በብዙ አማራጭ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ

ብሪክስ እንደ ቻይና፣ ሕንድና ሩሲያ ያሉ ታላላቅ የዓለም ኃያላን ሃገራትን አቅፏል። በአሕጉራቸው ላይ ተፅዕኖ ያላቸውን እንደ ደቡብ አፍሪካ እና ብራዚል ያሉ ሃገራትም አሉ። ቡድኑ ወደ 3ነጥብ5 ቢሊዮን ሕዝብን ይወክላል። ይህም 45 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ ይሸፍናል እንደማለት ነው።

የአባላቱ ድምር ምጣኔ ሀብት ከ28ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ አለው። ይህም ከዓለም ኢኮኖሚ 28 በመቶውን ማለት ነው። ቡድኑ ከፍተኛ የሚባል አቅም እንዳለው የሚያስመሰክሩ ማሳያዎች አሉ። ለአብነትም የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ከዓለም ጠቅላላ ምርት ድርሻቸው 30 ነጥብ አምስት በመቶ መሆኑ ማንሳት ይቻላል። ኢራን፣ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስን በአባልነት የሚያካትተው የብሪክስ ሃገራት ቡድን 44 በመቶ የሚሆነውን ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ያመርታሉ።

ቡድኑ አባላት የምዕራባውያን እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ያሉ እንዲሁም ለመንግሥታት ብድር የሚሰጡ ጠቃሚ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ባልተገባ መልኩ በቁጥጥራቸው ስር ስለማድረጋቸው በመጠቆም፣ ይህ ፈፅሞ ሊስተካከል እንደሚገባው አበክረው ይከራከራሉ።

ከዚህ አንጻር በመልማት ላይ ያሉ ሃገራት “የበለጠ ድምፅ እና ውክልና” እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። እአአ በ2014 የብሪክስ ሀገራት መሠረተ ልማትን ለማሳደግ የሚያግዝ ገንዘብ የሚያቀርብ አዲስ ልማት ባንክ አቋቁመዋል። እአአ በ2022 መገባደጃ ላይ ለአዳዲስ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ የባቡር መስመሮች እና የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች 32 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለሃገራት አቅርቧል።

ሌላው ጉዳይ አባል ሀገራቱ ዓለም በዶላር ከመገበያየት በመውጣት ሌሎች አማራጮች መስፋት አለባቸው ብለው የሚያስቡ በመሆናቸው፣ የምዕራቡ ዓለም ብቻ የሚመራው የዓለም ሥርዓት ብቻ እንዲኖር አይፈልጉም ይህ የተረጋጋና እኩልነት የሰፈነበት የዓለም ሥርዓት እንዲፈጠር ዕድል ይሰጣል።

ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ትልቅ የገበያ ሥርዓት ውስጥ የመግባትን ዕድል ይሰጣታል የሚል እምነት አለኝ፤ በምዕራቡ ዓለም ብቻ ተወስኖ ያለው የፖለቲካል የኢኮኖሚ ሥርዓት ሌላ አማራጭ እንዲያገኝ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ የኅብረቱ ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያ፤ በመርሕ ደረጃ ከሁሉም ጋር በሠላም የመኖር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስትከተል የኖረች ሀገር ናት። በዚህም እንደ ሀገር ወደዚህ ኅብረት መግባቱ የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ አማራጭ እንደሚያሰፋ ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው።

የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችላል። የኅብረቱ መሥራች ሀገራት በተለይ ቻይናና ሩሲያ የኢትዮጵያ ጠንካራ አጋርና ወዳጆች ሆነው መቆየታቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ በተለይ ከፖለቲካዊ ድጋፋቸው ባሻገር ኢትዮጵያ በተለይ በኢኮኖሚውም ይበልጥ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ዕድል ያሰፋል።

ኢትዮጵያ እያደገች ያለች ሀገር እንደመሆኗ ወደዚህ ጥምረት መግባቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የመደራደር አቅም ከፍ ያደርግላታል:: ከፖለቲካ እና ኢኮኖሚ አንፃርም ፋይዳው የጎላ ነው፤ ሀገሪቱ ወደ ውጭ ለምትልካቸው ምርቶች ተጨማሪ የገበያ አማራጭ ያስፈልጋታል:: በእነዚህ እና ሌሎች መሰል ምክንያቶች የጥምረቱ አባል መሆን ጠቀሜታው እንደ ሀገር ከፍተኛ ነው።

ኢትዮጵያ ዓባይን በማጠናቀቅ የኃይል ልማት የአቅርቦት መጠን በእጥፍ በማሳደግና ሠላሟ ተረጋግጦ ኢንቨስትመንት መሳብ ከቻለች በኅብረቱ በመቀላቀሏ በብዙ ተጠቃሚ እንደምትሆን አያጠራጥርም፤ በኅብረቱ የሚኖራት ተሳትፎ የቻይና፣ የሩሲያና የሕንድ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ኢንቨስት ማድረግ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምንጭን ያጠናክራል። በዚህም የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል።

የኢትዮጵያ 120 ሚሊዮን ሕዝብ፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ መሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ የቀይ ባሕር ጂኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥና በቀጣናው ያላት ተፅዕኖ ፈጣሪ ናት። ይህ በዚህ ኅብረት ለመቀላቀሏ ምክንያት ነው። ይህንን መልካም አጋጣሚ ደግሞ ለሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም መጠቀም ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ያለችበት የጂኦፖለቲካ ሁኔታ በጣም ወሳኝ ነው። አየር መንገድን የመሰሉ ግዙፍ ተቋማት አሏት:: የቴሌኮም ሴክተሩ ሊብራላይዝድ መሆን የሚያመጣቸው ዕድሎች ይኖራሉ:: ኢንቨስትመንቶቻቸውን ወደ ኢትዮጵያም የሚልኩ ሀገራት ደግሞ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት ይኖራል።

የህዳሴ ግድብ አሁን ያለውን የኃይል መጠን ከእጥፍ በላይ የሚያመነጭ ስለሆነ ከውጭ የሚመጡ ኢንቨስተሮች ይህን የኃይል አማራጭ ተጠቅመው ምርቶቻቸውን አምርተው ኤክስፖርት አድርገው እራሳቸውንም ኢትዮጵያን መጥቀም የሚችሉባቸው መንገዶች ይስፋፋሉ::

በዓለም ፖለቲካ ሁልጊዜ የኢኮኖሚ የበላይነት እጅጉን ወሳኝ ነው። የፖለቲካ የበላይነትን የሚያመጣው ይህ የኢኮኖሚ የበላይነት ነው። የጥምረቱ አባል መሆኑም ኢኮኖሚን ከማጎልበት ባሻገር በአንዳንድ አገራት ተፅዕኖ ስለዚህ እየተዛወረ ያለውን የዓለም ፖለቲካ የሚገዳደር አቅም ለመፍጠር ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።

የ‹‹ብሪክስ›› አባል ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚያቸውን እያሳደጉ ስለሆነ የዓለም ፖለቲካ የኃይል ሚዛኑን በመቀየር ደረጃ ትልቅ አስተዋፅዖ አላቸው። ‹እሺ› ብሎ ከመቀበል በዘለለ በብዙ ጉዳዮች በልዩነት ለመቆም የአንድ ወገን የበላይነትን በመገዳደር ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው። በአሁን ወቅት የዓለም ፖለቲካ እና አሰላለፉ እየተቀያየረ እየሄደ ነው:: በተፈጥሮውም ተቀያያሪ ነው:: በአንድ ቦታ የሚቆም አይደለም፤ ተለዋዋጭ ነው:: በዚህ ተለዋዋጭ የዓለም ፖለቲካ ኢትዮጵያ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የምትችልበትን አማራጭ ሁሉ መጠቀም አለባት፤ ከአንድ ወገን ጋር ብቻ ኅብረት በማድረግ የሚፈለጉ ብሔራዊ ጥቅሞች ማሳካት የሚቻል አይደለም::

ይህ እንደመሆኑም በዓለም ደረጃ ካሉ ጥምረቶች ጋር አጋርነት በመፍጠር እንደ ሀገር ማግኘት ያለባትን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም ሁሉ ማግኘት ከተፈለገ እንደ ‹‹ብሪክስ›› ካለ ጥምረት ጋር ኅብረት በመፍጠር በብዙ አማራጭ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ እንዲያስችላት ኅብረቱን መቀላቀሏ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

ወልደመስቀል

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You