ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ስታከናውን ቆይታለች። በሪፎርም ሥራዎቹም አዳዲስ፣ ዘመኑንና የሀገሪቱን ራዕይ የሚመጥኑ አሰራሮች እውን ተደርገዋል። ይህን ተከትሎም የአሰራር ለውጦች መጥተዋል፤ አስደናቂ ዕድገቶችም መመዝገብ ጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ገለጻ እንዳስታወቁትም፤ ሀገሪቱ ለረጅም ዓመታት ስትሠራበት የቆየችውን ኢኮኖሚያዊ ፣ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ስርአት ላይ ባለፉት ስድስት ዓመታት ሪፎርሞች አድርጋለች። ሪፎርሞቹ ውጤቶች የተገኙባቸውና ትምህርትም የተቀሰመባቸው መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የጋራ የመክፈቻ ስብስባ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የመንግሥትን የ2017 በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የተያዘው ዓመት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ማንሰራራት የሚጀመርበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ይህ ዓመት በታሪክ አይተናቸው የማናውቃቸውን ውጤቶች እያየን ለትውልድ የምናጸናበትና የምናሸጋግርበት ዘመን የመጀመሪያው ዓመት ነው ብለዋል። በሪፎርም ዘመኑ የማፍታታት ሥራ መሠራቱን አስታውሰው፣ በዚህ የማንሰራራት ዘመንም በርካታ ውጤቶች እንደሚጠበቁ አስታውቀዋል። የማንሰራራት ዓመት የምኞት እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ መንግሥት ባለፉት ዓመታት እንደሆነው ሁሉ የማይነጥፍ ሀሳብ ይዞ እንደሚነሳ፣ ሀሳቡ የሚዳሰስ የሚጨበጥ እንዲሆን መትጋቱን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ባለፉት የሪፎርሙ ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች ብዙ ተደክሞባቸው የተገኙ እንደመሆናቸው በቀጣይም ይህን በላቀ መልኩ ማስቀጠል እንደሚቻል የሪፎርም ሥራዎቹና ውጤቶቻቸው በሚገባ አመላክተዋል።
በሀገሪቱ ለተመዘገቡ ለውጦች የሪፎርሞቹ ሚና ከፍተኛ መሆኑ እርግጥ ነው። የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውና በየዘርፉ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎችን በአብነት ወስደን ብናብራራ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት በሀገሪቱ ከዕቅድ በላይ ስምንት ነጥብ አንድ በመቶ ሀገራዊ እድገት እንዲመዘገብ አስችለዋል። በዝርዝር ስንመለከትም በግብርናው ዘርፍ በስንዴ ልማትና በቡና የተመዘገቡ ዕድገቶች፣ በቀጣይም በሩዝ፣ በሰሊጥና በመሳሰሉት እንደሚመዘገቡ የሚጠበቁ ዕድገቶች፣ በአገልግሎት ዘርፉ የሚታዩ ትላልቅ ለውጦች፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ እያንሰራራ መምጣት ወዘተ የሪፎርሞቹ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታሉ።
ሀገሪቱ ወደ ትግበራ ያስገባችው ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እድገቱን ለማስቀጠል ሁነኛ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፤ ከብዙ ጥናት በኋላ በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ ያስገባቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና እሱን ተከትሎ የወጣው የውጭ ምንዛሬ ግብይት አስተዳደር ስርአት ማሻሻያ የምጣኔ ሀብቱን እግር ከወርች አስረውት ከቆዩ ችግሮች የሚያላቅቁ፣ የውጭ ባለሀብቶችን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ፣ ኢትዮጵያውያን በላኪነት በአምራችነት ወዘተ በስፋት እንዲሰማሩ ዕድል የሚፈጥሩ የታመነባቸው እንደመሆናቸው ሀገሪቱ በቀጣይም የላቀ ዕድገት ለማስመዝገብ እንደምትችል ይጠቁማሉ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መተግበር በጀመረበት በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም እንዲሁ በተለያዩ ዘርፎች ከፍ ያሉ ውጤቶች መመዝገባቸው የዚህ ማሻሻያ ውጤታማነት ማሳያዎች ናቸው። በሩብ ዓመቱ በወጪ ንግድ፣ በግብርናና በመሳሰሉት ዘርፎች ከተመዘገበው እድገት የአንዳንድ ዘርፎች እድገት በእጅጉ ላቅ ያለ ሆኖ ተገኝቷል።
ለዚህም የማእድን ዘርፉ ሊጠቀስ ይችላል። ወደ ብሄራዊ ባንክ ይገባ የነበረው የወርቅ ምርት መጠን እያሽቆለቆለ በ2015 በጀት አመት 4 ቶን ወርቅ ብቻ ነበር ለባንኩ የገባው። ይህ ችግር ግን በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መፍትሄ ማግኘት ችሏል። በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 7 ቶን ወርቅ ለባንኩ ገቢ ተደርጓል። በሩብ ዓመቱም ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ለውጭ ገበያ ተልኮ እንዲሁ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል።
እነዚህ ዕድገቶች በቀጣይ ትልቅ ለውጥ እንደሚመዘገብ አመላካች ስለመሆናቸው መንግሥት አስታውቋል። ሪፎርሞቹን ተከትሎ የተገኙት ውጤቶች፣ ሪፎርሞቹ በቀጣይ ብዙ ለውጥ እንዲመዘገብ እንደሚያስችሉ የታመነባቸው መሆናቸው፣ በተለይ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ይዟቸው የመጣው መልካም ዕድሎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ የምታንሰራራበት ዘመን የሚጀመርበት ዓመት መሆኑን ያበስራ ል።
በተለያዩ ዘርፎች የተቀመጡ ሰፋፊ ዕቅዶች፣ ባለፈው በጀት ዓመት እንደ ሀገር የተመዘገበውን የስምንት ነጥብ አንድ በመቶ ዕድገት በ2017 በጀት ዓመት ወደ ስምንት ነጥብ አራት በመቶ ለማሳደግ መታቀዱ ብቻ ሳይሆን የሩብ ዓመቱ አፈጻጸም ከዚህም በላይ ዕድገት እንደሚመዘገብ ማመላከቱ ይህን ዓመት ይዞ በሀገሪቱ ከፍ ያለ ዕድገት እንደሚመዘገብ እንዲጠበቅ ያደርጋል።
ስለተመኘን ብቻ ለውጦቹ በራሳቸው አይመጡም። ያለፉት ዓመታት ለውጦች በብዙ የሪፎርም ትግበራ ሥራዎች፣ በሕዝብና በመንግሥት የተቀናጀ ጥረት በተለይ በመንግሥት ቁርጠኛ አመራር የተመዘገቡ እንደመሆናቸው በቀጣይም በተለያዩ ዘርፎች የተቀመጡ ዕቅዶችን በላቀ መልኩ ውጤታማ ለማድረግ አቅምን አሟጦ መሥራት ያስፈልጋል።
ለውጡን ለማላቅ ብዙ መሠራት ይኖርበታል፤ ለዚያውም የሚቆጠር ሥራ። መንግሥት እንደ መንግሥት በሀገሪቱ ባለፉት ጥቂት ወራት ለተመዘገቡ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጦች እንደ አንድ ትልቅ አቅም እየተወሰደ ያለውን የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በሚገባ በሚተገበርበት ሁኔታ ላይ በትኩረት መሥራቱን ማጠናከር ይኖርበታል።
በዚህ የማንሰራራት ዘመን የመጀመሪያ ዓመት በሁሉም ዘርፍ የሚቆጠር ተግባር ማከናወን ይጠበቃል። ይህ ዘመን የማንሰራራትና ለትውልድ የማጽናት ዘመን እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስገነዘቡት መሰረት ሁሉም የልማቱ ኃይሎች የተያዙት ሀገራዊ ዕቅዶች በላቀ መልኩ እንዲፈጸሙ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ አማራጭ የሌለው የግድና የግድ መፈጸም ያለበት ተግባር ነው!
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም