ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 60 እና 70 ዓመታት በየቦታው ከየአቅጣጫው የሚታይ የትጥቅ ትግል ነበር፤ አሁንም አለ፡፡ ይህ ደግሞ በብዙ መንገድ ጉዳት አምጥቷል፡፡ ወንድም ወንድሙን ገድሏል። ንብረቱን አውድሟል፤ አቃጥሏል፤ ይህም ቂምና ቁርሾን አትርፏል።
ከመቀራረብ ይልቅ መገፋፋትን አስፋፍቷል። መጥፎ ትርክትን በትውልድ ላይ ዘርቷል። ይሄ አካሄድ ቀደም ሲልም ለሀገራችን አልጠቀመም አሁንም እየጠቀመ አይደለም። ስለዚህ አክሳሪውን ሳይሆን አዋጪውን የሰላም መንገድ መፈለግና መጠቀም ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆን አለበት።
የትጥቅ ትግል እጅግ አውዳሚ ነው። ጊዜ አባካኝ ፣ጉልበት እና ገንዘብ ጨራሸ ነው። የሰው ህይወትን የሚቀጥፍ እና ሕዝብን የሚያፈናቅል መሆኑን በዓይናችን አይተነዋል። ዛሬም እያየነው እንገኛለን። በመሆኑ በየትኛውም መልኩ ለየትኛውም ኃይል ምርጫው ሊሆን አይገባም። ምንም ዓይነት ዓላማን ለማሳካትም አዋጪ አይደለም።
በዓለም ላይ የሚከሰት ግጭትና ጦርነት መደምደሚያው ውይይት እና እርቅ ነው። በሀገራችንም የሚታየው ይሄው ልምምድ ነው። የሰው ህይወት ከጠፋ ንብረት ከወደመና ሕዝብ ከተፈናቀለ እንዲሁም የሀገር ኢኮኖሚ ከደቀቀ በኋላ ችግሮች በውይይት ይፈታሉ። ይሄን ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት በትግራይ ክልል ከሕወሓት ጋር በነበረው ግጭት አይተነዋል።
አለመግባባት ለምን ተፈጠረ ብሎ መጠየቅ አይቻልም፤ የሰው ልጅ የሰፋ ፍላጎት ባለበት ሁኔታና ቦታ ሁሉ” የተለየ ርዕዮተ ዓለም ለማራማድ፣ መብትና ነጻነትን ለማረጋገጥ፣ የግልና የቡድን ጥቅምን ለማስከበር፣ ያለውን ሥርዓት ለመቃወም …” በሚል የሚነሳ ግጭት ይኖራል። ይሄንን ፍላጎት ለማሳካት ደግሞ በቅድሚያ የሚታሰበው ጫካ መግባት ፣ መሸፈት እና የትጥቅ ትግል ማካሄድ ነው። ይሄ በተለያየ ጊዜ በሀገራችን ያየነው ነው። በዚህ መንገድ የተነሳ ግጭት ትርፉ አውዳሚነት ብቻ ነው። አሁንም በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውም ጥያቄን በትጥቅ ትግል ለማስመለስ መሞከር ከባለፈው ትምህርት ያልተወሰደበት እና አክሳሪ ነው። ይህም የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ እንጂ የሚያሸልም አይደለም።
ማንኛውንም ተቃውሞ በሰለጠነ መንገድ መግለጽ ይገባል። ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ከመሞት፣ ከመግደል በተቃራኒው ቆሞ በሰላማዊ መንገድ በመታገል ነው። እንዲመጣ የሚፈለገው መፍትሄ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ውጤቱ ግን የተሻለ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ከኃይል ይልቅ ሰላም በእጅጉ አዋጭ መንገድ ነው፡፡ በጦርነት የመጣ ሰላም ፣ የተገነባም ሀገር የለም። ስለዚህ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል።
የሰላም ዋጋው ውድ ጥቅሙም ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ፖለቲከኛውም ሆነ የትጥቅ ትግልን አማራጭ ያደረገ ወገን ለጥያቄው መልስ ማግኛው መንገድ የትጥቅ ትግል ሳይሆን ሰላማዊ መንገድ መሆኑን መረዳት አለበት።
መንግሥት ለሰላም እጁን ዘርግቶ በሩን ከፍቶ እየጠበቀ ይገኛል፤ ቀደም ሲልም ለሰላም ዝግጁ መሆኑን በተለያዩ መድረኮች አስታውቋል። “ተቀራርበን እንነጋገር ፣ እንወያይና ችግርን በጠረጴዛ ዙሪያ እንፍታ”ሲል ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን አቅርቧል። አሁንም የሰላም በሩ ክፍት መሆኑን በድጋሚ አብስሯል።
በመሆኑም በየትኛው አካባቢና ጦር ሰብቀው ጫካ ገብተው ያሉ ተፋላሚዎች ወደ ሰላም መድረኩ ብቅ ብለው ይህንን ሊያመልጥ የማይገባ ዕድል መጠቀም ይገባቸዋል። ማንኛውም ትግል ግቡ ሀገርና ሕዝብ መሆኑ ግልጽ ነው። ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስብ ተፋላሚ ደግሞ ሀገርና ሕዝብን ከሚጎዳ ፤ ዕድገትና ልማትን ከሚያደናቅፍ ተግባር መቆጠብ አለበት። የሰላምን አማራጭም ማስቀደም ይገባዋል።
የራስን ሀገር የራስን ሕዝብ ለማጥቃት ጦርነት መስበቅ አስፈላጊ አይደለም። እርስ በእርስ ለመጨራረስ፣ ሀብት ለማውደም መነሳትም የትም አያደርስም፤ አይጠቅምም። ለጥያቄ ሁሉ ጦር መስበቅ ጀግና አያደርግም። በዚህ ዘመን ጀግንነት ለሰላም ቅድሚያ መስጠትና ለዚሁ ዓላማ አበክሮ መስራት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ገና ለማደግ በሚውተረተር እና ወደ ኋላ ለቀረ፣ ሥራ አጥ ለበዛበት፣ ልማት ለጠማው ሕዝብና ሀገር የሚያስፈልገው ሰላምና ሰላም ብቻ ነው፡፡
በሰላማዊ ትግል ወደ ንግግር፣ ወደ ውይይት መምጣት ለራስም፤ ለሀገርም ሆነ ለሕዝብ ጠቃሚ ነው። የተሟላ ዕድገትና ልማትን ማረጋገጥና ብልጽግናን ማምጣት የሚቻለውም እጅ ለእጅ ተያይዞ ጸጋን ማልማትና ወደ ሀብት መቀየር ሲቻል ብቻ ነው። የሰላም ዋጋዋ ውድ ፍሬዋም ጣፋጭ ስለሆነም ነው ለሰላም ቅድሚያ እንስጥ ሰላምን እንሻ የሚባለው! ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም