የባሕር በር ማግኘት ኢትዮጵያ ወደኋላ የማትልበት ይፋዊ አቋሟ ነው !

ኢትዮጵያ ድህነትን ታሪክ አድርጎ ለማስቀረት ለጀመረችው ሀገራዊ መነቃቃት የባሕር በር ጉዳይ ወሳኝ ነው። ጉዳዩን አስመልክታ ያቀረበችው ጥያቄ እና እያራመደችው ያለው አቋም ከሞራልም ሆነ ከዓለም አቀፍ ሕግ አኳያ ተቀባይነት ያለው ነው፤ እውነታውን ወደ አደባባይ ይዛ የወጣችበትም ሆነ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኩል ያገኘው እውቅናም ይህንኑ በተጨባጭ የሚያመላክት ነው።

ኢትዮጵያውያን ከዘመን ዘመን፤ ከትውልድ ትውልድ ከፍ ያለ የመልማት ፍላጎት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው፤ ይህ ከትናንት የታላቅነት ታሪካቸው በብዙ ቁጭት የሚቀዳው የመልማት ፍላጎታቸው በየዘመኑ በብዙ ፈተናዎች ተጨባጭ መሆን ሳይችል ቀርቷል። በየዘመኑም ለዚሁ የመልማት ፍላጎታቸው ያልተገቡ ዋጋዎችን ለመክፈል የተገደዱባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም ።

የሀገሪቱ እና የሕዝቦቿ የመልማት ፍላጎትም ሆነ ለምቶ የመገኘት እውነታ እንደ አንድ ብሔራዊ ስጋት የሚመለከቱ ሀገራት እና ኃይሎች በግልጽም ይሁን በስውር ባካሄዷቸው ሴራዎች በአንድ ወቅት ከአንድም ሁለት፤ ሦስት ወደብ ባለቤት የነበረችውን ሀገር አሁን ላይ የባሕር በር አልባ እንዲሁም በአጭር ርቀት ላይ ከምትገኝበት የቀይ ባሕር ፖለቲካ ባይተዋር አድርገዋታል።

በርግጥ ሀገሪቱ ከመቶ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ፤ በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ እና ለቀይ ባሕር የቀረበ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ይዛ፤ የባሕ ር በር አልባ የመሆኗ ጉዳይ አጠቃላይ በሆነው የሀገሪ ቱ ፖለቲካዊ እና ኢኪኖሚያዊ ላይ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ አኳያ ችግሩ ከራሷ አልፎ ለአካባቢው ሀገራት ሠላም እና መረጋጋት የስጋት ምንጭ መሆኑ የማይቀር ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ይህን ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ስጋት ወደ መልካም ዕድል ለመለወጥ እየተጓዙበት ያለው መንገድ፤ በብዙዎች በኩል ተቀባይነት ያለው፤ ዘመኑን የሚዋጅ እና የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦች የመልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ፤ አካባቢውን ከግጭት አዙሪት ለማውጣትም ስትራቴጂክ እሳቤ እንደሆነም ይታመናል ።

በተለይም የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ከሁሉም በላይ በአካባቢው ሠላም እና መረጋጋት ሰፍኖ ያላቸውን የተፈጥሮ ፀጋዎችን አልምተው ከድህነት እና ከኋላቀርነት ለመውጣት ያላቸውም መሻት ተጨባጭ ለማድረግ ትልቅ ተስፋ እና አዲስ ጅማሬ፤ አካባቢውን አዲስ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ኃይል ለማድረግም መልካም አጋጣሚ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

የተፈጥሮ ፀጋዎችን በጋራ አልምቶ፤ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ሰጥቶ በመቀበል መርሕ እውን ማድረግም መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያውያን አዲስ መንገድ፤ ከሁሉም በላይ በአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ተፈጥሯዊ ወንድማማችነት፤ ከዚህ የሚመነጭ ቀናነትን እና አብሮ የማደግ መንፈስን የሚያጎለብት ነው።

በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል መተማመንን፣ ለጋራ መሻቶች አብሮ መቆምን፤ በዚህም በአካባቢው ዘላቂ ሠላም እና ልማትን ማስፈን የሚያስችል፤ በተሳሳቱ እና በተወናበዱ ትርክቶች በሕዝቦቹ መካከል ተፈጥረው የነበሩ አለመተማመኖችን ማረም የሚያስችል ነው።

ጎረቤት ሀገራት ሆነ መላው ዓለም አሁን ላይ በአግባቡ ሊረዳው የሚገባው ኢትዮጵያ፤ እንደ ሀገር እያነሳችው ያለው የባሕር በር ጥያቄ፤ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመረችው ልማት አንዱ አካል ነው። የልማት ጉዳይ ለሕዝቦቿ የሕልውና ጉዳይ እንደሆነ ሁሉ የባሕር በር ጥያቄዋም በተመሳሳይ መልኩ የሕልውናዋ ጉዳይ ነው።

ሀገሪቱ ካላት የሕዝብ ብዛት እና መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ አኳያም ከሕልውናዋ ጋር የተያያዙ ስጋቶች በአንድም ይሁን በሌላ በጎረቤት ሀገራት ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉት አሉታዊ ተፅዕኖ ለመገመት የሚከብድ አይደለም፤ ለአካባቢው ሀገራት ከፍ ያለ የስጋት ምንጭ መሆኑ የማይቀር ነው። ለቀጣናው ሠላም እና መረጋጋት የሚኖረው ተፅዕኖ ቀልሎ የሚታይ አይደለም ።

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትላንት በስቲያ በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ፤ ኢትዮጵያ ሠላማዊ በሆነ መንገድ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር ያስፈልጋታል ፤ ሀገሪቷ በዚህ ጉዳይ ወደኋላ የማይል ይፋዊ አቋም አላት፤ ይህን ለማሳካትም ሠላማዊ አማራጭን ትከተላለች ማለታቸው!

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You