የድምጽን ነገር (በተለይም ቅጥ ያጣ የተሽከርካሪ ክላክስ) እግረ መንገድ ብዙ ቀን አንስተን እናውቃለን። እስኪ ዛሬ የድምጽ ብክለትን ነገር ብቻውን እንየው፡፡
ስለሰለጠኑ ሀገራት ሳስብ፤ የረቀቀ ቴክኖሎጂ፣ ፈጣንና ምቹ መሰረተ ልማት ወይም ሌላ የሥልጣኔ መለያ የሆኑ ነገሮች ከሀገሬ ውጭ ለመኖር አጓጉተውኝ አያውቁም፡፡ የሰለጠኑ በሚባሉ ሀገራት የምቀናው በጤና የመኖር መብታቸውን ብቻ ነው፡፡ በጤና የመኖር መብት ላይ ያላቸው ጥበቃና ጥንቃቄ ያስቀናል፡፡
በሰለጠኑት ሀገራት የድምጽ ብክለት እጅግ ትልቅ ጉዳይ ነው፤ በእኛ ሀገር ግን የቅንጦት ነው፡፡ ምናልባትም ‹‹ምን ያህል ሥራ ፈት ቢሆን ነው!›› ሊያሰኝ ይችላል። የድምጽ እና የአየር ብክለት ግን እንደ ቀላል የሚታዩ አይደሉም፡፡ የአየር ብክለት ምንም እንኳን አሁንም ብዙ ቢቀረንም ቢያንስ አጀንዳ ስለሆነ እና በተደጋጋሚ ስለሚወራበት ማንም ያውቀዋል፡፡ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተጀመረው አዲስ አበባን የማስዋብ ፕሮጀክት እና የኮሪደር ልማት ይህን ችግር እየቀረፈ ነው። እጅግ ልብ ያልተባለውና የጆሮ ጠላት የሆነው የድምጽ ብክለት ግን አሁንም ልብ አልተባለም፡፡
የድምጽ ብክለት በሰለጠኑት ሀገራት ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ነው፡፡ እያንዳንዷ የምትወጣ ድምጽ መለኪያ አላት፤ ከዚያች ካለፈ ለቃቂው አካል ይጠየቃል፡፡
በኢትዮጵያ ግን ልብ በሉ! ከፊቱ ያለው ተሽከርካሪ መብራት ይዞት እያየ ከኋላ የመጣው ያለምንም ማቋረጥ ለረጅም ደቂቃ ያንባርቃል፡፡ መብራት ይዞት እያየ እንዴት ይሄዳል ብሎ ይሆን? ከፊቱ ያሉ ተሽከርካሪዎች የቆሙበትን ምክንያት እያወቀ አካባቢውን የሚያናውጥ ክላክስ ያስጮሃል፡፡
ይህን ነገር እንደደጋገምኩት ይገባኛል፡፡ ዳሩ ግን አደገኛ ችግር ስለሆነ ነው፤ የከተማዋን ገጽታ ስለሚያበላሽ ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የጤና ችግር ስለሚሆን ነው። የድምጽ ብክለት እንደ ሌላው የአካል ጉዳት በአንድ ጊዜ የሚታይ አይደለም፡፡ ልክ ስለት ነገር ሲቆርጠን ወይም ስንወድቅ ሰውነታችን እንደሚቆስለው አይደለም፤ ውስጥ ለውስጥ የሚጎዳ ነገር ነው፡፡ የድምጽ ብክለት ማለት ጆሯችን ሲቆስል የሚታይ አይደለም፤ ወደ ውስጥ ወደ ጭንቅላታችን የሚገባ ብክለት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሐሙስ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፤ ባለመኪና የሆነው ሕዝብ ከአንድ ሚሊዮን አይበልጥም፡፡ የተቀረው አምስትም ሆነ ስድስት ሚሊዮን የአዲስ አበባ ሕዝብ እግረኛ ነው፡፡ በዚያ ላይ መኪና ያለው ሁሉ መንደር ለመንደር ሁሉ በመኪና ይሄዳል ማለት አይደለም። በእግሩ ጉዞ(ዎክ) ማድረግ ይፈልጋል፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ ሕዝብ በድምጽ ብክለት እየተረበሸ ነው ማለት ነው።
ሌላው አደገኛ የድምጽ ብክለት ደግሞ የሙዚቃ ነገር ነው፡፡ መቼም ስለሙዚቃ ጥቅምና አስፈላጊነት ለማንም ማስረዳት አያስፈልግም፡፡ ያም ሆኖ ግን የሰውን ጆሮ ጤና የሚያበላሽ አለቃቀቅ አንድ ሊባል ይገባል፡፡ ምግብ ቤቶች ገና በማለዳ በሞንታርቦ የጆሮ ታምቡር የሚበጥስ ሙዚቃ ይከፍታሉ፡፡ ደንበኛው የሙዚቃውን ለዛ ከማዳመጥ ይልቅ የውስጡን ጤና ነው የሚያዳምጥ፡፡ ከአስተናጋጅ ጋር የሚወራው በከፍተኛ ጩኸት ነው፡፡ አብሮን ካለ ጓደኛ ጋር ስናወራ ቆይተን፤ ስንወጣ የጮህንበት ጉሮሯችን ሊዘጋ ሁሉ ይችላል፡፡ በማለዳ ምግብ ቤት ውስጥ ጆሮ የሚበጥስ ሙዚቃ መክፈት እስኪ ምንድነው አስፈላጊነቱ? የምር በዚያ ሙዚቃ የሚዝናና አለ? ቢኖር እንኳን ቢያንስ ለአብዛኛው ደህንነት ሲባል ገደብ ሊወጣ እና ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል፡፡
ሌላው የምታዘበው ደግሞ ተሽከርካሪዎች ውስጥ የሚከፈት ሬዲዮ ነው፡፡ አሁንም ስለሬዲዮ አስፈላጊነት ልናወራ አይገባም፤ ዳሩ ግን ጤናን የሚያውክ እና የሚወራውን መስማት እስከሚያስቸግር ድረስ የሚጮህ መሆን የለበትም፡፡
እዚህ ላይ ያለኝን ትዝብት እጥፍ ድርብ የሚያደርገው ደግሞ የመንግሥት ሰራተኞች ማመላለሸ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ የተማረ ነው። ቢያንስ ዲፕሎማ እና የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ነው። ለሀገር ዕድገትና ሥልጣኔ የሚሰራ ነው፤ ዳሩ ግን እንደዚያ ሲጮህ ምንም አይመስላቸውም፡፡
በተለይ ደግሞ የተቀረጸ (ፕሮዳክሽን) ሥራዎች (ማስታወቂያዎች እና የተለያዩ መልዕክቶች ማለት ነው) ሲሆኑ በጣም ነው የሚጮሁት፤ የቀጥታ ሥርጭት ዜናዎችና ፕሮግራሞች ይሻላሉ፡፡ ሬዲዮ እንደዚያ እየጮኸ፣ ሰዎች ደግሞ ለመሰማማት ሲሉ በጣም እየጮሁ ያወራሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሰርቪሱ በድምጽ ይናወጣል፡፡ አንዳንድ ደፈር ያሉ ሰዎች ‹‹ኧረ ቀንሰው!›› ሲሉትም አይሰማም፡፡ ሁሉም ተስማምቶ ግን ‹‹እየተጎዳን ነው ይቀነስ›› ቢባል አሽከርካሪውም ተጠያቂ ይሆን ነበር።
ችግሩ የአንድ አሽከርካሪ ወይም የአንድ ሬስቶራንት ብቻ አይደለም፤ እንደ አጠቃላይ ያለን ግንዛቤ ደካማ ስለሆነ ነው፡፡ የድምጽ ብክለትን እንደ ችግር ስለማናየው ነው፡፡ በየመንገዱ ዳር ያላስፈላጊ የሚለቀቁ ድምጾችን የሚቆጣጠር ስለሌለ ነው፡፡ ልብስ ቤቶች (ቡቲክ) ሁሉ ሳይቀር በሞንታርቦ ሙዚቃ ይለቀቃል፡፡ በተከታታይ ያሉ ቤቶች ሁሉም የየራሳቸውን ሙዚቃ ይለቃሉ፤ አላፊ አግዳሚው ግን የሚሰማው ጩኸቱን እንጂ አንዱንም ሙዚቃ የማጣጣም ዕድል አይኖረውም፤ ምክንያቱም አንዱ ሌላውን እየሸፈነ መረባበሽ ነው፡፡
በነገራችን ላይ በድምጽ ብክለት ላይ የተሰሩ ጥናቶችና መጣጥፎች እንደሚያሳዩት ፈልገን የማንሰማው ድምጽ ሁሉ ‹‹ምቾት የሌለው›› ተብሎ ነው የሚገለጽ፡፡ በሌላ በኩል የድምጽ መጠኑም መለኪያ አለው፡፡ የድምጽ መለኪያ ዴሲቤል ይባላል፤ ከ60 ዴሲቤል በላይ የሆነ ድምጽ ሁሉ ጎጂ ነው፡፡ በዚህ መለኪያ አዲስ አበባ ውስጥ በየመንገዱ የምንሰማውን ድምጽ አስቡት፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የድምጽ ብክለትን ማንም እንደ ችግርና እንደ ጎጂ አይቶት የሚያውቅ አይመስልም። ምንም እንኳን እንደ አጠቃላይ የጤና ደህንነት ላይ ያለን ግንዛቤ ደካማ ቢሆንም፣ ጆሯችንን ግን ትርፍ አካል ነው ያስመሰልነው፡፡ ጆሮ የድምጽ መቀበያ የሰውነት ክፍል ይሁን እንጂ ችግሩ ጆሮ ላይ ብቻ የሚቀር አይደለም፡፡ ከፍተኛ የሆነ የድምጽ ጫጫታና ጮኸት ሲበዛብን ራሳችንን(ጭንቅላት) የሚያመን ከጆሮ አልፎ ስለሚሄድ ነው፡፡ ስለዚህ የድምጽ ብክለት ከፍተኛ ችግር የሚያስከትል ነው፡፡
ከተማ ነውና የድምጽ ጫጫታ አይኑር ማለት አይቻልም፤ ዳሩ ግን ነባራዊ ሁኔታው ከሚፈጥረው ውጭ ያሉትን እና ሆን ተብሎ ያለአዋቂነት የሚለቀቁ ድምጾችን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ገና በማለዳ ምግብ ቤት ውስጥ በሞንታርቦ አካባቢውን ማናወጥ አስገዳጅ አይደለም፣ የትራፊክ መብራት የያዘው ተሽከርካሪ ላይ ያላቋረጠ ክላክስ ማድረግ የሚያስቀጣ መሆን አለበት፤ ተሽከርካሪ ውስጥ ሬዲዮ እስከ ላንቃው መልቀቅ መከልከል አለበት፤ ድምጹ ቀነስ ቢል ምን ችግር አለው?
በአጠቃላይ ጆሮ ከአምስቱ የስሜት ሕዋሳት አንዱ እንጂ ትርፍ የሰውነት ክፍል አይደለምና የድምጽ ብክለት ትኩረት ይሰጠው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም