ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን በሰላማዊ መንገድ የማሳካት ፍላጎት እንዳላት አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከሕዝብ እንደራሴዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የማይናወጥ ብሔራዊ ጥቅም አላት። ቀይ ባህርን በተመለከተም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር ፍላጎቷን ማሳካት ትፈልጋለች።
ለኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተጠቃሚነት ያስፈልጋታል። አንድ መቶ ሀያ ሚሊየን ሕዝብ ያለባት ሀገር የባሕር በር ተቆልፎባት መቀመጧ ተገቢ አይደለም። ቀይ ባሕር ሰፊ ሀብት ያለው በመሆኑ ሁሉም በጋር ተጠቃሚ መሆን ይችላል። እኛ በገንዘብ ተገዝተን የሆነን ቡድን አጀንዳ የምናራግብ ቅጥረኞች ሳንሆን አርበኞች ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ሀገሪቱ ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ዓለም ጋር በመተባበር የምትፈልገው ሀገር መገንባት ነው ሲሉ አስታውቀዋል። ለመሆኑ የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ እንዴት በዚህ ደረጃ ለሌሎች ሀገራት አጀንዳ ሊሆን ቻለ? ስንል የታሪክ ተመራማሪ ከሆኑት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የባሕር በር የመጠቀም ጥያቄ ከታሪክ አንጻር እንዴት ይታያል ?
ፕሮፌሰር አደም፡– ወደ ጥንቱ ነገር ተመልሰን ከታሪክ ማህደር የምናገኘው ራሱ ቀይ ባሕር የአበሻ የኢትዮጵያ እንደነበረ ነው። ይህ በበርካታ ሥነ ጽሑፎች ተከትቦ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የተካሄዱ ጥናቶችም ይህንኑ አረጋገጠዋል። አንዳንድ የአረብ ሀገራት ጸሐፊዎችም ቦታውን የአበሻ ባሕር ብለው ይጠሩት ነበር። ለእዚህ መነሻው ደግሞ ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት ሥልጣኔም ሆነ ማንኛውም የንግድና ሌሎች የውጭ ግንኙነት ታካሂድ የነበረው በዚሁ በቀይ ባህር በኩል ነበር።
ለዘመናት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ይደረጉ የነበሩት እስላማዊ ስደቶችም ሆኑ የትኛውም የጸሎት እንቅስቃሴዎች ይደረጉ የነበሩት ቀይ ባሕርን መሰረት አድርገው ነበር። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱም ቢሆን ዘመናትን የተሻገረ ሲሆን፤ እስልምና ከመታወጁ በፊት በታወጀበትና ከታወጀ በኋላ ዛሬን ጨምሮ ግንኙነቶች ይደረጉ የነበረው በዚሁ በኩል ነው። እስከ ቅርብ ጊዜም ኢትዮጵያ ወደ መካ መዲና የአየር በረራ አልነበራትም። በዚህም የተነሳ ወደ መካ መዲና ይደረጉ የነበሩ ጉዞዎች የሚከናወኑት ከአዲስ አበባ አስመራ በአውሮፕላን በመሄድ ከዛ በኋላ በምጽዋ ወደብ በኩል ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የአረቡ ዓለም እና ኢትዮጵያ ያላቸው ግንኙነት ጠንካራ አይደለም ይባላል። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ፕሮፌሰር አደም፡- ታሪኩ ረዥም ዓመት ያለው በመሆኑ ሁሉንም ጊዜ ለማውራት አይቻልም። ነገር ግን የቅርብ ጊዜውን እንኳን ብንመለከት ብዙውን ነገር መረዳት እንችላለን። የጅቡቲና የሱማሌያ ሀገራት የአረብ ሊግ አባል ሀገር መሆናቸውና የኤርትራ መገንጠል ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የነበራትን ባለቤትነት እና አጠቃላይ ሁኔታውን እየቀየረው እያዳከመው መጥቷል። ይህ የተደረገበት ራሱን የቻለ ሴራ ስለነበረ ነው።
የአረብ ሀገራት ሊግ ለመቀላቀል አረብኛ ቋንቋን መናገር ግዴታ ነው። ነገር ግን ለምሳሌ የሱማሌ እና የጅቡቲ ሕዝብ አረብ አይደለም። ዛሬም ድረስ አረብኛ ቋንቋ አይናገርም። በመልክዓ ምድር አቀማመጥም ቢሆን እዚህ ላይ በቅድሚያ ነዋሪዎቹን ከግምት አስገብተው የሚወስኑት በመሆኑም እነሱን ሊያካትት አይችልም። መለኪያው የእስልምና እምነት ተከታይ እንኳን ቢሆን፤ ኢትዮጵያ ያላት ሙስሊም ህብረተሰብ ከአፍሪካ ቀንድ ሆነ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከገልፍ ሀገራትም በላይ አቅፋ የምትገኝ ሀገር ናት። በመሆኑም የአረብ ሊግ ለመሆን የእስልምና እምነት ተከታይ ቁጥርን ከግምት የሚያስገባ ከሆነ ኢትዮጵያ ሁሉን መስፈርት ማሟላት ትችላለች። ነገር ግን የአረብ ሊግ አባላት ሀገራትንም ሲያስገባም ሆነ ሥራዎቹን ሲያከናውን የነበረው፤ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከግምት ገብተው አልነበረም። ይህ ለምን ሆነ የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ይህን ማን አደረገው የሚለው ምላሽ የሚሰጠው ይሆናል። ከዚህ ሁሉ ነገር ጀርባ ሆና ሁሉንም ነገር የምታዘጋጀውም የምትጋግረውም ግብጽ ሆና እናገኛታለን።
የአረብ ሊግ ውልንም በተመለከተ መነሻቸው ቢያደርጉ ለምን በኢትዮጵያ ላይ ብቻ የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ምክንያቱም እላያቸው ላይ የፍልስጤም ሕዝብ እየሞተ እየተፈናቀለ እየተራበና እያለቀ ባለበት ሰዓት ላይ ለምን በውላቸው መሰረት መረዳዳቱን መደጋገፉን እዛው ተግባራዊ አያደርጉም። ይህንን ሁሉ ስንመለከት ጉዳያቸው ከግድቡ ጋር ብቻ የተያያዘ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን። ዋናው መታየት ያለበት ለምን የባህር በር እና የግንኙነት ጉዳይ የኢትዮጵያ ሲሆን በልዩነት ይታያል የሚለው ነው። ከዚህ ቀደም እኮ አረብ ኢምሬትስ በበርበራ ላይ ተፈራርማ ነበር። የዛን ጊዜ እንኳን የዚህ ያህል ጩኸት ይቅርና ምንም የተባለ ነገር አልነበረም። ሱማሌ ላንድ እንደ ሀገር ቆማ ራሷን ማስተዳደር ከጀመረች ከሰላሳ ዓመት በላይ ሆኗታል። ከተለያዩ ሀገራትም የውስጥ እውቅናን አግኝታለች። ታዲያ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ለምን ወንጀል እና ነውር ተደርጎ ይወሰዳል?
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚ መሆኗ ግብጽ ወይም ሌሎች ሀገራት ላይ ምን ተጽእኖ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ይገመታል?
ፕሮፌሰር አደም፡- የኤርትራ መገንጠል የኤርትራ ሕዝብ ፍላጎት እንዳልነበር እናውቃለን፤ ይልቁንም መቶ በመቶ የግብጾች ፍላጎት የነበረና ያንንም ያሳካ ውሳኔ ነበር። በተጨባጭም የኤርትራን ማስገንጠል ሥራ የሰራው የተባበሩት መንግሥታትን ለአራት ዓመታት በፀሐፊነት የመራው ግብጻዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ የተባለው ግለሰብ ነው። ኢትዮጵያ ለምን ወደ ቀይ ባሕር እንዳትጠጋ ማለትም ከዛ ገለል እንድትል ተፈለገ፤ የሚለውንም ስናይ ከጅቡቲ እስከ ሱዳን ያለውን ክፍት በር ጠቅልለን በመያዝ በቀይ ባህር በኩል አግልለን የአረብ ሊግ አባል የምትሆን ኤርትራ የምትባል ሀገር መስርተን ቀይ ባህርና አካባቢው በሙሉ የአረብ ሀገራት ንብረት ማድረግ እንችላለን የሚል እቅድ ነድፈው ሲንቀሳቀሱ ነበር።
በርግጥ በዚህ በኩል የውጭ ፖሊሲውን በተመለከተ በእኛ ረገድ ክፍተትም ነበር ለማለት ይቻላል። በእነዚህ ሀገራት ይመደቡ የነበሩ አምባሳደሮች አረብኛ ቋንቋ የማይናገሩ የማያነቡና የማይጽፉ ስለነበሩ እንዲህ አይነት እንቅስቃሴዎችን በየወቅቱ እየተከታተሉ አንዳንድ መረጃዎችንና ማሳሰቢያዎችን ለመንግሥት በማድረስ ረገድ ክፍተት ነበረባቸው። በዚህ ረገድ የውጭ ግንኙነት ደካማ ነበር ለማለት ይቻላል። የእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ጉዳዩን እያደገና እየተወሳሰበ እንዲመጣ አድርገውት ዛሬ ላይ ደርሰናል።
አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄና ጠቀሜታው ከወቅቱ አንጻር እንዴት ይታያል ?
ፕሮፌሰር አደም፡– ይህ ምንም አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም። ንግድን በተመለከተ ከውጭ የምናስገባው ብቻ ሳይሆን እኛ ከፍተኛ ምርት ወደ ውጭ የምንልከው ስላለን ወደብ የግድ ያስፈልገናል። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል የሁለቱንም ሀገራት ፍላጎት ያንጸባርቃል ተብሎ ነበር። ነገር ግን ከኤርትራ ሕዝብ ውጭ ወደቡን በብቸኝነት ስትጠቀመው የነበረችው ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች። አሁንም በብቸኝነት አሰብንም ሆነ ምጽዋን መጠቀም የምትችለው ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ኢትዮጵያ የባህር በር የሚያስፈልጋት ምርቶቿን ወደ ውጭ በመላክና ገቢ በማግኘት ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ፤ ሕገወጥ ፍልሰትን ለማስቀረት አጠቃላይ ድህነትን ለማጥፋት ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የምትፈልገው በሌሎች ላይ ለመዘመት አይደለም፤ ወይንም ተጽእኖ ለማሳደርም አይደለም። አሁንም ቢሆን ዋናው ጉዳይ ከማንም ጋር እንፈራረም፤ ከማንም ጋር እንስማማ፤ ዋናው ነገር የውስጥ አንድነታችንን አጠናክረን ጥቅማችንን ማስጠበቅ መቻላችን ብቻ ነው። በአሁኑ ወቅት ቀይ ባህር ራሱ አካባቢው ሰላም አይደለም። መካከለኛው ምስራቅ እስራኤል፤ ኢራን፤ የመን አጠቃላይ አካባቢው ቀውስና ጦርነት ውስጥ ነው። እዚህ ላይ ሌላው መገንዘብ ያለብን ግብጽ ውስጥ ሰላሳ ሺ የሚሆኑ የሳውዲ ኩባንያዎች ሰባት ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ካፒታል በመያዝ እየተንቀሳቀሱ ናቸው።
የገልፍ ሀገራት ደግሞ የምግብ ዋስትና እና የውሃ ችግር አለባቸው። ግብጾች እነዚህን ሁሉ የሚያስተናግዱትና ለዚህ ምላሽ የሚሰጡት ከኢትዮጵያ በዓባይ አማካይነት የሚሄደውን ውሃና ለም አፈር በመጠቀም ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ሰላም ካገኘችና አንድነቷን ማጠናከር ከቻለች እነዚህን ኢንቨስተሮች ይነጥቁናል የሚልም ስጋት አለባቸው። በርግጥም ኢትዮጵያ ሰላም ከሆነች ምርቶቿን ከመላክ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከመሆን ባለፈ በቱሪዝምም ተመራጭ ሀገር መሆኗ አይቀርም። ከሁሉም በላይ የውስጥ ሰላማችንን ትኩረት ሰጥተን ልንሰራበት ይገባል የምንለው ለዚህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በተመለከተ ጉዳዩ በቀጥታ የማይመለከታቸው የተለዩ ሀገራት ጣልቃ ሲገቡ ይታያል። ይህ ለምን ሊሆን ይችላል?
ፕሮፌሰር አደም፡– ለእዚህ ምላሽ በቅድሚያ የሚሆነው የባሕር በር ጉዳይ በሌሎች አካላት በኩል በአሁኑ ወቅት ተለይቶ ለምን ጫጫታው በዛ የሚለውን ማየት ይጠበቃል። ጉዳዩ በቀጥታ ከግድቡ ጋር የሚያያዝ ነው። ግብጾች እስከ ቅርብ ጊዜ የሕዳሴው ግድብ እውን ይሆናል የሚል ግምት አልነበራቸውም። የግብጽ ፖለቲከኞችና ምሁራን ዓባይን የራሳቸው ንብረት አድርገው ከመመልከት ባለፈ ከፈጣሪ የተሰጠን ስጦታ ነው በማለት፤ እነሱም አምነው የግብጽንም ሕዝብ እስከማሳመን ደርሰው ነበር። በዓባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ምንም መሥራት የለባትም ብቻ ሳይሆን ካለ ግብጽ ፈቃድም መንቀሳቀስ የለባትም የሚልም እምነት አዳብረው ቆይተዋል።
ስምምነታቸውን በተመለከተ በታሪክ በ1902 ዓ.ም እና በ1959 ዓ.ም የነበሩት ስምምነቶች ኢትዮጵያን የሚመለከት አይደለም። ስምምነቱ ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት ሳይሆን ከቀኝ ገዢዎች ጋር የተካሔደ ነበር። ግብጽ በታሪኳ ስትንቀሳቀስ የነበረው አፍሪካዊነቷን ክዳ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ጋር ነበር። በዚህ ረገድ ወደ ስምምነቱም እንድትመጣ የተደረገችው ወዳ ሳይሆን ተገዳ ነበር። ነገር ግን ያልታሰበው ሆነና የሕዳሴው ግድብ በኢትዮጵያውያን ትብብርና ተሳትፎ ለመገንባት በቃ። ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ለግብጽ ትሰጥ የነበረው ውሃ ብቻ ሳይሆን ለም አፈርም ነበር። በዚህ ዓይነት ከሺህ ዓመት በላይ ሲጠቀሙ ቆይተዋል። በቻሉት መጠንም የግድቡን ሥራ ለማደናቀፍ ያልሞከሩት ሴራ ያልደረሱበት ቦታ አልነበርም።
ገና ከጅምሩም ግድቡን በመምታት ለማፈራረስ እቅድም ነበራቸው። ለዚህም ብለው ከፈረንሳይ አውሮፕላን እስከ መግዛት ደርሰው ነበር። ይህ ከፈረንሳይ የተገዛው ቦንብ ጣይ አውሮፕላን ሶስት ሺህ ኪሎ ሜትር በአንድ ነዳጅ ሙሌት መንቀሳቀስ የሚችል ነው። ርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት እንዲያደርግም ለአየር ኃይል አዛዥም መመሪያ ተሰጥቶት እንደነበር በአንድ ወቅት የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል። ነገር ግን ሁሉም ነገር ሳይሳካ ቀረና ግድቡም ተጠናቆ አንደኛውንም ሁለተኛውንም ሶስተኛውን አራተኛው ሙሌት ማጠናቀቅ ተቻለ። እስካሁንም ከስልሳ ሁለት ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ ለመያዝ በመቻሉ የማይደፈርበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ የግብጽ መሪዎች የግድቡን ሥራ ለማስቆም ወይም ለማስተጓጎል ይረዳናል ያሉትን ሁሉ ነገር ሲያደርጉ ነበር። በአካባቢው ሰላም ለማስጠበቅ ነው የሚሉትም ውሸት ነው። ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ገለል ካለች ሰላሳ ዓመት አልፏታል። ነገር ግን ያ አካባቢ አንድ ጊዜም ሰላም ሆኖ አያውቅም። በየመን ሁኔታዎች በየጊዜው መርከቦች ይታገታሉ። በአካባቢው ሌሎችም በርካታ ችግሮች እንዳሉ የአደባበይ ሚስጥር ነው።
አዲሰ ዘመን፡- ግብጻውያን የሕዳሴው ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱንና ወደኋላ እንደማይመለስ ካወቁ ለምን እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ አያነሱም ?
ፕሮፌሰር አደም፡– ከዚህ በፊት ማለትም ባለፉት አስር ዓመታት ገደማ የነበሩት ሁሉም የግብጽ መሪዎች ለሕዝባቸው ግድቡን እናስቆማለን እያሉ በየዘመኑ ቃል ሲገቡ የነበረ ቢሆንም አልተሳካላቸውም። ይልቁንም የግድቡ መጠናቀቅ ሲሰማ ሙሌቱም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሲካሄድ የግብጽ ሕዝብ መንግሥቱን ምን እየሰራችሁ ነው? የገባችሁትን ቃል መፈጸም አልቻላችሁም፤ እያለ በተደጋጋሚ ጥያቄ እያነሳ ይገኛል። ይህንን የሕዝብ ጥያቄና ቁጣ አድበስብሶ ለማለፍ መሪዎቹ በየወቅቱ የተለያዩ አጀንዳዎችን እያስቀመጡ ይገኛል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት የግብጽ መንግሥት ባለሥልጣናት በሱማሌያ በጅቡቲ በኬንያ በኡጋንዳና እየተዟዟሩ የመከላከያ ስምምነት የሚፈራረሙበት ሁኔታ መኖሩን እያየን ነው።
በሌላ በኩል ግብጾች አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን የሚደርስ መለዮ ለባሽ አለን፤ ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ ሰማኒያ ሺህ ያልዘለለ ነው ያላት በሚል ማሸነፍ እንችላለን እያሉም ለሕዝባቸው እንደሚያወሩ ይሰማል። የእነሱ ሠራዊት ግን ስልጠናውም ሆነ ዝግጅቱ የበርሃ ላይ ነው። ሠራዊቱ ራሱ የበርሃ ሠራዊት ነው። ግን ያን ያህል አቅም ያለው አይደለም። ይህም ከእስራኤል ጋር በነበረው ጦርነት በግልጽ ታይቷል። የግብጽ ሠራዊት የእስራኤልን ጦር መጋፈጥ አቅቷቸው ተሸንፈዋል። የተመለሱት የሲና በርሃንና ይቆጠሯቸው የነበሩ ተራሮቹንም አስረክበው ነው።
አጠቃላይ ይህ የግብጽ ባለስልጣናት አካሄድ ለኢትዮጵያ ስጋት ለግብጽ ሕዝብ ተስፋ የሚሰጥ ሳይሆን ለሥልጣን ማራዘሚያነት የሚጠቀሙበት ነው። ይህም ሆኖ የታሪክ ማስረጃዎችን በመጥቀስ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት መግጠም የማይታሰብ መሆኑንም የሚመክሩ የራሳቸው ጸሐፊዎችም አሉ። በመሆኑም አሁን ላይ እንደ አቅጣጫ አጀንዳ ይዘው የሚሰሩት የውስጥ ተቃዋሚና ግጭቶችን በመጠቀም ሃሳባቸውን ለማሳካት ነው። በሀገር ውስጥ ላሉ ተቃዋሚዎች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ኢትዮጵያን ለማዳከም እየሰሩም ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ የግብጽ ሙከራዎች ውጤታማ የመሆናቸው እድል ምን ያህል ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል ?
ፕሮፌሰር አደም፡– ውጤታማ እንደማይሆን እኛ ብቻ ሳንሆን እነሱም ጠንቅቀው ያውቁታል። አንዳንድ የግብጽ ምሁራኖች ከባለፈው ወር ጀምሮ እንደ ማሳሰቢያ እየተናገሩት ያለው ይሄ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ከሆነ ውሎ አድሯል። በመሆኑም ከዚህ በኋላ ግድቡን በተመለከተ የሚወሰዱ ርምጃዎች ቢኖሩ ግጭቱ የሚሆነው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ነው። ይህ ደግሞ የዘላለም ጥልና ጦርነት የሚቀሰቅስ ይሆናል የሚል ነው። በተጨማሪ ጉዳዩ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትንም የሚመለከት ይሆናልም ይላሉ።
ይህም ሆኖ የውስጥ ችግሮችንን ለመፍታት መሰራት ያለባቸው በርካታ ሥራዎች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ችግር እንዳለ እኛም የሚከታተሉንም ግብጾቹ ያውቃሉ። እነሱ ያዋጣናል የሚሉትን ነገር ሁሉ ከመሞከር አይመለሱም። በዚህ ረገድ የቀደመ ታሪካቸው የሚመሰክረውም ይህንኑ ነው። በመንግሥትም በኢትዮጵያ ሕዝብ በኩልም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስፈልገው ሥራ ሁሉ በወቅቱ መሰራት አለበት። በዚህ ረገድ የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት ምሁራንና የፖለቲካ ተሳታፊዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። የውስጥ ጉዳያችንን በውስጥ አቅም መፍታት ያለብን ሲሆን፤ በምንም መልኩ ከሀገራዊ አጀንዳዎች ጋር ማገናኘት የለብንም። በሀገር ውስጥ ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ የምናደርጋቸውም እንቅስቃሴዎች የውጭ ኃይልን ጣልቃ ገብነት የሚጋብዙና የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- በየባህር በር ለማግኘት በመንግሥት በኩል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ዜጎች በምን ዓይነት መልኩ መደገፍ መተባበር ይችላሉ።
ፕሮፌሰር አደም ፡– እኔ በዚህ ረገድ ክፍተት እንዳለ ይታየኛል። በውጭው ዓለም ከሰላሳ ዓመት በላይ ቆይቻለሁ። የሀገር ጥቅምን በማስጠበቅ ረገድ ከሕዝብ ስለሚጠበቀው ነገርም በቂ ግንዛቤ አለኝ። በዚህ ረገድ ከሃይማኖት ተቋማት ብነሳ የየትኛውም ሃይማኖት መሪ በበቂ ሁኔታ እየሰራ አይደለም ለማለት እችላለሁ። ከግብጽ እንቅስቃሴ አኳያ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በተለይም በሚዲያ ዘመቻ ረገድ ምንም እየተሰራ አይደለም ለማለት ያስደፍራል። የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች በሙሉ የግልም የመንግሥትም ትኩረታቸው ሁሉ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ነው። በአንጻሩ ግብጾች የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የአረቡን ዓለም ሚዲያ ሁሉ ተቆጣጥረው እኩይ አላማቸውን ለማሳካት እየተጠቀሙበት ይገኛል። በኢትዮጵያ በኩል ይኸው ሊደረግ ይገባል። ይህ የሀገር የትውልድ ጉዳይ ነው።
በውጭው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የሚጠበቅባቸው በርካታ ዕድሎች አሉ። አስር ሚሊየን የሚደርሱ ግብጻውያን ከሀገራቸው ውጭ በስደት እንደሚኖሩ ይገመታል። ስምንት መቶ ሺ የሚደርሱ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ባለሞያዎች አሏቸው። እነሱ በሁሉ በየሚዲያው በተለይ በአረብኛ በሚተላለፉት ላይ በዚህ ጉዳይ በንቃት ይሳተፋሉ። የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የአንድ አካባቢ ጥያቄ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ ነው። ዲፕሎማቶችም አረብኛ ቋንቋ የሚችሉ የአካባቢውን ባሕሉን የሚያውቁ መመደብ አለባቸው።
በመንግሥት በኩልም ለብዙሃኑ ተደራሽ እንዲሆን የፓናል ውይይቶችን ከማድረግ ጀምሮ፤ በርካታ ሥራዎች የሚጠበቁ ናቸው። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም የሕዳሴን ግድብ በተመለከተ የተናገሩትን እናስታውሳለን። አሁን ደግሞ በምርጫ እየተወዳደሩ ነው። ቢያሸንፉ አጠቃላይ በኢትዮጵያና በግብጽ ግንኙነት ላይ የሚኖራቸው አቋም ምን ይሆናል የሚለውም መታየት አለበት። ለዚህ ደግሞ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብዙ ይጠበቃል። በርግጥ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ድረስ ትኩረት ያደረጉት በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መሆኑ ግልጽ ነው። ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ያኮረፉ አካላትም ቢሆኑ የተለየ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ነገር መሆኑን መገንዘብ አለባቸው።
ከረሀብ እንውጣ፤ ከድህነት እንውጣ፤ ከኋላ ቀርነት እንውጣ የሚል ለውጥ እየታወጀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ግብጾች ኢትዮጵያ ከበለጸገች ለእኛም ሆነ ለአካባቢው ስጋት ትሆናለች ብለው ያስባሉ። በመሆኑም ይህንን ለመቀልበስ ማዳከም አለብን በማለት አጀንዳ አስቀምጠው ውስጥ ለውስጥ እየሰሩ ይገኛል። ይህ ነገር በተለይ የግብጾችን ሚዲያ ለሚከታተል ሰው አዲስ አይሆንም። ግብጾች በርካታ ሚዲያዎች ያላቸው ሲሆን፤ ለቁጥር የሚታክቱ ጋዜጠኞችን በዚህ ላይ እያሰሩም ይገኛሉ። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያ አሁንም በዲፕሎማሲው መስክ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ከቻለች በአረቡ ዓለም የተለየ ቦታ የሚኖራት ይሆናል። ይህንን እድል ለመፍጠርም ለመጠቀምም ከመንግሥትም ከሕዝብ ብዙ ሥራ የሚጠበቅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ጊዜ ከልብ እናመሰግናለን።
ፕሮፌሰር አደም፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም