌላ ግዜ ማስቀመጥ ሳይሆን፤ በወቅቱ ተረድተው ለማለፍ ቢሞክሩ መልካም ነው:: ምክንያቱም ግዜ ካለፈ በኋላ ተመልሶ ለማንበብ ሊያስጠላ እና የበለጠ ሊከብድ ይችላል:: ነገር ግን በወቅቱ ተረድተው ካለፉ በፈተና ወቅት የሚጠበቀው መከለስ ብቻ ነው :: ሌላው ከዩቱብ ቪዲዮች ጋር እያቀያየሩ ማንበብ እና ከጓደኞቻቸው ጋር መጠያየቅ የተሻለ ውጤታማ እንደሚያደርግ ትገልጻለች::

አመለወርቅ ከበደ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You