ሩሲያ ዩክሬንን ድል እስከምታደርግበት ቀን ድረስ ድጋፏን እንደምትቀጥል ሰሜን ኮሪያ አስታወቀች

ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ ከዩክሬኑን ጋር የጀመረችውን ጦርነት እስከምታሸንፍ ድረስ እንደምትደግፋት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ገለጹ፡፡ የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾ ሰን ሁይ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በሞስኮ ትናንት ውይይት አድርገዋል።

የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾ ሰን ሁይ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፣ ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደች ያለውን ጦርነት እስከምታሸንፍ ድረስ እንደምትደግፋት መግለጻቸው ተነግሯል፡፡

“ታሪካዊው እና ባህላዊው ግንኙነታችን ወደማይገበር ወታደራዊ ጓድነት አድጓል” ያሉት ቾይ፣ በፑቲን “ብልህ አመራር” የሩሲያ ጦርና ሕዝብ “የሉዓላዊነት ዘመቻቸውንና የሀገሪቱን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ቅዱስ ትግል ድል ያደርጋሉ።” በማለት “እኛም ድሉ እውን እስከሚሆንበት ቀን ድረስ ከሩሲያ ጓዶቻችን ጎን እንደምንቆም እናረጋግጣለን” ብለዋል።

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ባለፈው ሰኔ ወር በፒዮንግያንግ የፈረሙትን ወታደራዊ ስምምነት የበለጠ ማጠናከር እንዳለባቸው መግለጻቸውንም ተነግሯል፡፡

የሩሲያው አቻቸው ላቭሮቭ በበኩላቸው፣ ምዕራባውን ኔቶን ወደ ምስራቅ ማስፋፋታቸውን እና ዘረኛው ሥርዓት የሩሲያ የሆነን ሁሉ እንዲያጠፋ ማበረታታቸውን ተከትሎ የኮሪያ ወዳጆቻችን ለወሰዱት በመርህ ላይ የተመሠረተ አቋም ምስጋና እናቀርባለን ሲሉ መናገራቸው ተገልጿል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ጦር መካከል ቅርብ ግንኙነት መኖሩንና ይህም ወሳኝ የደህንነት ሥራዎችን ለመከወን እንደሚያስችላቸው ላቭሮቭ ገልጸዋል፡፡

ላቭሮቭም ሆኑ ቾይ፣ አሜሪካ፣ ኔቶ እና ደቡብ ኮሪያ፣ በዚህ ሳምንት ሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያ 10ሺ ወታደሮችን ልካለች በማለት ያወጡትን መግለጫ አልጠቀሱም። የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ለእንደነዚህ አይነት መግለጫዎች” ከዚህ በፊት ከተባለው በላይ የሚጨመር የለም” ብለዋል።

ሆኖም ግን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከእነዚህ ውስጥ 8ሺ የሚሆኑት ወታደሮች የዩክሬን ወታደሮች ባለፈው ነሐሴ ወር የሩሲያን ድንበር ጥሰው ወደገቡበት ኩርስክ ግዛት መድረሳቸውን ገልጸዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You