ጥገኝነትን ያሰናበቱ የላሊበላ ከተማ ሴቶች

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ ሴቶች የኢኮኖሚ ጥገኛ ናቸው:: አሁንም ቢሆን በተለይ በትምህርት ብዙም ያልገፉና በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በኢኮኖሚ የሚደግፉት ከባሎቻቸው በሚያገኙት ገቢ ነው:: ይህ ደግሞ በእነርሱ ላይ ከሚፈጥረው የስነ ልቦና ጫና ባሻገር በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዳይችሉና ከዚህ ይልቅ በሌሎች ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያስገድዳቸዋል::

ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ቢላቀቁ ራሳቸውን በራሳቸው ከመደጎም አልፈው ለቤተሰባቸውም እንደሚተርፉ ይታወቃል:: ይህ እንዳይሆን ታዲያ በርካታ ማነቆዎች አሉ:: በባህል ተፅዕኖ ምክንያት ሴቶች የማጀት ስራ ላይ ብቻ መጠመድ፣ የቤት እመቤት ሆነው ልጅ እንዲያሳድጉ መገደድ፣ ማህበረሰቡም ለሴት ልጅ ያለው አመለካከት ደካማነትና ሌሎችም ከማነቆዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ:: እነዚህ አስተሳሰቦች አሁንም ድረስ ሴቶች ከማጀት ወጥተው የራሳቸውን ስራ ሰርተው በኢኮኖሚ ቤተሰቦቻውንና ራሳቸውን እንዳይደጉሙ አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠሩ ነው::

ሆኖም አሁን አሁን ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ራሳቸውን የሚያላቅቁባቸው በርካታ ሁኔታዎች በመንግሥትና የልማት አጋር አካላት እገዛ እየተከናወኑ ይገኛሉ:: ከነዚህ ውስጥ አንዱ ሴንተር ፎር አክስለሬትድ ውሜን ኢኮኖሚክ ኢምፓወርመንት የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ድጋፍ በአማራ ክልል ላሊበላ ከተማ እየተከናወነ ያለና ምንም ገቢ የሌላቸውን ሴቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረገ ያለ ፕሮጀክት ነው:: በዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ከሆኑ ሴቶች መካከል ታዲያ ወይዘሮ ጥሩሴት አያሌው አንዷ ናቸው::

ወይዘሮ ጥሩሴት የላሊበላ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ከዚህ ቀደም በአነስተኛ ገቢ ነበር ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት:: ከቀን ስራ የሚያገኟት ገቢ ግን ከእለት ጉርስ የምታልፍ አልነበረችም:: በእነዚህ ሁኔታ ኑሯቸውን እየገፉ ነበር የሚኖሩበት ወረዳ ለስራ አጥ ስልጠና ለመስጠት ምልመላ ሲያደርግ ‹‹ቪሲት ላሊበላ›› ከተሰኘው ፕሮጀክት ጋር የተገናኙት:: በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ታቅፈው በሽምና ስራ የሶስት ወር ስልጠና ወስደዋል::

ስልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ የላሊበላ ከተማ አስተዳደር እርሳቸውን ጨምሮ ለአስራ አምስት ሴቶች በሰጣቸው ቦታ ላይ የሽመና ውጤቶችን በማምረት ምርቶቻቸውን በተለይም ለጎብኚዎች እያቀረቡ ይገኛሉ:: ቀደም ሲል በአካባቢው ላይ የነበረው የጎብኚዎች እንቅስቃሴ ቀዝቃዛ ቢሆንም በአነስተኛ ደረጃ እየሸጡ ነው:: ከሽመና ምርት ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ ነገ ህይወታቸውን እንደሚቀይር ተስፋ ሰንቀዋል:: ከሁሉ በላይ ደግሞ በገቢ ራሳቸውን መቻላቸው ከባለቤታቸው የኢኮኖሚ ጥገኝነት አላቋቸዋል::

ወይዘሮ ሄለን ሙሉጌታ የ‹‹ላሊበላን ይጎብኙ›› ፕሮጀክት አስተባባሪ ናቸው:: እርሳቸው እንደሚሉት የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማ 100 የሚሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና በላሊበላ ከተማ የሚኖሩ ሴቶችን በተለያዩ ስልጠናዎች በማብቃት የራሳቸውን ገቢ እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው:: ፕሮጀክቱ ‹‹ሴንተር ፎር አክስለሬትድ ዉሜን ኢኮኖሚክ ኢምፓወርመንት›› በተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን በአራት ዘርፎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል:: እነዚህም ሽመና፣ የሸክላ ስራ፣ ንብ ማነብና የማስጎብኘት አገልግሎት ናቸው:: የሚሰጡ ስልጠናዎችም እነዚህን ዘርፎች ኢላማ ያደርጋሉ::

ፕሮጀክቱን ለማስፈፀም በ ጂ አይ ዜድ ከ250 ሺ ፓውንድ በላይ የተመደበ ሲሆን እ.ኤ.አ ከህዳር 2023 እስከ ግንቦት 2024 ይቆያል:: የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚዎችም እድሜያቸው ከ18 እስከ 40 የሚሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የላሊበላ ሴቶች ናቸው:: በሽመና ስራ 15 ሴቶች የሶስት ወር የክህሎት ስልጠና ተከታትለው በማጠናቀቅ ወደ ስራ ገብተዋል:: የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት /COC/ ወስደዋል::

ሴቶቹ ወደ ፕሮጀክቱ ተመልምለው የሚመጡት አነስተኛ ገቢ ያላቸው መሆኑ በላሊበላ ከተማ ወረዳዎች የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ተረጋግጦ ነው:: በሽመና ስራ ሰልጥነው ወደ ስራ የገቡ ሴቶች ከወረዳዎች በተሰጣቸው መሸጫ ሱቆች አማካኝነት የሽመና ውጤቶችን ለጎብኚዎች በመሸጥ ራሳቸውን እየደጎሙ ይገኛሉ:: ይህም ራሳቸውን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲያላቅቁ አስችሏቸዋል::

በሌላ በኩል 15 ሴቶች ደግሞ በሸክላ ስራ ዘርፍ በተመሳሳይ የሶስት ወር የክህሎት ስልጠና ወስደው በማጠናቀቅ ወደ ስራ ገብተዋል:: 20 ሴቶች በቱሪስት አስጎብኚነት የአስር ቀን ክህሎት ስልጠና ከሁለት ወር የእንግሊዘኛ ቋንቋና ተግባቦት ክህሎት ጋር ተከታትለው አጠናቀዋል:: በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የአስጎብኚ ስክሪፕት ተዘጋጅቶላቸው ወደ አስጎብኚነት ስራ ለመግባት ብሄራዊ ፈተና ለመውሰድ እየተጠባበቁ ይገኛሉ:: የቱሪስት አስጎብኚ ማህበሩን ለማጠናከር ታላሚ ያደረገ የአንድ ቀን ዎርክሾፕም በላሊበላ ተዘጋጅቷል::

በማርና በማር ተረፈ ምርት ላይ ትኩረቱን ያደረገና በላሊበላ ያለውን የማር ምርት አቅም ለማወቅ ምዘና ተካሂዷል:: በዚህ ዘርፍ ላይም ተሳታፊ ሆነው ራሳቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ 15 ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶች ከአምስት ወረዳዎች ተመርጠዋል:: የአምስት ቀን የክህሎት ስልጠና ለመውሰደም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ:: ሴቶቹ ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ከማር ተረፈ ምርቶች የተለያዩ ጌጣጌጦችን ለጎብኚዎች በማዘጋጀትና በመሸጥ ራሳቸውን እንደሚደጉሙ ይጠበቃል::

አስተባባሪዋ እንደሚሉት ሴቶቹ በወሰዱት የክህሎት ስልጠና ብቁ ሆነዋል:: በመንግሥትም የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ወስደው አልፈዋል:: የተለያዩ ምርቶችን አምርተው ለገበያ እያቀረቡም ይገኛሉ:: ምርቶቻቸው ካልተሸጡ ግን ሴቶቹ ገቢ አግኝተው ራሳቸውን መቀየር አይችሉም:: ስለዚህ ምርቶቻቸው እንዲሸጡ የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራ እየተከናወነ ይገኛል:: በሀገር ውስጥና በውጪ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ አባላት አሉ:: እነዚህ አባላት ሴቶቹ የሚያመርቷቸውን ምርቶች በመውሰድ ለገበያ እንዲያቀርቡላቸው የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ነው::

የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ የላሊበላ ከተማ አስተዳደርም ትልቅ ስራ ሰርቷል:: በተለይ ሴቶቹ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡባቸውን ሱቆች በመስጠት የገበያ እድል እንዲፈጠርላቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል:: ሴቶቹም በተሰጣቸው ሱቆች ውስጥ የሽመናና የሸክላ ስራ ውጤቶችን ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ:: እስካሁን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሽመና ሰልጣኞች ምርቶቻቸውን በመሸጥ 43 ሺ 456 ብር ማመንጨት ችለዋል:: የሸክላ ስራ ሰልጣኞች ደግሞ 13 ሺ 711 ብር አመንጭተዋል::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You