ዲሞክራቶች ትራምፕ ቆጠራው ሳይጠናቀቅ አሸንፌያለሁ ብለው ቢያውጁ የሚሰጡትን ምላሽ ማዘጋጀታቸውን ገለጹ

ዲሞክራቶች ትራምፕ ቆጠራው ሳይጠናቀቅ አሸንፌያለሁ ብለው ቢያውጁ የሚሰጡትን ምላሽ ማዘጋጀታቸውን ገለጹ።

ዲሞክራቶች ዶናልድ ትራምፕ የድምጽ ቆጠራው ሳይጠናቀቅ እንደ ምርጫ 2020 ማሸነፋቸውን ቢያውጁ፣ ቆጠራው እስከሚጠናቀቅ ትግስት እና መረጋጋት እንዲፈጠር ለማድረግ ማህበራዊ ሚዲያውን የሚያጥለቀልቅ ፈጣን ምላሽ ማዘጋጀታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የምርጫ ባለሙያዎች በተለይ ድጋሚ ቆጠራ ማድረግ አስፈላጊ የሚሆንበት አጋጣሚ ካለ አሸናፊውን ለመወሰን በርካታ ቀናት ሊፈጅ ይችላል ብለው ቢያስጠነቅቁም፣ ትራምፕ ግን ምርጫው በሚካሄድበት ቀን አሸናፊነታቸውን እንደሚያውጁ ተስፋ አላቸው።

የአሜሪካ ምርጫ ውጤት አሸናፊዎች በአብዛኛው ይፋ የሚሆኑት ከምርጫ ባለሥልጣናት የሚገኙ ውጤቶችን በሚተነትኑት ትልልቅ ሚዲያዎች ነው። እጩዎች ማሸነፋቸውን ይፋ የሚያደርጉት አልፎ አልፎ ነው።

“(ትራምፕ) የሚያደርገው ከሆነ እኛም ተዘጋጅተናል፤ ፕሬስን ለራሱ መጠቀሚያ ማድረጉን እና የአሜሪካን ሕዝብ ለመሸወድ የሚሞክር መሆኑን ካወቅን… ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል” ሲሉ ሀሪስ ባለፈው ረቡዕ እለት ከኤቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

ሀሪስ ስለዝግጅቱ በዝርዝር ባይናገሩም፣ ስድስት ዲሞክራቶች እና የሀሪስ የምርጫ ዘመቻ ባለሥልጣናት ትራምፕ ቀድሞው አሸንፌያለሁ የሚሉ ከሆነ የመጀመሪያው ውጊያ በሕዝብ ፊት ይሆናል ብለዋል።

አሸናፊነት ከመታወጁ በፊት ቆጠራው ይጠናቀቅ የሚሉ መልእክቶችን በማህበራዊ ሚዲያ እና በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለማጥለቅለቅ አቅደዋል።

“ትራምፕ በሀሰት አሸንፌያለሁ ብሎ እንዳወጀ ወዲያውኑ በቴሌቪዥን ለመቅረብ፣ እውነታውን ለማቅረብ እና ተጽዕኗቸውን ተጠቅመው ሁኔታው እንዲቀለበስ የሚያደርጉ ሰዎችን ለመድረስ ተዘጋጅተናል” ሲሉ የዲሞክራቲክ ናሽናል ኮሚቴ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

አንድ ከፍተኛ የሀሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ባለሥልጣን ባለፈው ዓርብ እንዳሉት ከሆነ ትራምፕ በሀሰት ማክሰኞ ምሽት አሸንፌያለሁ ብለው እንደሚያውጁ “በደንብ እጠብቃሉሁ” ብለዋል። “ከዚህ በፊት አድርጎታል፤ ከሽፏል። ድጋሚ የሚያደርገው ከሆነ በድጋሚ ይከሽፏል” ብለዋል ባለሥልጣኑ።

በ2020ው ምርጫ ትራምፕ ማሸነፋቸውን ያወጁት ምርጫ ከተጀመረ ከሰዓታት በኋላ ነበር። ነገር ግን በመጨረሻ በጆ ባይደን ተሸንፈዋል። ትራምፕ እስካሁን ድረስ የምርጫውን ውጤት ያልተቀበሉ ሲሆን የተሸነፉት መጠነሰፊ በሆነ ማጭበርበር ድምጽ ተሰርቀው እንደሆነ ያምናሉ።

ትራምፕ የምርጫውን ውጤት እንማይቀበሉ መግለጻቸው ተከትለው ደጋፊዎቻቸው በ2021 በካቲቶል ሁከት ማስነሳታቸው ይታወሳል።

ትራምፕ የምርጫውን ውጤት እንማይቀበሉ መግለጻቸው ተከትለው ደጋፊዎቻቸው በ2021 በካቲቶል ሁከት ማስነሳታቸው ይታወሳል

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You