ሀገር በሰው፤ ሰውም በሀገር የመኖርና የመጽናታቸው ምስጢር የገባቸው ጥቂት ሀገራትና መንግሥታት የሀገራዊ የልማት ሥራዎቻቸውን ሰውን ማዕከል አድርገው ይከውናሉ፡፡ ይሄ ያልገባቸው ደግሞ የልማት ሥራዎቻቸው ሁሉ ሰውን የገፉ፤ ሰውን ያላማከሉ፤ ውበትና ድምቀት እንጂ ሠብዓዊነትን ያልተላበሱ ይሆናሉ፡፡ እናም ሰው እና ልማት ማዶ ለማዶ ሆነው ልማቱ ሰውን ሳያውቅ፤ ሰውም ከልማቱ ሳይገናኝ ይኖራሉ፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ በሁለቱም መልክ ተገልጣለች፡፡ ለምሳሌ፣ ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ቀደም ብለው የነበሩ ሦስት አስርት ዓመታትን እና ከለውጡ ማግስት ያሉ ስድስት ዓመታትን ለማንጸሪያነት እናንሳ፡፡ ከለውጡ በፊት ያሉ ዓመታት፣ እንደ ሀገር ተከታታይ የሚባል ልማት እና የኢኮኖሚ እድገት (ያውም ባለ ሁለት አሃዝ እድገት የተባለለት ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት) አስመዝግባለች፡፡
ይሄ እድገት ግን አንድም የኅብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል፣ ሁለተኛም የዜጎችን የስራ ዕድል ፈጠራና ተጠቃሚነት እውን በማድረግ፤ ሦስተኛም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ በኩል ይሄ ነው የሚባል ረብ አልነበረውም፡፡ ምክንያቱም፣ ልማትና ሰው ሳይገናኙ፤ ልማቱ ሰው እንዳሳደደ፣ ሰውም ከልማቱ እንዲሸሽ እንደተደረገ የኖረበት ነበርና፡፡
ለዚህም ነው ሰው ልማትን መመልከት ሳይሆን፣ ከልማት የመጠቀም ከፍ ያለ መሻቱ፤ ፍትሃዊ እና የእኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ፍላጎቱ፤ የልማት ሥራዎቹ የዜጋውን ማኅበራዊ ስሪት፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ ሥነልቦናዊ ማንነትና ልዕልና በሚያጎናጽፈው መልኩ እንዲሆንለት ከፍ ያለ ህልምን በመሰነቅ ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ ከፍ ባለ ሕዝባዊ ተቃውሞ የለውጡ አንድ አቅምና ገፊ ምክንያት ሆኖ ለውጡን ያዋለደው፡፡
ከለውጥ በኋላ የተሠሩ ሥራዎች እና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ታዲያ፤ ይሄንን የለውጥ አዋላጅ የሆነ ሕዝብ ፍላጎት ማዕከል አድርገው እንዲከናወኑ ተደርገዋል፡፡ ለዚህም ነው ለውጡ ከፍ ያለ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሌሎችም የሪፎርም ርምጃዎችን በፍጥነትም፣ በድፍረትም በመውሰድ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ያደረገው፡፡
ለምሳሌ፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና በትግል ስልታቸው ምክንያት ከሀገር የተሰደዱ እና ወደ ሀገራቸውም እንዳይገቡ የተደረገ ኃይሎች ሀገራቸው እንዲገቡ መደረጉ አንዱ የሕዝብን ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ የተደረገበት የለውጡ ድፍረት የተሞላበት ርምጃ ነበር፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ አሳሪ እና ፈላጭ ቆራጭ የነበሩ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዘኑ የሕግ ማዕቀፎች እንዲሻሩ፣ እንዲሻሻሉና አዳዲስ ሕጎችም እንዲወጡ መደረጉ የዚሁ የሕዝብን ጥያቄ መልስ መስጫ ርምጃዎች ናቸው፡፡
የተቋማት ሪፎርም ሥራም፣ ሕዝብን ማገልገል የሚችሉ ነጻ እና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትን የመገንባት ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ተግባር ነበር፡፡ በዚህ ረገድ የተሠራው ሥራም በሕዝብ ዘንድ ከፍ ያለ አመኔታን በማትረፍ ሕዝብ የሚተማመንበትን ምርጫ ማካሄድ የቻለ የምርጫ ቦርድን መፍጠር፤ ሀገርን ከመፍረስ የታደገ ኅብረ-ብሔራዊ የመከላከያ ተቋምና ሠራዊትንም መገንባት ማስቻሉ አብነታዊ ማሳያው ነው፡፡
በልማት በኩልም፣ ኢትዮጵያን ከለማኝነት ያላቀቀ፣ ከሸማችነት ያወጣ እና ወደ ሁሉን አቀፍ አምራችነት ያሸጋገረ ተግባር ተሠርቷል፡፡ ኢትዮጵያ ታምርት ተብሎ፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲያመርቱ ሆኗል፡፡ በምግብ ራስን እንቻል በሚልም ግብርናው ትርፍ አምራችነትን አጎናጽፏል፡፡ ለምሳሌ፣ ስንዴት ከመሸመት እና ከመለመን ወጥነት፣ ስንዴን ወደ መሸጥና ለርዳታ ወደመላክ ተሸጋግረናል፡፡ በሌማት ትሩፋትና በአረንጓዴ ዐሻራው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትም ሕዝብ ምን ያህል የለውጡ ተግባራት እሱን የመሰሉና ያቀፉ መሆናቸውን በተግባር የገለጡ ናቸው፡፡
በመሠረተ ልማት፣ በማኅበራዊ ልማትና ሌሎችም መስኮች የተከናወኑት የዚሁ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው፣ ከለውጡ ማግስት ከ170 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በጋ ከክረምት የሚያስጉዝ የጠጠር መንገድ፤ እንዲሁም ከ26 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የአስፓልት መንገድ ሥራ መከናወን የተቻለው፡፡ የጤና እና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ መሠረተ ልማቶች በብዛትም በጥራትም እንዲከወኑ መደረጉም የእነዚህ ልማቶች ትኩረታቸው ሰውን፣ ግባቸውም ሠብዓዊ ልማትን ማምጣት ስለመሆኑ አብነቶች ናቸው፡፡
በዚህ ረገድ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናወኑ ያሉ፤ ልማትንም ሠብዓዊነትንና ሰውንም ማዕከል ያደረጉ ከገበታ ለሸገር እስከ ገበታ ለትውልድ የዘለቁ፤ አሁን ደግሞ መነሻውን አዲስ አበባ አድርጎ እስከ ገጠር ቀበሌዎች የዘለቀው የኮሪደር ልማት ሥራ፤ መንግሥት እንደ መንግሥት እየሠራቸው ያሉ ተግባራት ሰው ተኮር ስለመሆናቸው ዐቢይ ምስክሮች ናቸው፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች (ለምሳሌ፣ የኮሪደር ልማቱ)፤ የአካባቢን መልክና ገጽታ ከመቀየር ባሻገር፤ ዜጎች ምቹ፣ ጤናማና ንጹህ ስፍራ የመኖር መብታቸውን እንዲጎናጸፉ የሚያደርግ ነው፡፡ ምክንያቱም የኮሪደር ልማቱ፣ የተጎሳቆሉ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩና ከፍ ላለ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የደህንነት ችግር ውስጥ የኖሩ ወገኖች የተሻለ ኑሮ ወደሚያገኙበት ከባቢ እንዲሸጋገሩ ያደረገ ነው፡፡
ከዚህ ባሻገርም፣ ዜጎች የሚዝናናኑባቸው፣ በጋራ ቁጭ ብለው የሚመክሩባቸው፣ አብረው የሚራመዱባቸው፣ አረፍ ብለው ሻይ ቡና እያሉ ድካማቸውን የሚወጡባቸው ንጹህና አረንጓዴ ሥፍራዎች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የሞተር አልባ ተሽከርካሪ መንገዶች በልካቸው የተሰናሰሉበት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ፋይዳ አላቸው ተብለው የሚከናወኑ ማንኛውም የልማት ተግባር ከስም የተሻገረ በተግባር የታጀበ፤ ልማት ከሰው የተነጠለ ሕልውና እንደሌለውም እንዲናገሩ ተደርገው እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር እንደመሆናቸው፤ እነዚህን ተግባራት በሁሉም ቦታ ላቅ አድርጎ ማስቀጠል የተገባ ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም