ለከተማዋ አዲስ ገፅታን ያላበሰው የቦሌ መገናኛ የኮሪደር ልማት

በመዲናዋ አዲስ አበባ በመጀመሪያው ዙር ከተጀመሩት የኮሪደር ልማት ግንባታዎች አንዱ የቦሌ ድልድይ መገናኛ ኮሪደር ልማት አንዱ ነው። በመዲናዋ ሰፊው ጎዳና ላይ የተካሄደው ይህ ግንባታ፣ ለትራፊክ ፍሰት ምቹ በሆነ መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መሆን ጀምሯል።

ይህ መንገድ እስከ ግንባታቸው ተካሂዶ ለአገልግሎት ክፍት ከተደረጉት የኮሪደር ልማቱ ግንባታዎች በአይነቱ ይለያል፤ በመስመሩ በሁለት ቦታዎች ላይ የመሬት ውስጥ የእግረኞች መተላለፊያ ተካቶበታል። መሥመሩ ቀለበት መንገድ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ከሶስት በላይ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የሚያሳልፍ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚታይበት ጎዳና ነበር።

ለእግረኞች ምቹ ተደርጎ ያልተገነባና በመንገዱ መሀል የተገነቡ አጥሮችን ዘለው የሚሻገሩ እግረኞች ለአደጋ የሚጋለጡበት ሁኔታም በስፋት ይታይ ነበር። በመንገዱ ለእግረኞችም ሆነ ለተሽከርካሪዎች ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎች ሲስተዋሉበት ቆይቷል። መሥመሩ በቂ የእግረኛ መሄጃ መንገድ እና መሻገሪያ አልነበረውም።

አሁን ግን በኮሪደር ልማቱ በተከናወነለት ልዩ ልዩ ግንባታ በከተማዋ ደረጃ ትልቁ ሰፊ ጎዳና መሆን ችሏል። ተሽከርካሪዎች እንደፈለጉ የሚፈሱበት ሲሆን፤ በአንድ አቅጣጫ ብቻ በአንድ ጊዜ አምስት ያህል ተሽከርካሪዎችን ለማንቀሳቀስ ተደርጓል።

በዚህ የኮሪደር ልማት በልዩ ሁኔታ በኢትዮ ቴሌኮም አማካይነት ከውጭ የመጡ ልዩ አገልግሎት ያላቸው ስማርት የመንገድ ዳር መብራቶችም ተገጥመውለታል። ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለትራፊክ ክፍት ከተደረጉት የኮሪደር መሥመሮች በተለየ መልኩ የተገጠሙለት ደረጃቸውን የጠበቁ ስማርት የመንገድ መብራት ምሰሶዎችና የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ የተገጠመላቸው ናቸው። በመንገዱ ግራና ቀኝ ለረጅም ዓመታት የሚያገለግሉ በኮንክሪት የተሞሉ የእግረኛ መሄጃ መንገዶችም ተሰርተዋል። በእግረኛ መሄጃው መሀል አይነስውራንን ታሳቢ ያደረጉ የእግር መንገዶችም በተመሣሣይ በኮንክሪት የተሰራ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የስራና ክህሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ይህን የቦሌ መገናኛ መስመር የኮሪደር ልማትን ሰሞኑን ለጋዜጠኞች ባስጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማት ግንባታ ከተካሄደባቸው የመጀመሪያው ዙር ኮሪደሮች አንዱ የቦሌ-መገናኛ መስመር ነው።

ይኸው የኮሪደር ልማት ሲካሄድ ማዕከል የተደረገው መሃል ከተማ ያለውን ወደ መገናኛ እንዲሁም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚመጡ እንግዶች መግቢያ መሆኑ ነው። ይህን የሚመጥን ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ ልማት ተከናውኖበታል። መንገዱ አራት ነጥብ ሶስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን በቀለበት መንገድነት ሲያገልግል የቆየ ሲሆን፣ እግረኞች በቀላሉ መሻገር የማይችሉበት፤ ተሽከርካሪዎች በፍጥነት የማይሄዱበት፣ ብዙም ያልለማና የንግድ ተቋማት የማይታይበትና ምቹም ያልነበረ ነው። በመንገዶች የቦታ አጠቃቀም ላይ ይታይ የነበረን ዲዛይን በማሻሻል ምቹ የትራንስፖርት አሰራር የተተገበረበት መሆኑንም ጠቅሰዋል። የዚህ መንገድ አጠቃላይ ፕሮጀክት ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን አመልክተው፣ መንገዱ ለትራፊክ ክፍት መደረጉን ገልጸዋል።

ዋና ስራ አስኪያጁ እንዳብራሩት፤ ከመገናኛ ቦሌ የኮሪደር ልማትን ከሌሎቹ የኮሪደር ልማት ስራዎች በልዩ ሁኔታ የተገነባ ነው፤ መንገዱ ሙሉ ለሙሉ ፈርሶ ስማርት ሆኖ በአዲስ መልክ ተሰርቷል። 68 ሜትር ስፋት ያለው እና አራት ነጥብ ሶስት ኪሎ ሜትር የሚረዝመው መንገዱ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲያስችል ተደርጎ የነገውን ትውልድ ታሳቢ ባደረገና ይበልጥ ስማርት ሆኖ የተሰራ ነው። በግራ እና በቀኝ በአንድ ጊዜ አምስት አምስት መኪኖችን የሚያስተናግድ በከተማዋ ትልቁ ጎዳና ሆኖ ተገንብቷል።

የአስፓልት ስራውን በተመለከተ እንዳስረዱት፤ አራት ዙር ያለው በተደጋጋሚ አስፓልቱን በመደረብ የተገነባ ሲሆን፣ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት መስጠት በሚያስችል መልኩ የተሰራ ነው። በአሁኑ ወቅትም የአስፓልት ስራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ለትራፍክ ከፍት ሆኖ ይገኛል። የእግረኛ መንገዱ በግራና በቀኝ አምስት አምስት ሜትር ስፋት ያለውና በኮንክሪት የተገነባ ነው። ይህም መንገድ ጥራቱን የጠበቀ እና ለረጅም ዓመታት ሊያገለግል እንዲችል ተደርጎ ተገንብቷል። በሌሎች የኮሪደር ልማት ስራዎች ጥቅም ላይ የዋለውን የታይልስ ንጣፍ የእግረኛ መንገድ ስራ በዚህኛው ላይ በማሻሻል ደረጃውን በጠበቀና የከተማዋንና የሀገሪቱን የወደፊት ደረጃ ከፍ የሚያደርግ መሆኑንም አብራርተዋል።

ሶስት ሜትር ስፋት ያላቸው የብስክሌት መሄጃ መንገዶች በመንገዱ በስተግራና በስተቀኝ ተገንብቶለታል። በዚህ ኮሪደር እንደ ችግር ይነሳ የነበረው አንዱ የእግረኛ ማቋረጫዎች ችግር የነበረ ሲሆን፣ እግረኞች በቀላሉ የሚያቋርጡበት ሁኔታ አልነበረም። በተለይ ቦራ በሚባለው አካባቢ ሰፊ የእግረኞች መሻገሪያ የነበረ ቢሆንም፣ ትልቅ የትራፊክ መጨናነቅ ሲፈጥርበት ቆይቷል።

በዚህ የተነሳ እግረኞች ሲሻገሩም ለአደጋ የሚጋለጡበት ሁኔታ ብዙ ነበር። መገናኛ አካባቢ ባለው ድልድይ ስርም እንዲሁ እግረኞች በጣም ተቸግረው የሚሻገሩበት፣ ተሽከርከሪዎች ለማቋረጥ የሚቸገሩበት፣ ሰውና ተሽከርካሪ እየተገፋፉ የሚተላለፉበት ነበር። የኮሪደሩ ልማቱ እነዚህን ችግሮች በመሰረታዊነት መቅረፍ ችሏል። ሁለቱም ቦታዎች ከስር የእግረኛ መተላለፊያ እንዲኖራቸው ተደርጓል። የአንዱ ግንባታም በአብዛኛው ተጠናቅቆ ለእግረኞች ክፍት ተደርጓል።

የመሬት ውስጥ የእግረኛ መሻገሪያ ስራዎች የመጀመሪያው ከስር መተላለፊያ ቦራ አካባቢ ሲሆን፣ መተላለፊያውም 58 ሜትር ይረዝማል። 10 ሜትር ስፋት ያለው ይህ የእግረኛ ማቋረጫ የመሬት ውስጥ መተላለፊያ የሲቪል ስራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ መንገዱ ክፍት ተደርጓል። ኤሌክትሮኒክስ የመግጠም ስራዎችም እየተሰሩ ይገኛል።

ሁለተኛው የመሬት ውስጥ እግረኞች መተላለፊያ ግንባታም መገናኛ ላይ የሚሰራው ነው፤ ይህም ሁለቱንም እኩል የሚቆርጥና የሚኖረውን የትራፊክ መጨናነቅ ታሳቢ በማድረግ የሚሰራ ይሆናል። ሌሎች ስራዎች እስኪሰሩ ድረስ ግንባታው የቆየ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ወደ ግንባታ መገባቱን ተናግረዋል።ይህ የመገናኛው የመሬት ውስጥ የእግረኞች መተላለፊያ ግንባታም በ45 ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅና ለእግረኞች ክፍት እንደሚደረግም አስታውቀዋል። ግንባታው 24 ሰዓት ቀንና ሌሊት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

እሳቸው እንደተናገሩት፤ በዚህ ኮሪደር ላይ የተሰራው ሌላው የእግረኛ መሻገሪያ 24 ድልድይ የሚባለው ነው። ቀደም ብሎ 24 ድልድይ ተገንብቶ የነበረ በመሆኑ ከቦሌ ወይም ከመገናኛ አቅጣጫ የሚመጡና በዚህ የእግረኛ መንገድ የሚሻገሩ ሰዎች ወደ መንገድ ወጥተው እንዲሄዱ የሚደረግበት ሁኔታ ነበር። በሁለቱም የድልድዩ አቅጣጫዎች ድልድዩን በመክፈት የእግረኛ ማቋረጫው በድልድዮቹ ስር እንዲገነባ ተደርጓል። ይህም እግረኞች በቀላሉ መሻገር እንዲችሉ አስችሏል፤ ወደ መኪና መንገድ ሳይወጡ እንቅስቃሴያቸውን በነጻነት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህ ግንባታ የሳይክል መንገዱንም የእግረኞቹንም ያካተተ ነው።

አቶ ጥራቱ እንዳስታወቁት፤ የቦሌ መገናኛ የኮሪደር ልማት የተገጠሙት የስማርት መብራቶች በሌሎች ሀገራትም የመጨረሻ የሚባል የቴክኖሎጂ ደረጃ ያላቸው ናቸው። የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ በዚህ ኮሪደር ላይ በተለይ መንገድ እንዲካተት ተደርጓል። ከመንገዱ ውጪ በሆኑ መሰረተ ልማት በሁለት ቦታዎች ላይ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ እየተሰራ ነው። ይህም በርከት ያሉ ተሽከርካሪዎች በአንድ ጊዜ ቆመው ቻርጅ ማድረግ የሚያስችላቸው ነው።

አንደኛው ቻርጅ ማድረጊያ አዲሱ ስታዲየም ፊትለፊት ያለው ሲሆን ሁለተኛውም አንበሳ ጋራዥ ፊትለፊት የሚሰራ ነው። እነዚህ ግንባታዎች ሲጠናቀቁም በአንድ ጊዜ በርከት ያሉ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው። በኤሌክትሪክ ምሰሶ ላይ ያሉ ቻርጅ ማድረጊያዎች አሁን ላይ ለአገልግሎት ክፍት አልሆኑም ሲሉ ጠቅሰው፣ ተጨማሪ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል። መንገዱ ላይ ቻርጅ የሚያደርጉ መኪኖች ቢቆሙ በርከት ያለ መኪና ቢቆም የሚኖረውን የትራፊክ መጨናነቅ ከግምት በማስገባት የትኞቹ ቦታዎች ላይ በየትኛው ሰዓት ላይ አገልግሎቱ ቢሰጥ የተሻለ እንደሚሆን ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠውቀሰው፤ አብዛኛዎቹ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ይሄንን ቴክኖሎጂ እንዲያካትቱ የተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኤሌክትሪክ ምሰሶዎቹ ላይ የካሜራ፣ የመልዕክት ማስተላለፊያ ስክሪን ተካቶባቸዋል። አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ መቀበል የሚችሉ ሆነው የተሰሩ ናቸው። ወደ ፊት ሌላ የተሻለ የቴክኖሎጂ አማራጮች ቢመጡም ሌላ ተጨማሪ መሰረተ ልማት መገንባት ሳያስፈልግ ቴክኖሎጂዎቹን በእነዚህ ስማርት ምሰሶዎች ላይ ማከል ይቻላል። እነዚህን በአንድ ማዕከል መቆጣጠር የሚቻል ነው፤ በሚፈለግበት ጊዜ የሚፈለገውን መልዕክት ማስተላለፍ የሚቻልባቸውም ናቸው። የመብራቶቹን የብርሃን ቀለማትም መቀያየር ይቻላል። በዚህ ኮሪደር በቀላሉ መቆጣጠር የሚያስችል ዘመናዊ ስራ ተሰርቷል።

አቶ ጥራቱ ይህ ኮሪደር ሀገሪቱ በአረንጓዴ ውበት ስራዎች የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ በሚያሳይ መልኩ መገንባቱንም አስታውቀዋል። መንገዱ ወደ ጫካ ፕሮጀክት የሚወስድና ከአየር መንገድ ተነስቶ ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች የሚቀበል ጎዳና መሆኑን ጠቅሰው፣ የሀገራችንን ገፅታ በሚያሳይ መልኩ ውብ ተደርጎ ተገንብቷል ብለዋል።

የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎች፤ እግረኞች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ በቀላሉ የሚገዟቸው አቅርቦቶችን ማቅረብ የሚያስችሉ ትናንሽ ሱቆች ተገንብተውለታል። ሁሉም የኮሪደር ልማት ስራዎቹ የከተማዋን ነዋሪ የፍላጎት ደረጃ ሊመጥን በሚችል መልኩ ተከናውኗል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በአጠቃላይ የከተማዋ አዲስ ገፅታ እየተላበሰች ነው፤ ለነዋሪዎችም ምቹ የሆኑ በምሽት ለሚንቀሳቀሱም ሆነ ለሌሎች የተመቹ ስራዎች ተሰርተዋል። የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የትኛውንም አይነት ዝግጅት ብታሰናዳ አሁን የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ ሊመጥኑ የሚችሉ ስራዎች በኮሪደር ልማት ተከናውነዋል።

ስራ አስኪያጁ የኮሪደር ልማቱ የፈጠረውን የስራ እድል በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል። የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ስራዎች በአንድ መልኩ የነዋሪውን የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት የሚሰሩ ሲሆኑ፣ የስራ እድል ፈጠራም ትኩረት ተደርጎ ተሰርቶባቸዋል። እንደ ከተማ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።

በኮንስትራክሽን ስራም ተቋራጮች በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል። ከቦሌ መገናኛ ኮሪደር ልማትም በተመሳሳይ ኮንትራክተሮችን በመቅጠር፣ በአማካሪነት በተለያየ የምህንድስና ሙያ በርካታ ባለሙያዎች ተቀጥረው እየሰሩ ናቸው።

የአረንጓዴ ስራው ለሰፊ የሰው ኃይል የስራ እድል ፈጥሯል፤ በተጨማሪም የኮሪደሩ ስራው ሲጠናቀቅ ቋሚ የስራ እድል የሚፈጥሩ ተጨማሪ አቅርቦቶች ተገንብተዋል። በኮሪደሩ በየቦታው የተሰሩ ሱቆችም ለወጣቶች የስራ እድል የሚፍጥሩ ናቸው። የካፍቴሪያ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ፣ ለወጣቶች ቋሚ የስራ እድል ይፈጥራሉ። በጊዜያዊ የስራ እድል ፈጠራም በርካታ የከተማዋ ወጣቶች ተጠቃሚ ሆነዋል። በቋሚነት ደግሞ ኮሪደሩ በመጠናቀቁ የሚከፈቱ አገልግሎቶች የስራ እድል በመፈጠሩ በኩል ትልቅ ድርሻ አላቸው።

ከኮሪደር ልማት ስራው ባሻገር ኮሪደሩ በመጠናቀቁ ምክንያት በንግዱ ውስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን መክፈት ጀምረዋል። የቦሌ መገናኛ መንገድ መስመር ላይ የካፍቴሪያ አገልግሎት ብዙ አልነበረም የሚሉት አቶ ጥራቱ፣ ኮሪደሩ ምሽት ላይም በጣም ጨለማ እንደነበረና ለንግድ ስራ ምቹ እንዳልሆነም አስታውሰዋል።

በዚህ ኮሪደር ላይ ካሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር በመነጋገር ለመኖሪያ ወይም ለተለያየ አገልግሎት ዝግ የነበሩ ሱቆቻቸውን ወደ ካፍቴሪያነት እንዲቀይሩ እየተደረገ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል። እነዚህ አገልግሎቶች በመከፈታቸው ምክንያት ተጨማሪ የስራ እድል እንደሚፈጠርም ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው በፈረቃ እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ ቀን ላይ ሲሰራ የነበረ ኦፕሬተር ማታ በሌላ ኦፕሬተር የሚቀየርበት ሁኔታ እንደተፈጠረም ጠቅሰዋል።ይህም አዲስ የስራ ባህል በማምጣት በኩል ልማቱ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሆነም አስረድተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You